ጦርነቱ እንዲቆም ዩክሬን ግዛቷን ለሩሲያ አሳልፋ ትሰጣለች? ዩክሬናውያንስ እንዴት ይመለከቱታል?

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዠዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአላስካ ከመገናኘታቸው ከቀናት በፊት ለሰላም ቅድመ ሁኔታው "የመሬት መለዋወጥ" ሲሉ የጠሩት ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የሩሲያና ዩክሬንን ጦርነት ለመቋጨት የትኛው መሬት ላይ ነው ልውውጥ የሚካሄደው? የሚለው በርካታ ዩክሬናውያንን ግራ ያጋባ ሆኗል።
ሩሲያ በወረራው ወቅት ለያዘቻቸው ግዛቶች ቅያሪ የሚሆን ቦታ ከግዛቷ ከፍላ ለዩክሬን ትሰጣለች? የሚል ጥያቄንም አጭሮ ነበር።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዋሽንግተን ላይ እየተጠበቁበት ባሉበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚያስቡትን "የመሬት ልውውጥ" እንዳላሰቡ ያሳየ ነው።
እንዲያውም ትራምፕ እየተዘጋጁ ያሉት የዩክሬንን አጠቃላይ ምሥራቃዊ ግዛቶችን ዶኔትስክ እና ሉሃንስክን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ለሩሲያ እንዲያስረክቡ ጫና ለማድረግ ማቀዳቸው ተዘግቧል።
በምላሹም ሩሲያ በተለያዩ ጦር ግንባሮች የምታደርገውን ግስጋሴ ትገታለች።
ይህንን ዕቅድ ያቀረቡትም ፑቲን በአላስካው ውይይት እንደሆነ ዘገባዎች ጠቁመዋል።
የሉሃንስክ ግዛት ሙሉ በሙሉ በሩሲያ ቁጥጥር ውስጥ ናት።
ሆኖም ዩክሬን ቁልፍ ከተሞች እና ምሽጎችን ጨምሮ 30 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክ ግዛትን በሺዎች የሚቆጠሩ የወታደሮቿን ሕይወት ገብራ ተቆጣጥራ ትገኛለች።
ዶንባስ እና ሉሃንስክ በመባል የሚታወቁት ሁለቱ ግዛቶች በማዕድን እና በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ናቸው።
እነዚህን ግዛቶች በአሁኑ ወቅት ለሩሲያ አሳልፎ መስጠት "አሳዛኝ" እንደሆነ ዩክሬናዊው የታሪክ ተመራማሪ ያርሶላቭ ህርይትሳክ ያስረዳሉ።
"ይህ የዩክሬን ግዛት ነው" የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው "የእነዚህ ግዛቶች ሕዝብ በተለይም ማዕድን አውጭዎቹ ለዩክሬናዊ ማንነት መጠናከር ትልቅ ሚና የተጫወቱ ናቸው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ዶንባስ "ታዋቂ ፖለቲከኞችን፣ ገጣሚዎችን እንዲሁም ተቃዋሚዎችን" ያፈራ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
የሩሲያ አካል ከሆነ ወደቤታቸው መመለስ የማይችሉ ስደተኞች ይኖራሉ።
ሩሲያ በዶንባስ ክልል በአውሮፓውያኑ 2014 የጀመረችውን ጥቃቶች ተከትሎ ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዩክሬናውያን ሸሽተው ተሰደዋል።
ሦስት ሚሊዮን የሚገመቱ ዩክሬናውያን ሩሲያ በወረራቻቸው መሬት ይኖራሉ።
ዩክሬን በምትቆጣጠራቸው ግዛቶች 300 ሺህ ያህል ነዋሪዎች እንዳሉ ይገመታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለጦር ግንባሮች ቀረቤታ ባላቸው ስፍራዎች መኖር በራሱ አደገኛ ትግል ነው።
ለወታደሮች እና ለቤተሰቦቻቸው መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡት የ55 ዓመቱ አንድሪ ቦርይሎ በጦርነት ክፉኛ በተመታችው ስሎቪያንስክ ይኖራሉ።
ከቀናት በፊትም ከቤታቸው አቅራቢያ የከባድ መሳሪያ ስብርባሪ ወድቋል ይላሉ።
"በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው" የሚሉት አንድሪ "የመሰላቸት እና የመረሳት ስሜት ይሰማናል። ይህንን ለመቋቋም ምን ያህል ጽናት እንዳለን አላውቅም። የሚጠብቀን ሰው ያስፈልገናል። ግን ማን? " ሲሉ ይጠይቃሉ።
አንድሪው የአላስካውን ውይይት በነቃ መንፈስ ተከታትለዋል።
"ይህንን ያደረገው ትራምፕ እንጂ ዜሌንስኪ አይደለም። ሁሉንም ነገሬን እየወሰዱብኝ ነው፤ ይህ ክህደት ነው" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ለሰላም ሲባል ተቆጣጥረው የያዙትን ግዛት ለሩሲያ አልሰጥም ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ሩሲያ ይህንን ግዛት ከተሰጣት በኋላም በጠቀለለቻቸው ግዛቶች ተወስና ለወደፊቱ ጥቃት አትፈጽምም ለሚለው መተማመኛ የለም።
በእነዚህም ምክንያቶች 75 በመቶ የሚሆኑት ዩክሬናውያን ለሩሲያ መሬታቸውን አሳልፈው መስጠት የሚቃወሙት እንደሆነ የኪየቭ ዓለም አቀፍ የሶሺዮሎጂ ተቋም ያደረገው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ ያሳያል።
ሆኖም ዩክሬን በጦርነቱ ተዳክማለች።
በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች ተገድለውባታል።
በርካታ ዩክሬናውያን በተለይም በዶንባስ ክልል የሚኖሩ ይህ ሰቆቃ እንዲያከትም ይፈልጋሉ።
"የዶኔትስክ ግዛትን አሳልፎ ስለመስጠት ትጠይቃላችሁ። ይህንን ጦርነት በኪሎ ሜትሮች ሳይሆን በሰዎች ሕይወት ነው የምለካው" ሲሉ በዶኔትስክ ግዛት ክራማቶርስክ ከተማ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ የሆኑት ይቭሄን ትካቾቭ ያስረዳሉ።
"ለበርካታ ሺህ ኪሎ ሜትሮች መሬት ሲባል በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሕይወት እንዲጠፋ ዝግጁ አይደለሁም። የሰው ልጅ ሐይወት ከግዛት በላይ ነው" ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ለአንዳንዶች አማራጩ መሬት ወይስ ሕይወት የሚለው ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ "በመስቀለኛ መንገድ ላይ ሲሆን የትኛውም ግን ጥሩ አማራጭ አይደለም" ሲሉ የዩክሬን ተቃዋሚ ፓርቲ ዩሮፒያን ሶሊዳሪቲ አባል እና የፓርላማ አባሉ ቮሎድሚር አሪዬቭ ይናገራሉ።
"ጦርነቱን ላልተወሰነ ጊዜ ለማስቀጠል የሚያስችል በቂ ኃይል የለንም። ነገር ግን ዜሌንስኪ ይህንን መሬት አሳልፎ ቢሰጥ የሕገ መንግሥቱ መፈራረስ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ክህደትም ሊታይ ይችላል" ይላሉ።
መሬት ለሩሲያ ይሰጥ ቢባል እንኳን በዩክሬን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ስምምነት የትኛውን መንገድ ተከትሎ ሊደረስ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
ማንኛውም መደበኛ የግዛት ርክክብ የፓርላማው ይሁንታ እንዲሁም የነዋሪው ሕእዝበ ውሳኔ አስገዳጅ ነው።
ሌላኛው ሊሆን የሚችለው መሬቱን በመተው በሩሲያ አካልነት መደበኛ እውቅና አለመስጠት ነው።
በዚህም ሁኔታ ቢሆን ሂደቱ ግልጽ እንዳልሆነ ሌላኛዋ የፓርላማ አባል ኢና ሶቭሱን ያስረዳሉ።
"ፐሬዝዳንቱ ዝም ብለው ስምምነቱን ይፈርማሉ? መንግሥት ነው የሚፈርመው? ወይስ ፓርላማው? ለዚህ የተዘረጋ ሕጋዊ አሠራር የለም፤ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁ ሰዎች ይህንን አላሰቡበትም" ይላሉ።
ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር በዋይት ሐውስ ከተነገጋሩ በኋላ የበለጠ ግልጽ ሊሆኑ ይችላሉ።
ዜሌንስኪ በአላስካው የሁለቱ መሪዎች ጉባኤ በአብዛኛው ደስተኛ ባይሆኑም፤ ለዩክሬን አንድ ጥሩ ጭላንጭልን የጠቆመ ሆኗል።
ትራምፕ ከሩሲያው መሪ ጋር ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ለዩክሬን የወደፊት የፀጥታ እና የደኅንነት ዋስትና ላይ የያዙትን አቋም በመቀየር፤ ለወደፊቱ ሩሲያ ከምታደርገው ጥቃት ለመከላከል ከአውሮፓ አጋሮቻቸው ጋር በመጣመር ጥበቃ ለማዘጋጀት አቅደዋል።
ለዩክሬናውያን ከየትኛውም በላይ የደኅንነት ዋስትናዎች የስምምነቱ ቀዳሚ ሁኔታ ሊሆኑ እንደሚገባ የሕዝብ አስተያየቶች ጠቁመዋል።
"የዩክሬን ሕዝብ የተለያዩ ዓይነት የደኅንነት ዋስትናዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነው። እነዚህን በዋናነት አጥብቀው ይሻሉ" ሲሉ የኪየቭ ዓለም አቀፍ የሶሺዮሎጂ ተቋም ዳይሬክተር አንቶን ግሩሼትስኪ ያስረዳሉ።
ለድንገተኛ አደገኛ ሠራተኛው ይህሄን ትካቾቭ የግዛት ልውውጥ ሊታሰብ የሚችለው "በተጻፈ ቃል ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ ዋስትናዎች ብቻ ነው" ይላሉ።
"ለምሳሌ የብሪታኒያ የሮያል የባሕር ኃይል በኦዴሳ ወደብ ላይ የሚሰማራ ከሆነ ዶንባስን ለሩሲያ ለመስጠት ደግፌያለሁ ለማለት እችላለሁ" ሲል ያስረዳል።
ስምምነቶች በሚፈጸሙበት ወቅት አንዳንዴ መሬት ላይ ያሉ ሰዎችን ሕይወት መዘንጋት ይታያል።
ዶንባስ ከሁሉም ዓይነት የኑሮ ደረጃ የተውጣጡ ዩክሬናውያን መኖሪያ እንደነበረች የሚናገሩት የታሪክ ባለሙያ የሆኔት ቪታሊ ድሪብንይትሲያ ናቸው።
"ስለ ባህል፣ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ሥነ ሕዝብ አወቃቀር ብቻ አይደለም እየተናገርን ያለነው። ስለ ሕዝብ ነው እያወራን ያለነው" ይላሉ።
ዶኔትስክ በዩክሬን ውስጥ በባህል ቁንጮነት ከሚቀመጡ አንዷ እንደሆነችው ኦዴሳ ዝነኛ ላትሆን ብትችልም የዩክሬን አካል ናት ይላሉ።
"የትኛውም የዩክሬን ማዕዘን አንዳንድ ትልቅ ባህላዊ ጠቀሜታ ኖረውም አልኖረውም፤ የዩክሬን አካል ናቸው" ብለዋል።















