ትራምፕ እና ፑቲን በቀጣዩ በሞስኮ? ከአላስካው የመሪዎቹ ውይይት የተወሰዱ አምስት ቁልፍ ጉዳዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለዩክሬን ጦርነት ሰላማዊ እልባት ይሰጣል በሚል በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ውይይት በአላስካ ተካሂዷል።
ሁለቱ መሪዎች ለሶስት ሰዓታት ገደማ ያደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ሳያፈራ ተጠናቋል።
ፑቲን ለትራምፕ ወደ ሞስኮ በቀጣዩ እንዲመጡ የጋበዟቸው ሲሆን፤ የሁለቱ መሪዎች ውይይት በርካታ ጥያቄዎችን ያጫረ ሆኗል።
ከአላስካው ውይይት የወሰድናቸው አምስት ቁልፍ ነገሮች:-
የፑቲን ወደ አለም ዓቀፉ መድረክ መመለስ
ምዕራባውያኑ ያገለሏቸው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት ወደ አላስካ ሲገቡ ሰማዩ ደመናማ ነበር።
በአላስካ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ወደሆነው ጆይንት ቤዝ ኤለመንሮርፍ ሪቻርድሰን ሲደርሱም ቀይ ምንጣፍ ተዘርግቶላቸው በማኮብኮቢያው አንደኛው ጫፍ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሊቀበሏቸው እየተጠባበቋቸው ነበር።
ፑቱን ሲቃረቡም፤ ትራምፕ አጨበጨቡ። ሁለቱ መሪዎች ሞቅ ባለ ሁኔታ ተጨባብጠው ፈገግታ ተለዋወጡ።
ሩሲያ ከሶስት ዓመት ገደማ በፊት ዩክሬንን መውረራሯን ተከትሎ ፑቲን በምዕራባውያኑ አገራት ተገልለው ይገኛሉ።
የዓለም አቀፍ ጉዟቸውም ውስንና ከሩሲያ ጋር ወዳጅነት ባላቸው እንደ ሰሜን ኮሪያ እና ቤላሩስ ባሉ አገራት ሆኗል።
የአላስካው ውይይት መደረጉ ለፑቲን ድልን ያቀዳጀ ነው።
ምዕራባውያኑ ዓይን ለአፈር ያሏቸው ፑቲን በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዘንድ እንደ አጋር እና ወዳጅ እየታዩ ነው። ፑቲን ውይይት ወደሚደረግበት ስፍራ ሲያቀኑም በራሳቸው ፕሬዚዳንታዊ መኪና አልነበረም።
ባልተጠበቀ ሁኔታም በትራምፕ ሊሞዚን ነው የተሳፈሩት።
ፑቲን በመኪናው ከኋላ ተቀምጠው ሲስቁም ታይተዋል።
ሆኖም ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ አልነበረም።
በአገራቸው ያለውን የፕሬስ ነጻነት በማፈና ምህዳሩን አጥበዋል የሚባልላቸው ፑቲን አላስካ እንደገቡም ከአንድ ጋዜጠኛ ያልጠበቁት ጥያቄ ተወርውሮባቸዋል።
"ሲቪሎችን መግደል ታቆማለህ?" የሚል ጥያቄ የተጠየቁት ፑቲን ምላሽም አልሰጡም፤ ጥያቄው የረበሻቸውም አይመስልም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መሪዎቹ ፎቶ ሊነሱ ባሉበትም ወቅት በርካታ ጥያቄዎች ወደ ፑቲን ተሰንዝሯል።
በሩስኪ ቋንቋ ከፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር ይገናኙ እንደሆነም የተጠየቁ ሲሆን ፑቲን ለየትኛውም ምንም ምላሽ አልሰጡም።
መሪዎቹ ጥያቄ ያልተቀበሉበት ጋዜጣዊ መግለጫ
ፑቲን እና ትራምፕ ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የአለማችን ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ እየተጠባበቁ ወደነበሩበት ክፍል አቀኑ።
ሁለቱ መሪዎች መግለጫ ቢሰጡም፤ ከጋዜጠኞች ምንም አይነት ጥያቄ አልተቀበሉም ።
ፑቲን ነበሩ መጀመሪያ ንግግር ያደረጉት። "በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ ገንቢ ውይይት የነበረው ድባብ ነበር" ሲሉ አወድሰው፤ አላስካም የቀድሞ የሩሲያ ግዛት መሆኗን ጠቅሰው አለፉ።
ፑቲን ንግግር ሲያደርጉ ትራምፕ በዝምታ ቆመው ነበር።
ፑቲን፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ነበር ለውይይታቸው መነሻ የሆነውን "የዩክሬን ሁኔታ" በሚል የጠቀሱት።
የሩሲያው መሪ ምን እንደሆነ ያልገለጹት "ስምምነት ላይ" መደረሱን ጠቅሰው፤ ሰላም ከመመምጣቱ በፊት "የግጭቱ መሰረታዊ መንስዔ" ዕልባት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አስምረዋል።
ፑቲን በዚህም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የተኩስ አቁም እንቅፋት ሲሏቸው የነበሩ ጉዳዮችን አመላክተዋል። የዩክሬን ግዛቶች የሚባሉት እና በአብዛኛው ተቆጣጥረው የሚገኙትን ክሪሚያ፣ ዶኔትስክ፣ ሉሃንስክ ፣ ዛፖሪዝዝሂያ እና ኬርሶን የሩሲያን ሉዓላዊነት ዕውቅና መስጠት ፤ ፑቲን ከዚህ ቀደም ሲጠቅሱት የነበረ ጉዳይ ነው።
ዩክሬን ወታደራዊ ትጥቆቿን እንድትፈታ፣ የገለልተኝነት አቋም እንዲኖራት፣ የውጭ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንድታስወግና ምርጫ እንድታደርግ የሚጠይቀው ደግሞ ሌላኛው የሩሲያ ጥያቄ ነው።
ይህንን እርምጃ በሩሲያ የግዛቷ መጠቅለል እንደሆነ ለምታምነው ዩክሬን ይህ ተቀባይነት የለውም።
በዚህም በዚህ ጉባኤ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ ያሳየ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ ጭምትነት የታየበት መግለጫ
ትራምፕ ተራቸው ደርሷቸው ሲናገሩ በአስደናቂ ሁኔታ ዩክሬንንም ሆነ የተኩስ አቁም ሊደረስ እንደሚችል አልጠቀሱም።
ትራምፕ ግጭቱን አስመልክቶ የተናገሩት ጉዳይ ቢኖር "አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት ሺሀ ሰዎች በሳምንት እየተገደሉ ነው፤ ፑቲንም ይህ ደም መፋሰስ እንዲቋጭ ይፈልጋሉ" በሚል ነበር።
ብዙ በማውራት የሚታወቁት ትራምፕ በዚህ ወቅት ከፑቲን ባነሰ መልኩ ነው የተናገሩት። በዚህም መግለጫ ላይ ጭምትነት የታየባቸው ሲሆን፤ መግለጫቸው አጭር፣ ያልተለመደ እንዲሁም በዋነኝነት ግልጽነት የጎደለው ነበር።
"የተስማማንባቸው በርካታ ነጥቦች ነበሩ" ያሉት ትራምፕ "በጣም ውጤታማ በሆነው በዚህ ስብሰባ ከፍተኛ መሻሻል የተገኘበት ነው" ብለዋል።
ሆኖም ከፍተኛ መሻሻል ስላሉት ጉዳይ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ለዩክሬን ጦርነት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃዎች የተወሰዱም አይመስልም። ስምምነቶችም ሆነ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ያሳተፈ የሶስትዮሽ ስብሰባ አልተገለጸም።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ካልደረሰች "ከባድ ቅጣት ይጠብቃታል" የሚለውን ማስጠንቀቂያቸውን በዚህ ወቅት አላነሱትም።
የፑቲን ወደ ሞስኮ ግብዣ
የመሪዎቹ ጉባኤ በዩክሬን ሰላም ለማምጣት ምንም አይነት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ባይችልም፤ ነገር ግን በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ንፋስ ገብቶበት የነበረውን ግንኙነት ወደ መቀራረብ አምጥቶታል።
ሁለቱ መሪዎች በተደጋጋሚ እጃቸውን ሲጨባበጡና ፈገግታ ሲለዋወጡ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጋርተዋል።
እንዲሁም አሜሪካውያን አገልግሎት ሰጭዎች ፑቲን ለሚራመዱበት ቀይ ምንጣፍ ሲዘረጉ የሚያሳይ ምስልም እንዲሁ።
ፑቲን ንግግራቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት ትራምፕ በተደጋጋሚ የሚሉትን በማንጸባረቅ፤ ትራምፕ በስልጣን ላይ ቢሆኑ የዩክሬን ጦርነት አይነሳም ነበር ብለዋል።
ትራምፕ በዚህ ውይይት "ታላቅ መሻሻል" ታይቷል ቢሉም በአላስካው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ምንም አይነት ተጨባጭ ነገር አልተገለጸም።
ሆኖም ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በመጪው ውይይት ሊኖር እንደሚችል በሩን ክፍት አድርገውታል፤
ምናልባትም በሩሲያ ምድር ሊሆን ይችላል።
"በቅርቡ እንደገና አይሃለሁ" ሲሉ ነበር ትራምፕ ወደ ፑቲን እያዩ የተናገሩት።
ፑቲን ባልተለመደ ሁኔታ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ፈገግ ብለው ወደ ትራምፕ እየተሞለከቱ "በሚቀጥለው ጊዜ በሞስኮ" አሉ።
ትራምፕም በምላሹ "ያ አስገራሚ ነው፤ ምናልባትም ትችት ሊደርስብኝ ይችላል። እንደሚሆን ግን ይታየኛል" በሚል ነበር የመለሱት።















