ትራምፕ ፑቲን የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም ፈቃደኛ ካልሆኑ 'ከባድ ቅጣት' እንደሚጠብቃቸው አስጠነቀቁ

ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን
የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት በአላስካ ተገናኝተው በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሁለቱ መሪዎች በአላስካ የሚያደርጉትን ስብሰባ ተከትሎ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆም ፈቃደኛ ካልሆኑ "በጣም ከባድ ቅጣት" እንደሚጠብቃቸው አስጠነቀቁ።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ረቡዕ ዕለት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው።

የአውሮፓ መሪዎች ረቡዕ ዕለት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በቪዲዮ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት በአላስካ ተገናኝተው የዩክሬን ጦርነት የሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ የስብሰባው ዓላማ በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ መሆኑን ለአውሮፓውያን መሪዎች መናገራቸው ተዘግቧል።

በተጨማሪም ማንኛውም የግዛት ጉዳዮች ቮልዲሚር ዜሌንስኪ በተሳተፉበት መወሰን እና የደህንነት ዋስትናዎች የስምምነቱ አካል መሆን እንዳለባቸው መስማማታቸውን የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናግረዋል።

ማክሮን ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ውይይት "ሃሳባቸውን እንዲያብራሩ" እና አውሮፓውያን "የምንጠብቀውን እንድንገልጽ" ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል።

ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ጄዲ ቫንስ የዩኬ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የኢጣሊያ፣ የፊንላንድ እና የፖላንድ መሪዎች እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ኃላፊ ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን እና የኔቶ አዛዥ ማርክ ሩትን አነጋግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አውሮፓውያን በአላስካ በተዘጋጀው የሁለቱ መሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ያልተጋበዙ ሲሆን ረቡዕ ላይ በነበራቸው የስልክ ውይይት የዩክሬንን ጥቅም እና የአህጉሪቱን ደህንነት የትራምፕ ግንባር ቀደም አጀንዳ ለማድረግ ያደረጉት የመጨረሻ ሙከራ ነበር።

የመሪዎቹ ጥረት በመጠኑም ቢሆን የሚሰራ ይመስላል።

ረቡዕ ምሽት ትራምፕ ስብሰባውን "10" በመስጠት የገለፁት ሲሆን፣ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ "በጣም ከባድ መዘዝ" እንደሚጠብቃት ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአርቡ ስብሰባ ጥሩ የሚሆን ከሆነ ፑቲን እና ዜሌንስኪን የሚያሳትፍ "ፈጣን ቀጣይ" ስብሰባ ለማዘጋጀት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።

የአውሮፓ መሪዎች በመግለጫቸው ኪየቭ በማንኛውም የመጨረሻ ውሳኔ ውስጥ መሳተፍ እንደሚኖርባት አሳስበዋል።

ፑቲን የተኩስ አቁም ለማድረግ በምትኩ የዩክሬንን ግዛት ለመውሰድ ትራምፕን ያሳምኗቸዋል የሚል ፍርሃት አሁንም በአውሮፓ መሪዎች ዘንድ ገዝፎ ይታያል።

የፖላንዱ ዶናልድ ተስክ "አውሮፓ ዶናልድ ትራምፕን ማንም ሩሲያን ማመን እንደማይችል ማሳመኗ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ ግን መሪዎቹ "ቀጣይ ስብሰባዎች ሲደረጉ ዩክሬን በስብሰባው ላይ መገኘት እንዳለባት ግልፅ አድርገዋል" ብለዋል ።

ሩሲያ በዚህ የማትስማማ ከሆነ "ዩናይትድ ስቴትስ እና እኛ አውሮፓውያን ግፊታችንን መጨመር አለብን" ብለዋል ሜርዝ።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ እና የሩሲያ መሪዎች በአላስካ ተገናኝተው በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ፣ትራምፕ በኪየቭ እና በሞስኮ መካከል የሚኖረውን "የመሬት ልውውጥ" በተመለከተ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ በዩክሬን እና በአጋሮቿ ዘንድ ትራምፕ የፑቲን የረጅም ጊዜ ፍላጎት የሆነውን የዩክሬን ግዛትን መውሰድ ይደግፉ ይሆናል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ረቡዕ ማለዳ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሌክሲ ፋዴቭ የሩሲያ አቋም ፑቲን በሰኔ 2024 ካስቀመጡት እንዳልተቀየረ በድጋሚ ተናግረዋል።

በወቅቱ ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነት የሚደረሰው የዩክሬን መንግሥት በከፊል በሩሲያ ከተያዙ አራት ክልሎች ማለትም ዶኔትስክ፣ ሉሃንስክ፣ ኬርሰን እና ዛፖሪዝህዝሂያ ለቅቆ በሚወጣበት ደቂቃ ነው ብለው ነበር።

በተጨማሪም ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እርግፍ አድርጋ በይፋ መተው አለባት ብለዋል።

እነዚህ በሩሲያ መንግሥት የተቀመጡ መደራደሪያዎች ኪየቭም ሆኑ የአውሮፓ አጋሮቿ አይቀበሏቸውም።

ዜሌንስኪ ሩሲያ እንድትቆይ በሚፈቀድላት የትኛውንም ክልል በመጠቀም ወደፊት ወረራዋን ታስፋፋለች ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

ለዚህ ስጋት ምላሽ ለመስጠት አንዱ መንገድ ዩክሬንን ለረዥም ጊዜ ለመጠበቅ ቃል በመግባት የደህንነት ዋስትናዎችን መስጠት ነው።

የጀርመኑ ፍሬድሪክ መርዝ እና ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪን በሙኒክ ተገናኝተው ተነጋግረዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የጀርመኑ ፍሬድሪክ መርዝ እና ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪን በሙኒክ ተገናኝተው ተነጋግረዋል

በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ከትራምፕ ጋር የስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዲህ ዓይነት ዋስትናዎች እንደተጠቀሱ ያስታወቁ ሲሆን፣የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በዚህ ረገድ ትክክለኛ መሻሻል መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ትራምፕ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።

"ለሦስት እና ከዚያ በላይ ዓመታት ይህ ግጭት ቀጥሏል እናም ወደ ተኩስ አቁም ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ መፍትሄ ላይ አልደረስንም። አሁን ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ጥረት ያንን ዕድል አግኝተናል" ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሣይ "የፈቃደኞች ጥምረት" እየተባለ የሚጠራውን ሩሲያ ዩክሬንን ከተጨማሪ ወረራ ለመከላከል ቃል የገቡ አገራት ስብስብ ለመፍጠር ጥረቶችን በመምራት ላይ ናቸው።

ረቡዕ ዕለት ቡድኑ "ጦርነቱ ካቆመ በኋላ የሚያረጋጋ ኃይል" በማሰማራት "ንቁ ሚና ለመጫወት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት "ለትራምፕ እና ለአውሮፓ አጋሮቻችን ፑቲን እየሸወዱን እንደሆነ ነግሬያቸዋለሁ" ያሉ ሲሆን፣ በሩሲያ ላይ "ተጨማሪ ጫና" እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ከፑቲን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው እንኳ በዩክሬን ሰላማዊ ዜጎችን መግደል እንዲያቆም ማድረግ እንደማይችሉ የተቀበሉ ይመስላል።

"ከእርሱ ጋር ያን ውይይት አድርጌያለሁ... ነገር ግን ስመለስ ሮኬት የአረጋውያን ማቆያን ወይም የአፓርትመንት ሕንጻ ሲመታ፣ ሰዎች በመንገድ ላይ ሲሞቱ አየሁ። ስለዚህ ለዚያ መልሱ ምናልባት አይሆንም ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።"