ፑቲን ትራምፕን ከማግኘታቸው በፊት ኪም ጆንግ ኡን "ወዳጄ ነው" አሉ

ፑቲን እና ኪም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን እና ኪም

ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ለመምከር ቀጠሮ የያዙት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሁንም ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር "ወዳጆች" መሆናቸውን ተናገሩ።

ፑቲን ከኪም ጋር "ወዳጅነታቸውን" ደግመው ያረጋገጡት ቢቢሲ የሰሜን ኮሪያ ዜጎች ባርነት መሰል በሆነ መንገድ ወደ ሩሲያ ተወስደው በግንባታ ሥራ ላይ እንደሚሰማሩ ዘገባ ባወጣበት ወቅት ነው።

ፑቲን እና ኪም ትናንት ማክሰኞ ሲነጋገሩ ፑቲን በዩክሬን ጦርነት የፒዮንግያንግ ወታደራዊ ድጋፍ ያለውን ቁልፍ ቦታ አንስተው ኪምን አመስግነዋል።

በያዝነው ሳምንት ሩሲያ በዩክሬን አዲስ ወታደራዊ ዘመቻዎች እያካሄደች ሲሆን፣ ወደ ምሥራቃዊ ዩክሬን ዶብሮፒሊያ ግዛት ዘልቃ መግባት ችላለች። በዘመቻው እስከ 10 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ግዛቱ የሩሲያ ወታደሮች ገብተዋል።

ክሬምሊን ያወጣው መግለጫ "ፑቲን እና ኪም ጓደኝነታቸውን፣ ጥሩ ጎረቤትነታቸውን እና ትብብራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ተወያይተዋል" ይላል።

ፑቲን በአላስካ ከትራምፕ ጋር ስለሚኖራቸው ውይይት ለኪም ማብራሪያ እንደሰጡ እና "ከትራምፕ ጋር የሚኖራቸውን ንግግር በተመለከተ መረጃ እንደተለዋወጡ" ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ያወጣችው መግለጫ ስለ ጉዳዩ የጠቀሰው ነገር የለም።

ከክሬምሊን የወጣው መግለጫ "የኩርስክ ግዛትን ነጻ በማውጣት ረገድ ሰሜን ኮሪያ ላደረገችው እገዛ ፑቲን ምስጋናቸውን አቅርበዋል" ሲል ያትታል።

አምና ባልተጠበቀ ጥቃት የዩክሬን ወታደሮች ለተወሰነ ጊዜ ወደ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት መዝለቅ ችለዋል።

ሩሲያ አሁን የዩክሬንን 20 በመቶ ግዛት የምትቆጣጠር ሲሆን፣ የዩክሬን የኩርስክ ግዛት ወረራ ምዕራባውያን አጋሮቿ ሩሲያን መቋቋም እንደሚችሉ ያሳየ ነው ተብሏል።

ፑቲን እና ትራምፕ በአላስካ በአካል ሲገናኙ እአአ ከ2022 ወዲህ የመጀመሪያቸው ይሆናል።

ትራምፕ የፊታችን አርብ ከፑቲን ጋር በሚያደርጉት ውይይት ለዩክሬን የተወሰነ ግዛት ለማስመለስ እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ሲባል ሩሲያ የዶንባስ ግዛታቸውን እንዲተው ብትጠይቅ ውድቅ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ሩሲያ ከምዕራባቸውን ጋር ያላት የምጣኔ ሃብት እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሻክሯል። በሌላ በኩል ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ እንዲቀራረቡ ምክንያት ሆኗል።

ዩክሬን እና ሰሜን ኮሪያ እንዳሉት ቢያንስ 10 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሩሲያ ሠራዊነት ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ መላካቸው ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ሚሳዔልና ሌሎችም የጦር መሣሪያዎችም አቅርባለች።

የሩሲያ ወታደሮች ከመገደላቸው፣ በውጊያ ከመወጠራቸው እና ከአገር በመሸሻቸው የተነሳ ሞስኮ ወደ ሰሜንኮሪያ ወታደሮች ፊቷን ማዞሯን የሰሜን ኮሪያ የደኅንነት ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።