ትራምፕ ከፑቲን ጋር በሚኖራቸው ንግግር የዩክሬንን ግዛቶች ለማስመለስ እንደሚሞክሩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሚያደርጉት ውይይት ለዩክሬን የተወሰነ ግዛት ለማስመለስ እንደሚሞክሩ ተናገሩ።
በዋይት ሐውስ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት "ሩሲያ የዩክሬንን ሰፊ ክፍል ይዛለች።ዋና ግዛት ነው የያዘችው።የተወሰነውን ግዛት ለዩክሬን ለማስመለስ እንሞክራለን" ብለዋል።
ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት በሳምንቱ መጨረሻ በአላስካ ተገናኝቶ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለውጥ ይኖር እንደሆነ ማወቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የአርብ ዕለቱ ስብሰባ ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆም ለማበረታታት ያለመ እና "አቋሙን ለማወቅ የሚደረግ ስብሰባ" እንደሚሆን ገልፀው፣ ይህንን ጉባዔ እንደ መነሻ እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
ትራምፕ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል "አንዳንድ የመሬት ልውውጦች" ሊኖሩ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ የትኛውን የዩክሬን ግዛት ልትወስድ እንደምትችል ባይታወቅም "የመሬት ልውውጥ" የሚለውን ሐረግ ሲጠቀሙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም።
ኪየቭ የትኛውንም የሩሲያ ግዛቶች ይገባኛል ብላ አታውቅም።
ትራምፕ ፑቲን በውይይቱ ወቅት "ፍትሃዊ ስምምነት" የሚያቀርቡ ከሆነ ለአውሮፓ መሪዎች እንደሚያሳውቁ ገልፀው፣ በመጀመሪያ ግን ለዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን "ለክብራቸው" ሲሉ እንደሚያነጋግሯቸው አስታውቀዋል።
"መጀመሪያ ለእርሱ እደውላለሁ... ከዚያ በኋላ እደውልለታለሁ፣ማለት የምችለው 'ብዙ ዕድል አለ፤ትግልህን ቀጥል' ወይም 'ስምምነት ላይ ልንደርስ እንችላለን' እላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ ዜሌንስኪ እና እኔ "ወዳጅ" ብንሆንም እንኳ "[የዩክሬን ፕሬዝዳንት] ባደረገው ነገር በጣም አልስማማም" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ትራምፕ እአአ በ2022 ሩሲያ አገራቸውን መውረሯን ተከትሎ ለተቀሰቀሰው ጦርነት ዜሌንስኪን ተወቃሽ አድርገዋቸው ነበር።
ወደፊት የሚካሄደው ስብሰባ ዜሌንስኪን ሊያካትት እንደሚችል እና ፑቲንን እና ራሳቸውን ጨምሮ የሦስትዮሽ ውይይት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካጃ ካላስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፑቲን ከትራምፕ ጋር ባደረጉት ውይይት "በቀደመው መንገድ መሄድ...የተፅዕኖ አካባቢዎችን እና ግዛቶችን እንከፋፍል" የሚለውን መርጠዋል ብለዋል።
ነገር ግን ዩክሬን ያልተስማማችበትን ስምምነት አውሮፓ እንደማትቀበል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
"ዩክሬን የስምምነቱ አካል ካልሆነች የትኛውም ስምምነት ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።ለዚህም ነው ዩክሬን በዚያ ጠረጴዛ ዙሪያ መገኘት ያለባት" ሲሉ ዜሌንስኪ በስብሰባው ላይ እንደሚጋበዙ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ክሬምሊን በተደጋጋሚ ከዜሌንስኪ ጋር የፊት ለፊት ውይይት ሊኖር እንደማይችል ተናግሯል።
በቅርቡ ፕሬዚዳንት ፑቲን ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ጊዜው ሩቅ ነው ብለው ነበር።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታደርግ አልያም ተጨማሪ የአሜሪካ ማዕቀቦች ሊጣልባት እንደሚችል ያስቀመጡት ቀነ ገደብ በሚያበቃበት ዕለት፣ ባለፈው ሳምንት አርብ ከፑቲን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል።
አላስካ የሚደረገው የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ ከተሰማ በኋላ ዜሌንስኪ የኪየቭ ግብዓት የሌለበት ማንኛውም ስምምነት "የከሸፈ ውሳኔ" ይሆናል ብለዋል።
ሰኞ ዕለት የዩክሬን የስለላ ቢሮ ያወጣውን መረጃ ጠቅሰው ሩሲያ በዩክሬን የምታካሄደውን ጦርነት ለማቆም ፍላጎት እንዳላት የሚያሳይ ምንም ዓይነት ምልክት የለም ብለዋል።
ዜሌንስኪ ረቡዕ ዕለት ከትራምፕ፣ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና ከአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ጋር በቪዲዮ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ ቃል አቀባይ ትራምፕ ከፑቲን ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የአውሮፓ መሪዎችን እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት እና የኔቶ መሪዎችን ሞስኮ ላይ እንዴት ጫና ማድረግ እንደሚቻል ለመነጋገር ስብሰባ ጠርተዋል ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር እና የካናዳ አቻቸው ማርክ ካርኒ ሰኞ ዕለት በስልክ ባደረጉት ውይይት የሰላም ስምምነቱ "ከዩክሬን ጋር በጋራ በመሆን መደረስ እንዳለበት፣ በአገሪቱ ላይ መጫን እንደሌለበት ተስማምተዋል" ሲሉ የዳውኒንግ ስትሪት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከትራምፕ እና ከዜሌንስኪ ጋር "በሚቀጥሉት ቀናትም ተቀራርበው መስራታቸውን ይቀጥላሉ" ሲሉም አክለዋል።















