ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ለተገደለው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ባለሥልጣን ልጅ ሽልማት አበረከቱ

የፎቶው ባለመብት, Michael Gloss / via Facebook
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ልጃቸው ለተገደለባቸው የአሜሪካ የስለላ ተቋም፣ሲአይኤ ምክትል ዳይሬክተር በዶናልድ ትራምፕ ልዑክ በኩል ሽልማት መላካቸው ተነገረ።
ፑቲን 'የሌኒን ሽልማት' የተሰኘውን የላቀ አበርክቶ ለሰጡ ግለሰቦች የሚበረከተውን ብሔራዊ ሽልማት በዚህ ሳምንት የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ለመምከር በሞስኮ ጉብኝት ላደረጉት ለስቲቭ ዊትኮፍ መስጠታቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ምንጮች ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በዩክሬን የተገደለው የ21 ዓመቱ ማይክል ግሎስ የሲአይኤ ምክትል ዳይሬክተር ጁሊያን ጋሊና ልጅ ነው።
የሽልማቱ ዜና የተሰማው የዩክሬን ጦርነት ዕጣ ፈንታን በተመለከተ በመጪው አርብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ፑቲን በአላስካ ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
በሶቪየት ዘመን የላቀ አገልግሎት ለሰጡ ግለሰቦች የሚበረከተውን 'የሌኒን ሽልማት' ለማይክል ግሎስ መሰጠቱን በተመለከተ ከክሬምሊንም ሆነ ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ግለሰቡ ሽልማቱን ለማግኘት ምን ሥራ እንደሰራ ግልፅ አይደለም።
ዋይት ሐውስ፣ ሲአይኤ እና ስቲቭ ዊትኮፍ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም።
የማይክል ግሎስ የሞት ዜና መጀመሪያ የተሰማው ባለፈው ሚያዚያ በሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዜናው ከተሰማ ከወር በኋላ ሲአይኤ በሰጠው መግለጫ ማይክል የአዕምሮ ጤና ሕመምተኛ እንደነበር እና ሞቱ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጿል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሲቢኤስ ማይክል የሲአይኤ ሠራተኛ እንዳልነበር ተናግረዋል።
ምንጮች አክለውም ክሬምሊን በ2023 ለሩሲያ ጦር ኃይል የዘመተው ማይክል፣ የማን ልጅ እንደነበር እውቅና እንዳልነበራቸው ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት ወጣቱ በሞስኮ 'ቀይ አደባባይ' የተነሳውን ምስል በማኅበራዊ የትስስር ገፆች አጋርቷል።
ማይክል"የዩክሬን የውክልና ጦርነት" እና መገናኛ ብዙኃን ለጦርነቱ የሰጡትን የዘገባ ሽፋን "የምዕራባዊያን ፕሮፓጋንዳ" በማለት ውድቅ በማድረግ ባጋራቸው ልጥፎች ከሩሲያውያን ድጋፍ አግኝቷል።
በኅዳር 2024 ከሞተ በኋላ የታተመው የሕይወትታሪኩ ኅዳር 4 "በምሥራቅ አውሮፓ ተገድሏል" ይላል።
ከአራት ወራት በፊት ሞቱን አስመልክቶ ሲአይኤ በሰጠው መግለጫ ምክትል ዳይሬክተሯ እና ቤተሰቧ "የማይታሰብ ቤተሰባዊ ሀዘን" ገጥሟቸዋል ብሏል።
የማይክል ወላጅ አባት ላሪ ግሎስ የኢራቅ ጦርነት አርበኛ ሲሆኑ ባለፈው ሚያዚያ ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገሩት ልጃቸው አብዛኛውን የሕይወቱን ዘመን ከአዕምሮ ጤና ጋር ታግሏል።
"ወደ አገሩ እንዲመለስ ስንጠብቅ ትልቁ ፍርሃታችን እዚያ [ሞስኮ] ያለ አንድ ሰው ነጥብ እና ነጥቦችን አገናኝቶ እናቱ ማን እንደሆነች ሊደርስበት ይችላል፤ እናም እንደ መሣሪያ ይጠቀመዋል የሚል ነበር" ሲሉ ላሪ ግሎስ ተናግረዋል።















