የተኩስ አቁም ቀነ ገደቡ እየተቃረበ ባለበት ወቅት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ከፑቲን ጋር ተገናኙ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ

የፎቶው ባለመብት, Sputnik/Gavriil Grigorov/Pool via REUTERS

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በክሬምሊን ተገናኝተው እየተወያዩ መሆኑን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ዊትኮፍ ሞስኮ የደረሱት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንድትደርስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ እየተቃረበ ባለበት ወቅት ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያካሄደች ያለውን "አሰቃቂ ጦርነት" ለማቆም እርምጃ ካልወሰደች ከባድ ማዕቀብ ሊጣልባት ወይም ከእርሷ ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ አገራት ላይ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ ገንዘብ ካላጣች በስተቀር ወደ ሰላም ለመምጣት እርምጃ እንደማትወስድ አስጠንቅቀዋል።

የሩሲያን ነዳጅ በሚገዙ አገራት ላይ አሜሪካ ጠንከር ያለ ማዕቀብ እና ታሪፍ ለመጣል መዛቷን በደስታ ተቀብለዋል።

በሩሲያ መገናኛ ብዙኃን አማካይንት የተጋሩ ምሥሎች መልዕክተኛው እና ፑቲን በክሬምሊን አዳራሽ ውስጥ ፈገግ ብለው ሲጨባበጡ ይታያል።

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተገናኝተዋል።

ምንም እንኳ አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል ደጋግማ ብትዝትም እንዲሁም ትራምፕ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ አርብ ዕለት የሚያበቃ ቢሆንም፣ ሩሲያ ግን በዩክሬን ከተሞች ላይ የምታካሄደውን መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣናቸውን በይፋ ከመረከባቸው በፊት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት በአንድ ቀን ማቆም እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ አሳካዋለሁ ያሉትን ከግብ ሳያደርሱ መቅረታቸውን ተከትሎ ትዕግስት እያጡ በመምጣታቸው ስለ ሩሲያ መረር እና ከረር ያሉ ንግግሮችን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ባለፈው ወር "[ጦርነቱ] ብዙ ጊዜ የተፈታ መስሎን ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ፕሬዝዳንት ፑቲን ወጥተው እንደ ኪየቭ ባሉ አንዳንድ ከተማዎች ሮኬቶችን ማስወንጨፍ ይጀምራሉ። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎችን በአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ የሚኖሩ ጭምር ተገድለዋል" ብለዋል።

ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች ሦስት ዓመት ተኩል የሆናት ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ በቱርክ ኢስታንቡል ሦስት ዙር የሰላም ድርድር ቢካሄድም ጦርነቱን ማስቆም አልተቻለም።

ሞስኮ የምታስቀምጣቸው ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች በኪየቭ እና በምዕራባውያን አጋሮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም።

ዜሌንስኪ ከፑቲን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለመወያየት ያቀረቡትንም ጥያቄ ክሬምሊን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር ማክሰኞ ዕለት ዜሌንስኪ እና ትራምፕ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ለዩክሬን የ200 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የወታደራዊ መሳሪያዎች ሽያጭ አጽድቋል።

ሁለቱ መሪዎች በተጨማሪ በመከላከያ ትብብር እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ላይ መምከራቸው ተሰምቷል።

ዩክሬን የሩሲያ የነዳጅ ማምረቻዎችን እና የኃይል ማመንጫዎችን ለመምታት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ስትጠቀም ሞስኮ ደግሞ የአየር ጥቃትዋን በዩክሬን ከተሞች ላይ አድርጋለች።

የኪየቭ ከተማ ወታደራዊ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ላይ በደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ከተገደለ በኋላ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 32 መድረሱን ተናግሯል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ጀምሮ በኪየቭ ላይ ከፍተኛው ጉዳት ያደረሰ የአየር ድብደባ ነበር ተብሏል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ሩሲያ በማዕከላዊ ዛፖሪዝሂያ በሚገኝ የመዝናኛ ካምፕ ላይ በፈፀመችው ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 12 ቆስለዋል።

ዜሌንስኪ የአየር ድብደባውን ተከትሎ "በዚህ ጥቃት ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ምክንያት የለም። ሰዎችን ማስፈራራት እና ጭካኔ ብቻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።