የፑቲን እና የትራምፕ ግንኙነት ለምን ንፋስ ገባው? ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል?

በዶናልድ ትራምፕ እና በቭላድሚር ፑቲን መካከል ያለው ግንኙነት ደፍርሷል?
አንድ ታዋቂ የሩሲያ ጋዜጣ እንደዚያ ያምናል። ጋዜጣው የአሁኑን የአሜሪካ ሩሲያ ግንኙነት ሁኔታ ለማሳየት ባቡርን ተጠቅሞ በምሳሌ ማስቀመጥ መርጧል።
ሞስኮቭስኪ ኮምሶሞሌትስ በቅርቡ "የፊት ለፊት ግጭት የማይቀር ይመስላል" ሲል ዘግቧል።
"የትራምፕ እና የፑቲን ፉርጎ አንዳቸው ወደ ሌላኛቸው በፍጥነት እየተምዘገዘጉ ነው።
"እና ሁለቱም ሞተሩን ለማጥፋት ወይም ለማቆም እና ለመቀልበስ ዝግጁ አይደሉም።"
የ'ፑቲን ፉርጎ'፣ 'ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ' እየተባለ በሚጠራው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ተጋግሎ ወደፊት እየገሰገሰ ነው።
የክሬምሊን መሪዎች ጦርነቶችን ለማስቆም እና የረጅም ጊዜ የተኩስ አቁም ለማወጅ ምንም ፍላጎት አላሳዩም።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ 'የትራምፕ ፉርጎ' ሞስኮ ጦርነቱን እንድታቆም ግፊት ለማድረግ ጥረቶችን በማፋጠን ላይ ይገኛል።
የትራምፕ አስተዳደር የጊዜ ገደቦችን በማስቀመጥ፣ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል በማስፈራራት እንዲሁም እንደ ሕንድ እና ቻይና ባሉ የሩሲያ የንግድ አጋሮች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣል ጫናውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በተጨማሪም ዶናልድ ትራምፕ ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸው ወደ ሩሲያ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ከባቡር ፉርጎ ወሬው ወደ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦች ሲቀየር ነገሮች ከባድ እንደሆኑ ይታወቃል።
ግን ያ ማለት ዋይት ሐውስ በዩክሬን ጉዳይ ከክሬምሊን ጋር "ወደ ግጭት ለመግባት" እያቆበቆበ ነው ማለት ነው?
ወይንስ በዚህ ሳምንት የዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በሞስኮ የሚያደርጉት ጉብኝት፣ በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ምልክት ነው?
ከትራምፕ መምጣት በኋላ የታየው መልካም ጅማሮ
በሁለተኛው የትራምፕ ሥልጣን ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሞስኮ እና ዋሽንግተን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እንደገና ለመጀመር ጥሩ ጅማሮ አሳይተዋል።
ቀጥታ ወደ ግጭት የሚያስገባ ምንም ፍንጭ አልታየም።
ከዚያ በራቀ ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ቭላድሚር ፑቲን እና ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ሰረገላ ውስጥ ሆነው ወደ አንድ አቅጣጫ የሚሄዱ ይመስሉ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት ወር ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግሥታት ከሩሲያ ጎን በመቆም በአውሮፓ የተረቀቀውን ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን "ጥቃት" የሚያወግዝ የውሳኔ ሃሳብ ተቃውማለች።
በዚያው ወር ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በስልክ ባደረጉት ውይይት ስለ ይፋዊ ጉብኝት ተነጋገሩ።
ይህም የፑቲን እና ትራምፕ ጉባዔ በማንኛውም ቀን ሊካሄድ እንደሚችል ፍንጭ ሰጠ።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር በሞስኮ ላይ ሳይሆን በኪዬቭ ላይ ጫና ማሳደር ጀመረ።
እንደ ካናዳ እና ዴንማርክ ካሉ የአሜሪካ የቆዩ አጋሮች ጋር በዚሁ ጉዳይ እሰጥ ገባ ውስጥ ገቡ።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሚያደርጓቸው ንግግሮች እና በሚሰጧቸው የቴሌቭዥን ቃለመጠይቆች ኔቶን እና የአውሮፓ መሪዎችን ክፉኛ ተቹ።
ይህ ሁሉ ለክሬምሊን ጆሮ ሙዚቃ ነበር።
በመጋቢት ወር ላይ በሩሲያ የሳይንስ አካዳሚ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ኮንስታንቲን ብሎኪን "ዋሽንግተን ከብራሰልስ ወይም ከኪዬቭ ጋር ካለው ወጥ አቋም ይልቅ፤ አሁን የበለጠ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ተመሳሳይ አቋም አላት" ብለው ነበር።
በሚቀጥለው ወር ይኸው ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘገበ።
"ትራምፖች አብዮተኞች ናቸው። የስርዓቱ ማርሽ ቀያሪዎች ናቸው። በዚህ ብቻ ሊደገፉ ይችላሉ። የምዕራቡ ዓለም አንድነት አሁን የለም፣ ጂኦ ፖለቲካዊ ግንኙነት አይደለም፣ ትራምፒዝም የትራንስ አትላንቲክን ስምምነት በእርግጠኝነት እና በፍጥነት አጥፍቷል።"

የፎቶው ባለመብት, EPA
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዶናልድ ትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የሩሲያ መደበኛ ጎብኚ ሆነዋል።
በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አራት ጊዜ ወደ ሩሲያ ያቀኑት ልዩ መልዕክተኛው ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ለሰዓታት ተናጋግረዋል።
ከአንድ ስብሰባ በኋላ የክሬምሊኑ መሪ ለዋይት ሐውስ የዶናልድ ትራምፕን ምስል በስጦታነት አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በስጦታው "በግልጽ ተደስተዋል" ተብሏል።
ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሞስኮ የሥዕል ስጦታ ብቻ አይፈለጉም። ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ውስጥ ያለ ቅድመ ሁኔታ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ ይፈልጋሉ።
እየጨመረ የመጣው የፕሬዚዳንት ትራምፕ ብስጭት
ሩሲያ አሁን በጦር ሜዳ ላይ ባላት የበላይነት በመተማመን ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኗን ቢናገሩም ውጊያውን ግን ለማቆም አልፈለጉም።
ለዚህም ነው ዶናልድ ትራምፕ በክሬምሊን ላይ በጣም የተበሳጩት።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ የፈፀመችውን የማያባራ ጥቃት "አስጸያፊ"፣ "አሳፋሪ" በማለት አውግዘው፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ "ብዙ የማይረባ ነገር" ያወራል ሲሉ ከስሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ወር ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን የሚያካሄዱትን ጦርነት እንዲያቆሙ የ50 ቀናት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ማዕቀቦችን እና ታሪፎችን ለመጣል አስፈራርተዋል።
ከዚያም የጊዜ ገደቡን ወደ አስር ቀናት ዝቅ አድርገውታል።
ትራምፕ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ያበቃል።
እስካሁን ድረስ ቭላድሚር ፑቲን ለዋሽንግተን ማስጠንቀቂያ እና ዛቻ እንደሚሸነፉ የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም።
አብሮ የሚነሳው ጥያቄ ቭላድሚር ፑቲን ምን ያህል ጫና ይሰማቸዋል? የሚለው ነው።
በኒውዮርክ ስኩል የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር የሆኑት ኒና ክሩሽቼቫ "ዶናልድ ትራምፕ ብዙ ቀነ ገደቦችን ስለቀያየሩ እና እርሱም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ስለተለዋወጠ፣ ፑቲን በቁም ነገር የሚመለከተው አይመስለኝም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፑቲን እስከቻለ ድረስ ይዋጋል፤ ወይም ዩክሬን 'ደክሞናል፣ የእርስዎን ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ፍቃደኞች ነን' ካላሉ በስተቀር።
"ፑቲን በክሬምሊን ተቀምጦ የሩስያ ንጉሠ ነገሥቶችን እና እንደ ጆሴፍ ስታሊን ያሉ መሪዎች ሕልምን ሩሲያ በንቀት መታየት እንደሌለባት ለምዕራቡ ዓለም በማሳየት እየፈፀምኩ ነው ብለው ያስባሉ።"
ስምምነት አሁንም ይቻላል
እስካሁን ድረስ በቀረበው መረጃ መሠረት የፑቲን እና የትራምፕ ተሽከርካሪዎች ፊት ለፊት መጋጨታቸው የማይቀር ሊመስል ይችላል።
ግን የግድ አይደለም።
ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸውን እንደ ታላቅ አስማሚ አድርገው ይመለከታሉ። ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ያላቸውንም ግንኙነት ለመጠበቅ መሞከራቸውን አላቋረጡም።
ስቲቭ ዊትኮፍ በዚህ ሳምንት ከክሬምሊን መሪ ጋር ለመነጋገር ወደ ሩሲያ ያመራሉ።
ምን አይነት ማግባቢያ ይዘው እነደሚሄዱ እስካሁን ድረስ አልታወቀም።
ነገር ግን በሞስኮ የሚገኙ አንዳንድ ተንታኞች ከኃይል እርምጃ ይልቅ የበለጠ የሚያቀራርብ ሃሰብ እንደሚኖር ይተነብያሉ።
እሁድ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሩሲያ "ማዕቀብን በማስወገድ ረገድ ጥሩ ትመስላለች" ማለታቸው ትኩረት የሳበ ንግግር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰኞ ዕለት በሞስኮ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢቫን ሎሽካሬቭ፣ ዊትኮፍ "ከዩክሬን ጋር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ተግባራዊ የሚሆኑ ጠቃሚ የትብብር ማዕቀፎች [ለሩሲያ]" ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ለኢዝቬሺያ ተናግረዋል።
ከሦስት ዓመት ተኩል ጦርነት በኋላ ክሬምሊንን ለማሳመን ይህ በቂ ሊሆን ይችላል?
ምንም ዋስትና የለም።
ለነገሩ እስካሁን ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ግዛቶች ላይ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት፣ የዩክሬን ገለልተኝነት እና የዩክሬን ጦር የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ካቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ስንዝር እንኳ አላፈገፈጉም።
ዶናልድ ትራምፕ ስምምነት ይፈልጋሉ። ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ ድል ።















