ፑቲን ለትራምፕ የማዕቀብ ማስፈራሪያ ፍንክች እንዳላሉ ተነገረ

ፕሬዚዳንት ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, SPUTNIK/KREMLIN POOL/EPA/Shutterstock

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ በመጪው ነሐሴ 2/ 2017 ዓ.ም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ካልደረሰች ማዕቀብ ይጣልባታል በሚል ቢያስፈራሩም፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን ወታደሮቻው በዩክሬን በተለያዩ የጦር ግንባሮች "የሚያደርጉትን ግስጋሴ እንደማይገቱ" አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳነት ቭላድሚር ፑቲን ከዪክሬን ጋር በቀጣይ በሚደረጉ የሰላም ንግግሮች ተስፋ እንዳላቸው ቢገልጹም ጦራቸው ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው።

ፑቲን "ሁሉም ቅር መሰኘቶች የሚመነጩት የተጋነኑ ነገሮች ሲጠበቁ" ነው ያሉት ፑቲን፤ በዚህም ትራምፕ ከዚህ ቀደም የሩሲያ አቻቸው ጦርነቱን ባለመቋጨታቸው "ቅር እንደተሰኙባቸው" ለሰጡት አስተያየት ምላሽ የሰጠ ነው።

አገራቸው በዩክሬኗ መዲና ኪየቭ ጥቃት በፈጸመች ማግስት አስተያየታቸውን የሰጡት ፑቲን በዚህም ንግግራቸው ዩክሬን ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ እንዲሁም አገራቸው በወረራ የተቆጣጠረቻው የዩክሬን ግዛቶች እውቅና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ዩክሬን ይህንን የፑቲን አስተያየት "እጅ እንደ መስጠት" አድርጋ ነው የምትመለከተው።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ከፑቲን ጋር "በማንኛውም ጊዜ" ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሩሲያ ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው የቫላም ገዳም ደሴት ላይ ሆነው አርብ ዕለት ንግግር ያደረጉት ፑቲን ከዩክሬን ጋር የሚደረገው ድርድር ይቀጥላል ብለው እንደሚጠብቁ እንዲሁም "ድርድርን በአዎንታዊ መልኩ" እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

ሆኖም የዩክሬን እንዲሁም ምዕራባውያን አጋሮቿ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እያደረጉት ያለውን ጫና በተመለከተ በደፈናው "በየትኛውም ሁኔታ ቅር መሰኘት ከየትኛውም ወገን የሚመጣው ከመጠን በላይ ነገሮችን ሲጠበቅ ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያው መሪ "ጠላቶቻችን እና መጥፎ የሚመኙልን አካላት አንድ ከፍተኛ ጉጉት አላቸው። በማንኛውም ወጪ በዩክሬን የምናደርገውን ግስጋሴ ማስቆም" ሲሉ አክለዋል።

ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ሩሲያ የዩክሬን ተጨማሪ ግዛቶችን ለመቆጣጠር በመሞከር፤ የሰላም ድርድሩን በማጓተት ማንኛውንም ትርጉም ያለው የተኩስ አቁምን ወድቅ አድርጋለች ሲሉ ይወቅሷታል።

ባለፉት ወራት በቱርክ መዲና ኢስታንቡል የተካሄደው ሶስት ዙር የሩስያ እና የዩክሬን ድርድር ፍሬ ሳያፈራ ተጠናቋል። ሆኖም ሁለቱ አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር ምርኮኞችን ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ከፑቲን አስተያየት በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተናገሩት ዜሌንስኪ ሩሲያ "ጦርነቱን በተገቢው ወቅት ለማቆም እና እና እውነተኛ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ዝግጁነት አላት? ወይ" ሲሉ ጥያቄ አቅርበው "ለጦርነቱ ተጨማሪ ጊዜ ለመግዛት እና ማዕቀቦችን ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ ብቻ ነው" ሲሉ ደምድመዋል።

ሩሲያ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) እና ሚሳኤሎች በመታገዝ በዩክሬን ላይ የምታደርገው ጥቃት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሐሙስ ዕለት ሩሲያ በኪዬቭ በፈጸመችው ጥቃት አምስት ህጻናትን ጨምሮ 31 ሰዎች ተገድለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩስያን ጥቃት በማውገዝ አዳዲስ ማዕቀቦች ይጠብቋታል ሲሉ አስፈራርተዋል።

ትራምፕ መጀመሪያ ላይ ፑቲን ጦርነቱን በ50 ቀናት ውሰጥ ካላቆሙ ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልካቸው ነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ያነጣጠረ ከባድ ታሪፍ እንደሚጥሉ ቢዝቱም ፑቲን ምላሽ አልሰጡም።

ትራምፕ ቀነ ገደባቸውን ቀንሰው 10-12 ቀናት ሲያደርጉትም የሩሲያው መሪ ምላሽ ዝምታ ነበር።

ነገር ግን ፑቲን አርብ ዕለት በሰጡት ምላሽ ለትራምፕ ማሰፈራሪያ ፍንክች እንደማይሉ የጠቆመ ነው።

በቫላም ደሴት እንግዳቸው የነበሩት የቤላሩስ መሪ አሌከሳንደር ሉካሼንኮ የትራምፕን ቀነ ገደብ ውድቅ ያደረገ አስተያየት ሰጥተዋል።

"አምሳ ቀናት፣ ስልሳ ቀናት፣ አስር ቀናት። በዚህ መንገድ አይደለም ፖለቲካ የሚሰራው" ሲሉ ሉካሼንኮ ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ ቀነ ገደቦችን የቀየሩት ትራምፕ አዲሱን ያስቀመጡት ነሐሴ 2 ሲሆን በዚያን ወቅት ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልፈረመች ማዕቀብ ይጣልባታል ብለዋል።

ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሩሲያ የመንግሥት ሚዲያዎችን ዘገባ በመገምገም አሜሪካ በሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ትጥላላች በሚለው ላይ የሩሲያ ባለስልጣናት ጥርጣሬ አላቸው።

ፑቲን አርብ ዕለት ሩሲያ በዩክሬን ጦር ግንባሮች ግስጋሴዋን እንደማትገታ መናገራቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ እንደማይደረስ የጠቆመ ነው።