የዩክሬን ባለሥልጣናት በወታደራዊ ድሮኖች ግዢ ወቅት በተፈጸመ ሙስና ተወንጅለው በቁጥጥር ስር ዋሉ

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን ፀረ ሙስና ተቋማት ከድሮን ግዢ ጨረታ ጋር በተያያዘ ትልቅ የሙስና ወንጀል መፈፀሙን ይፋ አድርገዋል

አንድ የዩክሬን የፓርላማ አባል እና ሌሎች ባለስልጣናት የአገሪቱ የፀረ ሙስና ኤጀንሲዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የኤሌክትሮኒክስ የጦር መሳሪያዎችን ግዢ ሂደት የነበረን መጠነ ሰፊ ሙስና ካጋለጡ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ አንድ የዩክሬን ፓርላማ አባል፣ የአውራጃ እና የከተማ አስተዳደሮች እና በርካታ የብሔራዊ ዘብ አገልግሎት አባላት በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው ተገኝተዋል። በዚህም የተነሳ መንግሥት ከአቅራቢዎች ጋር በገባው ውል ላይ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ተፈራርመዋል ሲሉ ጽፈዋል።

ዜለንስኪ በዩክሬን ውስጥ ለሙስና "ምንም ትዕግስት" ሊኖር እንደማይችል አስታውቀው፣ ኤጀንሲዎችን ለስራቸው አመስግነዋል።

የዩክሬን ፀረ ሙስና ኤጀንሲዎች ነጻነት ሐሙስ ዕለት በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ወደ ነበረበት ተመልሷል።

የዜሌንስኪ አስተዳደር የብሔራዊ ፀረ ሙስና ቢሮ እና ልዩ የፀረ ሙስና አቃቤ ሕግ ቢሮን ነፃነት የሚነፍግ ሕግን አርቅቆ ካቀረበ በኋላ ሰፊ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ፕሬዚዳንቱ ኤጀንሲዎቹ "ከሩሲያ ተጽዕኖ መፅዳት አለባቸው" በማለት ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ በከፍተኛ የሙስና ወንጀሎች ማን መከሰስ እንዳለበት የመወሰን ስልጣን ለመስጠት አቅደው ነበር።

ብዙዎች ይህንን የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ በዩክሬን ውስጥ የታየውን ሙስናን የመዋጋት ጥረት ወደ ኋላ የሚመለስ እርምጃ አድርገው ተመልክተውታል።

በዚህም የተነሳ ሩሲያ አገሪቱን ከወረረችበት እአአ ከ2022 ወዲህ ታይቶ አይታወቅም የተባለ ትልቅ የፀረ መንግሥት ሰልፍ ተካሄዷል።

ዜሌንስኪ የሕዝቡን ተቃውሞ በመቀበል ኤጀንሲዎቹ ወደ ቀድሞ ነፃነታቸው የሚመልስ አዲስ ሕግ አቅርበዋል።

ይህም የመጀመሪያው ሕግ ከፀደቀ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምጽ ተሰጥቶበታል።

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር የደህንነት ኃላፊ የሆኑት ኪሪሎ ቡዳኖቭ የፀረ ሙስና ኤጀንሲዎችን ሥልጣን በተመለከተ "የሕዝቡን ተቃውሞ በመስማታቸው" እና "ስህተት ባለመስራታቸው" ዜሌንስኪን አመስግነዋል።

የፕሬዚዳንቱ እርምጃ በመጀመርያው ረቂቅ ሕግ ላይ ያላቸውን ስጋት በገለፁ የአውሮፓ ኅብረት አገራትም ተሞካሽቷል።

ዩክሬን የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን ለምታደርገው ጥረት የፀረ ሙስና ትግሉ ጉልህ ሚና አለው።

የዩክሬን ሁለቱ የፀረ ሙስና ተቋማት በአውሮፓ ኅብረት እና በአይኤምኤፍ እአአ በ2014 የሰጡትን ምክረ ሃሳብ ተከትሎ የተቋቋሙ ናቸው።

ይህም በወቅቱ የቪዛ ገደቦችን ለማላላት እንደሚያግዝ የታመነበት ሲሆን፣ በ2022 ኪየቭ የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን በእጩነት ተቀባይነት እንድታገኝ አድርጓታል።

የፀረ ሙስና ተቋማቱ መመስረት እና የአውሮፓ ኅብረት ዕጩ አባል መሆኗ አገሪቱ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የበለጠ እንድትቀራረብ ያደረገ አንድ እርምጃ ነበር።

ሁለቱ የፀረ ሙስና ተቋማት ወደ ስራ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ባለሥልጣናት እና መስሪያ ቤቶች የተዘረፉ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገመት ሀብትና ንብረት ላይ ሰፊ ምርመራ አድርገዋል።

እአአ በ2023 ባደረጉት የጋራ ምርመራ የዩክሬን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኃላፊ ቭሴቮሎድ ክኒዚዬቭ ከ3 ሚሊዮን ዶላር ሙስና ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለዋል።