ትራምፕ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የሙስና ክስ ተቋርጦ 'ምህረት' እንዲደረግላቸው ጠየቁ

ዶናልድ ትራምፕ እና ቤንያሚን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሙስና የተከሰሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ክሳቸው ውድቅ ተደርጎ ምህረት እንዲደረግላቸው ለእስራኤል ጥሪ አቀረቡ።

ትራምፕ እስራኤል ከኢራን ጋር በነበራት ግጭት አገራቸው ጣልቃ በመግባት እንዳዳነቻት ገልጸው አሁን ደግሞ ኔታንያሁን "እናድናለን" ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጉቦ፣ በማጭበርበር እና እምነትን በመጣስ የተመሰረተባቸው ክስ የፍርድ ሂደት አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል።

ኔታንያሁ በበኩላቸው ትራምፕን "ለእኔ ላደረክልኝ ድጋፍ እንዲሁም ለእስራኤል ላደረግከው ታላቅ እገዛ አመሰግናለሁ" ሲሉ የምስጋና መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የእስራኤል ዋና ተቃዋሚ መሪ ያየር ላፒድ ትራምፕን በመተቸት "በነጻ ሃገር ህጋዊ ሂደት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለባቸውም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ይህንን ጥሪ ያቀረቡት 12 ቀናት ያስቆጠረውን የእስራኤል እና ኢራን ግጭት ተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ጥሳ ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ ቁጣ ከሰነዘሩ ከቀናት በኋላ ነው።

ኔታንያሁ፤ ትራምፕ የኢራንን የኒውክሌር ይዞታዎች በቦምብ ለመምታት ያሳለፉትን ውሳኔ "ቆራጥ እርምጃ" በሚል ቃል ነው ባለፈው እሁድ በተደጋጋሚ ያወደሱት።

ትራምፕ የረዥም ጊዜ አጋራቸውን ለእስራኤል ብዙ የሰሩ "ጀግና" እንዲሁም "ተዋጊ" በሚሉ ቃላት በማህበራዊ ሚዲያቸው አሞካሽተዋቸዋል።

ኔታንያሁ በመጪው ሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተረድቻለሁ ያሉት ትራምፕ የፍርድ ሂደቱ "በአስቸኳይ እንዲሰረዝ" ወይም ምህረት ሊደረግላቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍርድ ሂደታቸው ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ጊዜያት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የአሜሪካው መሪ በእስራኤል አቻቸው ላይ የቀረበውን ክስ "ሆን ተብሎ የሚፈጸም ማሳደድ" በሚል ፈርጀው "እንዲህ አይነት የፍትህ መዛባት ሊፈቀድ አይገባም" ብለዋል።

ትራምፕ "ከኔ ጋር በስምምነት መስራት የሚችል ከሱ የተሻለ ማንም የማውቀም ሰው የለም" ብለዋል ለአቻቸው ኔታንያሁ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በምላሹ "የጋራ ጠላቶቻችንን ለማሸነፍ፣ ታጋቾችን ነጻ ለማውጣት እንዲሁም ሰላም በቀጣናው ለማስፈን በጋራ መስራታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ሆኖም ተቃዋሚው ያይር ላፒድ ትራምፕ እየሞከሩት ያሉት ጣልቃ ገብነት የተሰላ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

"ኔታንያሁ የታጋቾች ስምምነት ላይ እንዲደርስ ጫና በማድረግ የጋዛን ጦርነት ለመቋጨት እና በምላሹ ትራምፕ ይህንን ሽልማት ሊሰጡት ነው" ሲሉ ያይር ላፒድ ይኔት ለተሰኘው የእስራኤል ድረ ገጽ ተናግረዋል።

የኔታንያሁ የፍርድ ሂደት የጋዛ ጦርነት ከተጀመረም በኋላ ቢቀጥልም መዘግየቶች መከሰታቸው አልቀረም።

ኔታንያሁ በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲራዘም የሚፈልጉት ምርጫው እንዲዘገይ እና የፍርድ ሂደቱንም ከመጠናቀቅ ለማደናቀፍ እንደሆነ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።