ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ ፈተና ሆኖባቸው ፊታቸውን ወደ መጠጥ ያዞሩት የሩሲያ ወታደሮች

የሩሲያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ጦርነት እንደሚሰበከው ቀላል አይደለም።

የሰው ልጅ ሊመልሰው የማይችለው የሕይወት መቀጠፍ፣ የሰብዓዊነት መሰለብ፣ የንብረት መውደም፣ የሰላማዊ ሰዎች ሰቆቃ. . . ሌላም ሌላም ጠባሳ ይጥላል።

ገፈት ቀማሹ ተሸናፊዎቹ ብቻ አይደሉም አሸናፊዎችም ቢሆኑ ከሰቆቃዎች ጋር ሊኖሩ ግድ ይላቸዋል።

በጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ወታደሮች ጠላትም የሚሉት ቢሆን የሰውን ልጅ ሕይወት መቅጠፍን ከህሊናቸው ጋር እንዴት ያለማምዱታል የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

ለዚያም ነው በርካታ ወታደሮች ከጦር ግንባር ተመልሰው ሕይወታቸውን መምራት ፈታኝ የሚሆንባቸው።

ያዩትን ሰቆቃ ዝም ብለው መርሳት ስለማይሆንላቸው ራሳቸውን የሚያጠፉም አይታጡም።

"አብዛኞቹ ወታደሮች የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን ማየት አይፈልጉም" ትላለች ታትያና [ስሟ የተቀየረ] የተባለች በሩሲያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የተቋቋመው 'ፋሚሊ ኸርት ፕሮጀክት' በጎ ፈቃደኛ የሥነ ልቦና ባለሙያ።

የሚመጡ ወታደሮችም በጦር ግንባር ላይ ውላ ስለማታውቅ ያለፉበትን ልትረዳ እንደማትችል ወይም ያዩዋቸውን ነገሮች ልትቋቋማቸው እንደማትችል ያስባሉ ትላለች።

ታትያና ወታደሮቹ ያለፉባቸውን ሁኔታዎችን ለመቋቋም ከጓደኞቻቸው ጋር መጠጣት እንደሚመርጡ ታዝባለች።

የአእምሮ ጤና እክል ገጥሟቸው ከዩክሬን የጦር ግንባር የሚመለሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮች እንደሚሆኑ ይገመታል።

ወታደሮች በአብዛኛው የሚገጥማቸው ፒቲኤስዲ (ድኅረ ሰቆቃ የጭንቀት ቀውስ) ነው።

ከሦስት ዓመት ተኩል በላይ እየተካሄደ ባለው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ፣ ሩሲያ ከጦር ግንባር ለተመለሱ ወታደሮች የሥነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠት ውጤታማ ሥርዓት አለመዘርጋቷን የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ታቲያና እንደምትለው ወታደሮች ወደ ቀደመ የሲቪል ሕይወታቸው መመለስን ቀላል ሆኖ አያገኙትም።

"ባልደረባዬ አንድ ታካሚ ነበረው ካፌ ውስጥ ገብቶ እዚያ ያሉ ደንበኞች ዘና ብለው በመቀመጣቸው ተበሳጭቶ የሚደባደብ" ትላለች፤ አክላም "አሁን ጥሩ፣ ደግ ሰው ነኝ፤ በጦር ግንባር ደግሞ ሰዎችን እገድል ነበር የሚለውን ማስታረቅ ይከብዳቸዋል" ስትል ታስረዳለች።

ወታደሮቹን ሥነ ሥርዓት ለማስያዝ በሚል ያለ ምግብና ውሃ ለቀናት ጉድጓድ ውስጥ እንዲቀመጡ ያደረገ አንድ የጦር አዛዥን ታማክር ነበር።

ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ግን ምን ያህል ጸጸት ውስጥ እንደገባ ታወሳለች።

ታትያና እንደምታስረዳው ባለፈው አንድ ዓመት ስምንት ወታደሮች ብቻ ናቸው ለሥነ ልቦና ድጋፍ ወደ እሷ ዘንድ የመጡት። ሆኖም ብዙዎቹ ተስፋ ቆርጠው አልኮልን አማራጭ አድርገዋል ትላለች።

የሩሲያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ላይ ምን ያህል ወታደሮችን እንዳሰማራች እስካሁን ይፋ አላደረገችም። ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን 617 ሺህ ወታደሮች በዩክሬን ጦር ግንባር ተሰማርተው እንዳሉ ገልጸዋል። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ተጨማሪ 490 ሺህ ወታደሮች ተሰማርተዋል።

እንደ የሩሲያ ቤክቴሬቭ የሥነ አእምሮ ማዕከል ከሆነ በጦር ግንባር ከተሰማሩ ወታደሮች ከ3 አስከ 11 በመቶው በፒቲኤስዲ እንደሚሰቃዩ ያስረዳል።

በተለይም ወታደሮች በግንባር ከተጎዱ የአእምሮ ጤና እክል ችግር የማጋጠም ዕድሉ ከ14 አስከ 17 በመቶ እንደሚጨምር ከማዕከሉ የተገኘው መረጃው ያሳያል።

ሩሲያ ጦርነቱን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር የወታደሮችን የአእምሮ ጤና ለመደገፍ ወደ 2,700 የሚጠጉ የሥነ ልቦና የሕክምና ማዕከላትን አቋቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት የሚደገፍ ፕሮግራም ከአንዳንድ የበጎ ፈቃደኛ ድርጅቶች ጋር በመጣመር ድጋፍ ይሰጣል።

ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ጥረቶች በቂ እንዳልሆኑ እንዲሁም እነዚህ የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚሰጡ ማዕከላት በጣም አነስተኛ ወይም በቂ የሰው ሃይል እንደሌላቸው ከእነዚህ ማዕከላት በአንዱ የምትሠራው ያና [ስሟ ተቀይሯል] የተባለች የሥነ ልቦና ባለሙያ ታስረዳለች።

ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችውን ወረራ የምትቃወመው ያና መጀመሪያ ላይ በዚህ ጦርነት ከተሳተፉ ወታደሮች ጋር መሥራት ፈታኝ ነው ብላ ታምን ነበር።

ሆኖም የእሷ ድጋፍ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ስለተሰማት የማማከሩን ሥራ ጀመረች።

"እነዚህ አደገኛ ሰዎች ናቸው እናም ይህንን አደጋቸውን ለመቀነስ ነው የምሠራው ትላላች" ያና ከቢቢሲ ሩሲያ ጋር ባደረገችው ቆይታ።

ከዚህም በተጨማሪ ሩሲያ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ብላ የምትጠራውን ይህንን ጦርነት መተቸት ሕገ ወጥ በመሆኑ ሌላ ፈተና ሆኖባታል ባለሙያዋ። ታካሚውም ሆነ ባለሙያዋ አብዛኛውን ጊዜ በግልጽ ለመናገር እንደሚፈሩም ታስረዳለች።

"አመለካከትህን ለማይጋራ ሰው ከተናገርክ ሊወጣ ይችላል። አንድ ሰው ይህንን ሪፖርት ሊያደርግ ይችላል። ይህም ሕይወትህን ያበላሸዋል" ትላለች።

የሩሲያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ስምሪት

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ያሰማራቻቸው ወታደሮችን ብቻ አይደለም።

የእስር ቅጣታቸው እንዲቀንስ በሚል የተፈረደባቸው ወንጀለኞች በጦር ግንባሮች ተሰማርተዋል።

በርካታዎቹ የተመለመሉት ሕይወቱ ባለፈው የቭጌኒ ፕሪጎዢን በተመሠረተው በሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር ነው።

እስረኞች ለስድስት ወራት በጦር ግንባር ሲያሳልፉ ለዚህ አገልግሎታቸው በምላሹ የቅጣት ማቅለያ ወይም ይቅርታ እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል።

የቀድሞው የቫግነር መሪ 50 ሺህ እስረኞች መመዝገባቸውን ገልጾ ነበር።

ቫግነር ያደርገው የነበረው ምልመላ በአውሮፓውያኑ 2004 ሲቀንስ፣ ይህንንም ሚና የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ተረክቧል።

ሚኒስቴሩ ከተረከበ በኋላ ሁኔታዎች የተቀየሩ ሲሆን፣ ፈቃደኛ የሆኑ እስረኞች ጦርነቱ እስኪያልቅ ድረስ ማገልገል አለባቸው ተብሏል።

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የተሰማሩ ወታደሮች ከግንባር መውጣት የሚችሉት ከባድ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው፣ በዕድሜ ወይም አዲስ የወንጀል ፍርደኛ ከሆኑ ነው የሚል የወሰነችው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።

ይህም በእስረኞቹም ስምሪት ላይ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።

ወንጀል የሚፈጽሙ እና የሚፈረድባቸው ወታደሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ቨርስትካ የተሰኘው ሚዲያ ባደረገው ምርመራ ከአውሮፓውያኑ 2022 እስከ 2024 ባለው ጊዜ 242 ሰዎች ከጦር ግንባር በተመለሱ ወታደሮች ሲገደሉ፣ 227 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ወታደሮቹ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃቶችን እንዲሁም የከፉ ድብደባዎችን መፈጸማቸውን ይኸው ዘገባ አስፍሯል።

ከጥቂት ወራት በፊት የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አካል የሆነው የኡራል የሕግ ተቋም "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ በሩሲያ ወንጀሎች ላይ ያስከተለው ተጽእኖ" በሚል አንድ ጥናት አውጥቷል።

ጥናቱ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ከበድ ባሉ ወንጀሎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አግኝቷል።

በአንድ የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኞች ማከሚያ ማዕከል ውስጥ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆነው ማትቪ [ስሙ ተቀይሯል] እሱ እና ባልደረቦቹ ከጦር ግንባሮች በተመለሱ ወታደሮች ከፒቲኤስዲ ጋር የተያያዘ የአልኮል ሱሰኝነት እንደሚጨምር ጠብቀው ነበር።

በቤክቴሬቭ ማዕከል ክሊኒካዊ መመሪያዎች መሠረት እንደ ውጊያ ላሉ አሰቃቂ ሁኔታዎች የተጋለጡ ሰዎች ለአደንዛዥ ዕጽ እና ተያያዥ ሱሶች የመጋለጥ ሁኔታቸው ከፍተኛ ነው።

በሩሲያ ዋነኛው የሥነ አእምሮ ሆስፒታል ሰርብስኪ ማዕከል ባለፈው ዓመት ከነበሩ የሱስ ታካሚዎች መካከል 10 በመቶው ወታደሮች መሆናቸው ታይቷል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ለሰቆቃ በተጋለጡ እና በሱስ መያዝ መካከል ግንኙኑት ቢኖረውም በሩሲያ ውጤታማ የሕክምና አማራጮች አሁንም እምብዛም አይደሉም።

ማትቬይ እንደሚናገረው ታካሚዎች በተቋሙ ውስጥ ከሁለት ሳምንት ላልበለጠ ጊዜ እንደሚቆዩ አብራርቶ ይህም ከውጤታማ ሕክምና ይልቅ በማስታገሻ ላይ ያተኮረ ነው ይላል።

ቢያንስ 12 ክፍለ ጊዜዎችን የሚጠይቁ እንደ የግንዛቤ (ኮግኒቲቭ) ያሉ የሕክምና ዘዴዎች በበይነ መረብ አማካይነት ማግኘት አይቻልም ይላል።

"ለአብዛኞቹ ወታደሮች ሕክምናው በጣም የሚያም ነው ወይም የማይጨበጥ የሆነ ስሜት ይሰማቸዋል። ታካሚዎቻችን የሆነ ችግር እንዳለባቸው ሊረዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ችግሩ በጣም አስከፊ፣ አሰቃቂ እና ሕመም ስለሚፈጥርባቸው መንካት አይፈልጉም" ይላል።

አክሎም "የፒቲኤስዲ ሕክምና አስገዳጅ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ" ይላል።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ዓመት ከጦር ግንባር የተመለሱ ወታደሮች የሥነ ልቦና ሕክምና ግዴታ ሊሆን እንደሚችል ሃሳቡን ቢያንሸራሽሩም እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ እስካሁን አልተጀመረም።

የፖለቲካ ፍላጎቱ ቢኖርም አገሪቱ ብቃት ያላቸው ልዩ ባለሙያዎች እጥረት ገጥሟታል።

በሩሲያ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች አሃዝ ግምቶች የተለያዩ ሲሆኑ፣ በዚህም 57 ሺህ ወይም ከ100 ሺህ በላይ የሚገምቱ አሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አራት እስከ 5 የሚሆኑ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ለ100 ሺህ ዜጎች አገልግሎት ይሰጣሉ ይላል። ይህ መጠን ከዓለም አቀፉ ደረጃ አንጻር በጣም ዝቅ ያለ ነው።

እንደእነዚህ ዓይነት መሰናክሎች ቢያጋጥሙም አንዳንድ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በሚችሉት አቅም በርካቶችን እየረዱ እንደሆነ ይናገራሉ።