ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ለተኩስ አቁም ስምምነት ሲባል የዶንባስ ግዛታቸውን እንደማይተው አስታወቁ

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ሲባል ሩሲያ የምታቀርበውን የዶንባስ ግዛታቸውን እንዲተው የሚጠይቅ ማንኛውንም ሃሳብ ውድቅ እንደሚያደርጉ ገለጹ።

የተወሰነውን የዶንባስ ግዛት ተቆጣጥረው የሚገኙት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ይህ ሁኔታ ለወደፊቱ ለሚፈጸሙ ወረራዎች እንደ መንደርደሪያ ሊያገለግል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ዘለንሰኪ ይህንን የተናገሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በመጪው አርብ በአላስካ ከሚያደርጉት ስብሰባ በፊት ነው።

ትራምፕ የትኛውም የሰላም ስምምነት "አንዳንድ ግዛቶችን መለዋወጥን ያካትታል" ያሉ ሲሆን ይህም የፑቲን ጥያቄ ዩክሬን ተቆጣጥራው የምትገኘውን የተወሰነውን የዶንባስ ግዛት አካል እንድትሰጥ ነው ተብሎ ይታመናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ወታደሮች በምስራቅ ዶብሮፒሊያ ከተማ አቅራቢያ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም በአጭር ጊዜ ውስጥ 10 ኪሎሜትር ዘልቀው መግባት ችለዋል።

ዘለንስኪ የሩሲያ ወታደሮች እያደረጉት ያሉትን ግስጋሴ በበርካታ ግንባሮች መሆኑን አምነው ነገር ግን ጦራቸው በቅርቡ ይመክተዋል ብለዋል።

የሩሲያን ግስጋሴ በማሳነስ አላማው ፑቲን ከትራምፕ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት "ሩሲያ ወደፊት እየገሰገሰች ፤ ዩክሬን እየተሸነፈች ነው" የሚል የመረጃ ክፍተት "መፍጠር እንደሆነ "ለኛ ግልጽ ነው" ሲሉ ዘለንኪ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ሁለቱ መሪዎች በሚያደርጉት ውይይት የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ምን ሊጠይቁ እንደሚችሉ ምንም አይነት ይፋዊ መረጃ የለም።

ሩሲያ ከሞላ ጎደል መላውን የሉሃንስክ እና 70 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክ ከተማ ተቆጣጥራ የምትገኝ ሲሆን ነገር ግን ዘለንስኪ ማክሰኞ ዕለት ዶንባስን በሙሉ ለመተው የቀረበውን ማንኛውም ሃሳብ እንደማይቀበሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

"ዛሬ ከዶንባስ ምሽጎቻችን፣ ከመሬታችን፣ ከምንቆጣጠራቸው ከፍታዎች ለቀን ብንወጣ ለሩሲያ ጥቃት ዋነኛ በር መክፈት ነው" ብለዋል።

ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም ሲልም ዩክሬናውያን "መሬታቸውን ለወራሪ እንደማይሰጡ" አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ የተሰማ ሲሆን አገሪቱ የግዛት ለውጥ ከማደረጓ በፊት በህገ መንግሥቷ መሰረት ህዝበ ውሳኔ አስገዳጅ ነው ብለዋል።

ዘለንስኪ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግራቸውም ሩሲያ በሶስት ግንባሮች በዛፖሪዝሂዝሂያ ፣ ፖክሮቭስክ እና ኖፖፓቭሎቭ አዳዲስ ጥቃቶች ለመክፈት በዝግጅት መሆኗንም አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት ትራምፕ ለሩሲያ እና ዩክሬን "መሻሻል ሲባል አንዳንድ ግዛቶች ልውውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል" ይህም ሁኔታ በኪዬቭ እና በመላው አውሮፓ ሩሲያ የዩክሬንን ድንበሮች በኃይል እንድትከልል ይፈቅድላታል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ሩሲያ በአሁኑ ወቅት ከ20 በመቶ በታች የዩክሬንን ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች።