ትራምፕ ከፑቲን ጋር ባይስማሙም በውይይታቸው 'ለውጥ እንደታየ' ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአላስካ ባደረጉት ውይይት ከስምምነት ላይ ባይደርሱም "ለውጥ መታየቱን" ገለጹ።
"ስምምነት ላይ እስከሚደረስ ድረስ ስምምነት የለም። እዚያ ላይ አልደረስንም" ብለዋል።
ለሦስት ሰዓታት ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። ከጋዜጠኞች ጥያቄ ግን አልተቀበሉም።
ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለመግታት "በጣም እንደሚፈልጉ" ከመግለጽ ባለፈ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
በውይይቱ ያልተጋበዙት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ "ስምምነት እንዲፈርሙ" ትራምፕ ጠይቀዋል።
ትራምፕ ሰላም በማስፈን ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ማሳየት ቢፈልጉም በአላስካው ውይይት ግን እምብዛም ስምምነት ላይ አለመደረሱ ተገልጿል።
ትራምፕና ፑቲን ሁለት ጊዜ የተጨባበጡ ሲሆን ሞቅ ያለ ሰላምታ ሲለዋወጡም ታይተዋል። በትራምፕ ሊሞዚን ወደ ውይይቱ ሥፍራ በጋራ ሲሄዱም ተስተውሏል።
ዩክሬን ግዛቶቿ በሩሲያ እንዲወሰድ የሚያደርግ ስምምነት ላይ በውይይቱ አለመደረሱ በኪየቭ ደስታን ያጫረ ይመስላል።
ትራምፕ በባለቤታቸው ሜላንያ ትራምፕ በእጅ የተጻፈ ደብዳቤ ለፑቲን ሰጥተዋል።
ስሎቬንያ የተወለዱት ቀዳማዊት እመቤቷ በአላስካው ውይይት አልተገኙም።
ደብዳቤው በጦርነቱ ወቅት ልጆች እየታፈኑ መሆኑን እንደሚጠቅስ ተገልጿል።
የዩክሬን መግንሥት የታገቱ ልጆች ቁጥር 19,500 መሆኑን አስታውቋል።
የታገቱ ሕጻናት ሳይመለሱ የሰላም ስምምነት መፈራረም ተገቢ እንደማይሆን በዩክሬን በኩል ይታመናል።
እአአ በ2023 ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሕጻናትን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር ክስ ፑቲን እና የሕጻናቶች መብቶች ኮሚሽነራቸው ማሪያ ልቮቫ-ቤሎቫ ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።
በአላስካ ትራምፕና ፑቲን ሲወያዩ የሩሲያ ድሮን በዩክሬን ጥቃት መፈጸሙን ቀጥሏል።
የሩሲያን ግስጋሴ ለመግታት ዩክሬን ወደ ምሥራቃዊ ግዛት ወታደሮች አሰማርታለች።
ዘለንስኪ እንደሚሉት ፑቲን ሰላም ለማውረድ ቁርጠኛ መሆናቸውን የሚጠቁም ማስረጃ የለም።
ፑቲን ከዘለንስኪ ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ አይደሉም። የዩክሬን ትክክለኛ መሪ ዘለንስኪ ናቸው ብለውም አያምኑም።
ዘለንስኪ ፑቲንን እንደማያምኗቸውና "ተስፋቸው አሜሪካ እንደሆነች" ተናግረዋል።
ትራምፕ በአላስካው ውይይት ሩሲያ የተኩስ አቁም እንድታደርግ ጫና ማሳደር ነበር ግባቸው። ሆኖም ግን ፑቲን በዚህ አልተስማሙም።
ትራምፕ ለፑቲን ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው በታላቅ አክብሮት ነው የተቀበሏቸው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሩሲያ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ይዝቱ ነበር። ሆኖም ግን የተኩስ አቁም ጥያቄያቸው ከፑቲን አወንታዊ ምላሽ አላኘም።
የሩሲያ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የሁለቱ መሪዎች ውይይት "እጅግ አመርቂ" ነበር ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ውይይት "በጋራ ወደፊት ለመጓዝ" የሚረዳቸው ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ስላደረጉት ውይይት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የጦር እስረኞች ልውውጥ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።
"50 50 ዕድል ነው ያለው። ማንኛውም ነገር ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም ፑቲን ችግሩን መፍታት እንደሚፈልግ አምናለሁ" ብለዋል።
"በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ዝርዝር ሰጥተውኛል። እናስፈታቸዋለን" ሲሉም ትራምፕ አክለዋል።
እነዚህ እስረኞች በሩሲያ አልያም በዩክሬን ወገን ያሉት ስለመሆናቸው ፕሬዝዳንቱ አልገለጹም።
የዩክሬን ጦርነት ግዛቶችን በማስረከብ የሚገባደድ ይሆናል? በሚል የተጠየቁት ትራምፕ በአብዛኞቹ የውይይት ነጥቦች ከፑቲን ጋር መስማማታቸውን ጠቅሰው "በጣም ጥሩ ውይይት ነው። ወደ ስምምነት እየተቃረብን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም ግን ዘለንስኪ ስምምነት መፈረም እንዳለበት ትራምፕ ገልጸዋል። "እምቢ ሊሉ ይችላሉ። ግን ዘለንስኪ ስምምነት መፈረም አለበት" ብለዋል።
ከአውሮፓውያን ደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን ዘለንስኪ ስምምነት እንዲፈርሙ ትራምፕ አሳስበዋል።
በቀጣይ ፑቲን እና ዘለንስኪ የሚገኙበት ውይይት እንደሚካሄድ ትራምፕ ተናግረዋል።
የቀድሞው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) የአሜሪካ አምባሳደር ዳግላስ ሉት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በአላስካው ውይይት ትራምፕ "ምንም ያገኙት ነገር የለም"።
"ፑቲን ከዓለም አቀፍ መድረክ ተገልለው ነበር። አሁን ግን ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸው ከትራምፕ ጋር በውይይቱ ተገኝተዋል። ትራምፕ ግን ከውይይቱ ያገኙት አንዳችም ነገር የለም" ብለዋል።















