አሜሪካ አላስካን ከሩሲያ ለመግዛት የወሰነችው ውሳኔ "የብልሆች ወይስ የቂሎች" ግብይት?

የፎቶው ባለመብት, Hulton Archive/Getty Images
ነገ አርብ ነሐሴ 9 2017 ዓ.ም. የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው አቻቸው በአሜሪካዋ አላስካ ግዛት ተገናኝተው በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በሁለቱ መሪዎች መካከል በአላስካ ለማካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ስብሰባ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የታየ ጉልህ ዲፕሎማሲያዊ እድገት ነው ሊባል ይችላል።
ስብሰባው ብቻ ሳይሆን የስብሰባው ቦታም ታሪካዊ ጠቀሜታ አለው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን የሚገናኙት በአሜሪካዋ ግዛት በአላስካ ትልቋ ከተማ አንኮሬጅ ነው።
ነገር ግን ስብሰባው የተካሄደው ከ150 ዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መገናኛ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ይሆን ነበር።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አሁን በአሜሪካ ውስጥ ትልቋ ግዛት የሆነችው እና ከጠቅላላው የአገሪቱ የመሬት ስፋት አንድ አምስተኛውን የምትሸፍነው ይህች ግዛት፣ በአንድ ወቅት የሩሲያ የነበረች መሆኑ ነው።
"ምክንያታዊ ለሆነ ስብሰባ ምክንያታዊ ቦታ"
በሰሜን አሜሪካ በሰሜን ምዕራብ ራቅ ያለ ቦታ ላይ የምትገኘው አላስካ ከሩሲያ በቤሪንግ ሰርጥ ተለያይታለች።
ይህም በጠባቡ የሰርጡ ክፍል ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ይርቃል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጉባኤው በአላስካ እንደሚካሄድ ባስታወቁበት ወቅት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ረዳት የሆኑት ዩሪ ኡሻኮቭ ለሩሲያ ልዑካን "በቤሪንግ ሰርጥ ላይ በመብረር በአላስካ ለሚያካሄዱት አስፈላጊ እና የሚጠበቅ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ስብሰባ"፤ "በጣም ምክንያታዊ ቦታ ይመስላል" ብለዋል።
ነገር ግን በሩሲያ እና በአላስካ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በ1700 ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተጀመረ ሲሆን በሳይቤሪያ የሚገኙ ነባር ሕዝቦች መጀመሪያ በምሥራቅ በሚገኘው ሰፊ መሬት ላይ ይኖሩ እንደነበር ይነገራል።
የዴንማርኩ መርከበኛ ቪተስ ቤሪንግ የተመራ አንድ የአሳሽ ቡድን ይህ መሬት ከሩሲያ ጋር ያልተገናኘ መሆኑን ደረሰበት።
ነገር ግን በወቅቱ አካባቢው በከባድ ጭጋግ ተሸፍኖ የነበረ በመሆኑ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም።
እአአ በ1741 እንደገና በቤሪንግ የተመራ ሌላ የአሳሾች ቡድን ወደ ስፍራው አቅንቶ የተሳካ ጉዞ አድርገ።
ከዚያ በኋላ ባህርተኞች ወደ ስፍራው አምርተው በርካታ የንግድ ጉዞዎች አድርገዋል።
ይህም ከሩሲያ የባህር ኦተር ፀጉርን በማምጣት በአውሮፓ፣ በእስያ እና በሰሜን አሜሪካ የፓስፊክ የባህር ዳርቻ መካከል ትርፋማ የሆነ የፀጉር ንግድ እንዲኖር በር ከፈተ።
ይሁን እንጂ በ19 ኛው ክፍለ ዘመን የብሪታኒያ እና የአሜሪካ ፀጉር ነጋዴዎች ለሩሲያውያን ብርቱ ተፎካካሪዎች ሆኑ።
የከረረው የንግድ ፉክክር እአአ በ1824 እልባት አግኝቶ ሩሲያ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከብሪታንያ ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራረመች።
የባህር ኦተሮች ለመጥፋት መቃረባቸው እና የክሬሚያ ጦርነት (1853-56) ፖለቲካዊ ውጤቶች ሩሲያ አላስካን ለአሜሪካ ለመሸጥ ፈቃደኛ እንድትሆን ካደረጓት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
"የጅል ግብይት"
በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዊልያም ሴዋርድ የመሬት ግዥ ድርድርን በመምራት ከሩሲያውያን ጋር ስምምነት አደረጉ።
ከብዙ ተቃውሞ በኋላ የአሜሪካ ኮንግረስ የሴዋርድን የ7.2 ሚሊዮን ዶላር ግብይት አጽድቆ እአአ በጥቅምት 18 ቀን 1867 የአሜሪካ ባንዲራ በወቅቱ የአላስካ ዋና ከተማ በነበረችው በሲትካ ተሰቀለ።
መጀመሪያ ላይ የአላስካ ግዢ መሬቱ ምንም ነገር የለውም ብለው በሚያምኑ ተቺዎች "የሴዋርድ ቂላቂል ግብይት" እያሉ ይጠሩት ነበር።
የዋጋ ግሽበት ከግምት ገብቶ አሜሪካ የከፈለችው 7.2 ሚሊዮን ዶላር በዛሬ ገበያ ቢሰላ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል።
በሚያስደንቅ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ ትልቁ ግዛት ለሆነችው አላስካ ዝቅተኛ ዋጋ ነው የተከፈለው።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ አላስካ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኙት ወርቅ፣ ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ እንዳሉባት ታወቀ።
የሴዋርድ እርምጃ አዋጪ ሆኖ የተገኘ ሲሆን በ1959 አላስካ የአሜሪካ 49ኛ ግዛት ሆነች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተፈጥሮ ሀብቷ የበለፀገችው አላስካ ዛሬ ከ12,000 በላይ ወንዞች እና በርካታ ሐይቆች አሏት።
ዋና ከተማዋ ጁኑዋ፣ በጀልባ ወይም በአውሮፕላን ብቻ የሚደረስባት ብቸኛዋ የአሜሪካ ዋና ከተማ ነች።
በአንኮሬጅ ውስጥ የሚገኘው ሁድ ሐይቅ በቀን ወደ 200 የሚጠጉ በረራዎችን የሚያስተናግድ በዓለም ላይ በጣም የተጨናነቀ የባህር አውሮፕላን ማረፊያ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ፑቲን በግዛቲቱ በሚገኘው ትልቁ ወታደራዊ ተቋም በኤልመንዶርፍ-ሪቻርድሰን የጦር ሰፈር ይገናኛሉ።
አሜሪካ በአርክቲክ ላላት ወታደራዊ ፍላጎት አገልግሎት የሚሰጥ 64,000 ሔክታር መሬት ያለው ቁልፍ ቦታ ነው።
አላስካ በአሜሪካ ዲፕሎማሲ ውስጥ ቁልፍ ሚና ስትጫወት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021፣ የጆ ባይደን አዲስ የዲፕሎማቲክ እና የብሔራዊ ደህንነት ቡድን ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር በአንኮሬጅ ተገናኝተዋል።
ስለ ጉባኤው ምንም ዓይነት ይፋዊ መረጃ ባይወጣም ዋይት ሐውስ ግን የአላስካው ስብሰባ ለትራምፕ "የመስማት ዕድል" የሚሰጥ እንደሚሆን እና ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት "ይህን ጦርነት እንዴት ማቆም እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ" እንደሚሆን ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የመሪዎች ጉባኤውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ትራምፕ ስብሰባው ወደ ሰላም የሚያመሩ ተጨባጭ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል ተናግረው ነበር።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቀደም ሲል ኪየቭ ያልተሳተፈችባቸው ስምምነቶች "የከሸፉ ውሳኔዎች" ይሆናሉ ብለዋል።















