በሩሲያ ጥቃት 17 ሰዎች ሲገደሉ፣ የአውሮፓ ኅብረት ጽህፈት ቤት ተመታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአውሮፓ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ከሐምሌ ወር ጀምሮ ሩሲያ በኪዬቭ ላይ በፈጸመቻቸው ከባድ ጥቃቶች እና በዩክሬን ዋና ከተማ በሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ጽህፈት ቤት ላይ ጉዳት በመድረሱ ቁጣቸውን ገለፁ።
በሩሲያ የአየር ድብደባ አራት ሕጻናትን ጨምሮ 17 ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት ባለ አምስት ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ወድሟል፣ የአውሮፓ ኅብረት ተልዕኮ እና በአቅራቢያው የሚገኘው የብሪቲሽ ካውንስል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ቮን ደር ሌየን ጠንከር ባለ ቃል በሰጡት መግለጫ ላይ የሩሲያ ሚሳዔሎች ከዲፕሎማቲክ ልዑኩ ጽህፈት ቤት በቅርብ ርቀት ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል።
"ሁለት ሚሳዔሎች ከልዑካን ቡድኑ 50 ሜትር ርቀት ላይ በ20 ሰከንድ ልዩነት ወድቀዋል።"
ጦርነቱን ለማስቆም በአሜሪካ መሪነት የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ ረቡዕ ሌሊት የተፈፀመው ጥቃት ዩናይት ኪንግደምን እና የአውሮፓ ኅብረትን አስቆጥቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የሩሲያውን ቭላድሚር ፑቲንን "የሰላም ተስፋዎችን እያጨለሙ ነው" ሲሉ የወነጅሉ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ በበኩላቸው "በሰላም ጥረቶች ላይ ለማሳለቅ ሆን ተብሎ የተደረገ" ብለዋል።
ሞስኮ "ከድርድር ጠረጴዛው ይልቅ የባሌስቲክ ሚሳዔሎችን መርጣለች" ያሉት ደግሞ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሲሆኑ፣ በሩሲያ ላይ "አዲስ እና ጠንካራ ማዕቀብ" እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሩሲያ አሁንም ለድርድር "ፍላጎት እንዳላት" ብትገልጽም ቮን ደር ሌየን በበኩላቸው ጥቃቱ "ሌላ አሳፋሪ ማሰጠንቀቂያ ነው" በማለት ሩሲያ "ዩክሬንን ማሸበር እንደማታቆም" ተናገረው ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ከመግደሏ አልፎ የአውሮፓ ኅብረትን ዒላማ አድርጋለች ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ቃል አቀባይ ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ተቋም ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደሌለበት እና ለጥቃቱ ምላሽ በብራሰልስ የሚገኘው የሩሲያ ኃላፊ ተጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቋል ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደምም በተመሳሳይ በለንደን የሩሲያ አምባሳደር አንድሬ ኬሊን ወደ ውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት እንደሚጠሩ ገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, EU
የዩክሬን ጦር ሩሲያ ወደ 600 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ከ30 በላይ የባላስቲክ እና ክሩዝ ሚሳዔሎችን መተኮሷን ተናግሯል።
ይህም በዚህ ወር በዋና ከተማዋ ላይ ከደረሱት ጥቃቶች ሁሉ ትልቁ ነው ተብሏል።
በኪዬቭ ከተገደሉት መካከል ብዙዎቹ በደቡብ ምሥራቅ ዳርኒትስኪ አውራጃ ባለ አምስት ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ነበሩ።
ጠዋት የነፍስ አድን ሠራተኞች ፍርስራሹን ያነሱ ሲሆን፣ በሕይወት የተርፉ ሰዎችን ፍለጋው ቀጥሏል።
ጥቃቱ በደረሰበት የሕንፃው ክፍል ውስጥ ብቻ 10 ሰዎች ይኖሩ የነበረ ሲሆን፣ ባለሥልጣናቱ እስካሁን ሊደርሱላቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ከተገደሉት ልጆች መካከል ሦስቱ ሁለት፣ 14 እና 17 ዓመት የሆናቸው ናቸው። ሌሎች በርካታ ወጣቶች ደግሞ ቆስለዋል።
ሩሲያ በተከታታይ ሚሳዔሎችን ያስወነጨፈችው የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን ረቡዕ ዕለት በኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከ100,000 በላይ ዩክሬናውያን ያለ መብራት ካስቀረ በኋላ ነው።
ሌሎች 60,000 ነዋሪዎች ደግሞ በማዕከላዊ ቪኒትሲያ ክልል ውስጥ ረቡዕ ሌሊት በተፈጸሙ ጥቃቶች የሚያገኙት የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጡን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዜሌንስኪ በዩክሬን ከተሞች እና ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት ለሳምንታት እና ለወራት በርካቶች ሲጠይቁ ለነበረው "የተኩስ ማቆም እና እውነተኛ ዲፕሎማሲ" ክሬምሊን የሰጠችው ግልጽ ምላሽ ነው ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ የሩሲያ ጥቃቶች "አስደንጋጭ ነበሩ" ብለዋል።
የብሪቲሽ ካውንስል ከሌሎች አገራት ጋር የባህል ግንኙነትን የሚያጎለብት እና ከአውሮፓ ኅብረት ተልዕኮ ጋር በተመሳሳይ ስፍራ የሚገኝ ሲሆን ጽህፈት ቤቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት እና ላልተወሰነ ጊዜ ለጎብኚዎች ዝግ እንደሚሆን ተናግሯል።
ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን የአውሮፓ ኅብረት 19ኛውን የማዕቀብ ፓኬጅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልፀው በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከሩሲያ እና ከአጋሯ ቤላሩስ ጋር ድንበር የሚጋሩ ሰባት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል።
አርብ ወደ ኢስቶኒያ፣ ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ሊቱዌኒያ እና ሮማኒያ ከማምራታቸው በፊት ወደ ላቲቪያ እና ፊንላንድ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ዜሌንስኪ እና የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲንን ያሳተፈ ጉባኤ ለማዘጋጀት ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም ጥረታቸው እስካሁን አልተሳካም።
በመጀመሪያ ከፑቲን ጋር በአላስካ፣ በመቀጠል ደግሞ በዋሽንግተን ከዜሌንስኪ እና ከአውሮፓ መሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ሩሲያ በተደጋጋሚ የዩክሬን ከተሞች ላይ የኤር ድብዳ ብትፈጽምም የአሜሪካ ባለሥልጣናት አርብ ዐዕለት በኒውዮርክ ከዩክሬን ልዑካን ጋር ይወያያሉ።















