የፑሽኪን እና የጎጎል መጽሐፍት ከአውሮፓ ታላላቅ ቤተ መጽሐፍት ተሰርቀው የሚወሰዱት ወዴት ነው?

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 2022 ሁለት ሰዎች በኢስቶኒያ ወደሚገኘው ታርቱ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጽሐፍት ገብተው በሁለት የ19 ኛው ክፍለ ዘመን ደራሲዎች የተጻፉ ስምንት መጽሐፎችን ለማንበብ ጠየቁ።
እነዚህ መጽሐፍቶች የሩሲያ ገጣሚ እና ፀሐፌ ተውኔት አሌክሳንደር ፑሽኪን እና የሥመጥሩ ደራሲ ኒኮላይ ጎጎል ናቸው።
ሁለቱ ሰዎች ራሽያኛ ይናገሩ የነበረ ሲሆን ታናሽ ወንድማቸው በአሜሪካ ትምህርቱን ለመቀጠል የተለያዩ ነገሮችን እየተመለከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከሦስት ወራት በኋላ የቤተ መጻሕፍቱ ሠራተኞቹ ሁለቱ መጽሐፍቶች በሐሰተኛ መጽሐፍት እንደተተኩ አስተዋሉ።
የቤተ መጻሕፍት መዛግብት እነዚህ የጠፉ መጽሐፍት ለመጨረሻ ጊዜ የተወሰዱት በእነዚሁ ሰዎች በሚያዝያ ወር መሆኑን ያሳያሉ።
የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎቹ የቀሩትን ስድስት የሩሲያ ዘመን አይሽሬ መጽሐፍት ለማየት ሄዱ።
በተደረገው ምርመራ መረዳት የተቻለው መጽሐፍቶቹ ተመሳስለው በተዘጋጁ ሌሎች ቅጂዎች ተተክተዋል።
መጽሐፍቱ እውነተኛ እንዲመስሉ የቤተ መጻሕፍቱ ማህተም እና ቁጥሮች አርፎባቸዋል።
በዘራፊዎች ዒላማ የተደረገው የታርቱ ቤተ መጽሐፍት ብቻ አይደለም።
ከሳምንታት በኋላ በኢስቶኒያ ዋና ከተማ ከሚገኘው የታሊን ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት አሥር የማይገኙ መጻሕፍት ጠፍተዋል።
ከ18 ወራት በላይ፣ በርካታ የሩሲያ ዘመን አይሽሬ እና ሌሎች በሩሲያኛ የተጻፉ ጥንታዊ ጽሑፎች ከ12 የአውሮፓ ቤተ መጻሕፍት፣ ከባልቲክስ፣ ፊንላንድ፣ ስዊዘርላንድ እና ፈረንሳይ ተሰርቀዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች ዋና መጽሐፍቶቹ በቅጂዎች ሲተኩ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ መጽሐፍቱ ከቤተ መጽሐፍት በውሰት ተወስደው አልተመለሱም።
በምላሹ ዩሮፖል የአውሮፓ ኅብረት የሕግ ማስከበር ትብብር ኤጀንሲ "ዘመቻ ፑሽኪን" የተባለ ምርመራ ጀምሯል።
ይህ ከ100 በላይ ፖሊሶች በተለያዩ አገራት የሚገኙ በርካታ ንብረቶች ላይ ፍተሻ እንዲያደርጉ አስገድዷል።
በአጠቃላይ እስካሁን ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ክትትል ተደርጎባቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ሁሉም ተጠርጣሪዎች የጆርጂያ ዜጎች ናቸው።

'አስማተኛው' ባለ መጽሐፍ
እነዚህን ታሪካዊ እና ብርቅዬ መጽሐፍት በመስረቅ ወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረው የመጀመሪያው ግለሰብ የ48 ዓመቱ ቤቃ ስሬኪዜ ነው። ግለሰቡ በተመሳሳይ ጊዜ ላትቪያ እና ኢስቶኒያ ውስጥ ከታርቱ እና ታሊን ቤተመፃሕፍት ስርቆት ጋር በተያያዘ በሦስት ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበት ተፈርዶበታል።
ስሬኪዜ በአሁኑ ጊዜ ኢስቶኒያ ውስጥ የተፈረደበትን የሦስት ዓመት ከሦስት ወር እስራት እየተቀበለ ይገኛል።
ስሬኪዜ ማረሚያ ቤት ሆኖ ለቢቢሲ እንደተናገረው በ2008 ቤተሰቡን ለመመገብ ጥንታዊ መጽሐፍትን በመሰብሰብ እና በመሸጥ ለመሳተፍ ወሰነ።
መጻሕፍቱን በመሰብሰብ ረገድ ስላለው መደበኛ ትምህርት ሲጠየቅ ሁሉንም በተግባር መማሩን ይናገራል።
"እኔ መጽሐፍ እንዳለው አስማተኛ ነኝ። በእጄ የገባ መጽሐፍ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እና በጨረታ ላይ ምን ያህል እንደሚያወጣ ወዲያውኑ መናገር እችላለሁ" ብሏል።
ስሬኪዜ ከሕግ ጋር መጀመሪያ የተላተመው እአአ በ 2016 ጆርጂያ ውስጥ ከተብሊሲ የታሪክ ሙዚየም ጥንታዊ መጽሐፎችን ሰርቆ በተከሰሰበት ጊዜ ነው።
በወቅቱ ጥፋተኛነቱን ያመነ ሲሆን በገደብ ቅጣት ተጥሎበት ቆይቷል።
"ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የታየ ትልቁ ዘረፋ"
እአአ በጥቅምት 2023 ሁለት ወጣቶች ጥቁር ኮፍያ ያደረገ ወንድ እና ቀይ ፀጉር ያላት ሴት፣ በዋርሳው ዩኒቨርስቲ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ቁጭ ብለው እያነበቡ ነበር።
የአሮጌ መጽሐፍቱን ገጾች እያገላበጡ እያለ ወንዱ አብራው ያለችውን ሴት ጉንጭ አጥብቆ ሳመ።
ይህ ሁሉ የታየው በቤተ መጽሐፍቱ ውስጥ በተተከለ የደህንነት ካሜራ ነው።
ወጣቱ ልጅ የስሬኪዜ ልጅ ሜት ሲሆን ሴቷ ደግሞ የሜት ባለቤት አና ጎጎላድዜ ነች።
ሁለቱም በኋላ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ከቤተ መጻሕፍቱ 100,000 ዶላር የሚያወጣ መጽሐፍ በመስረቅ ወንጀል ተከስሰዋል።
ዩኒቨርስቲው በቅድመ እና ድህረ ሶቪየት መጽሐፍት የደለበ ክምችት የሚገኝበት ነው።
በዚህ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ እአአ በ1944 በነበረው ሕዝባዊ አመጽ ሕንጻው እና በርካታ ንብረቶች ሲቃጠሉ የተረፉ መጽሐፍት ይገኙበታል።
ፕሮፌሰር ሔሮኒም ግራላ "የሆነ ትውልድ እነዚህን መጽሐፍት ለእኛ እንዳተረፈልን የምንረዳ ትውልዶች ነን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜው ውስጥ እንደልብ የማይገኙ እና 600 ሺህ ዶላር እንደሚያወጡ የተገመቱ 73 ውድ መጽሐፍት ከቤተ መጻሕፍቱ ተሰርቀዋል።
አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቀበኞች እስካሁን ድረስ አልተያዙም።
ፕሮፌሰር ግራላ የወንጀሎቹን መጠን ለመገናኛ ብዙኃን ሲያስረዱ "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ ዝርፊያ ነው" ብለዋል።
"ከዘውድ ላይ ጌጣጌጦቹን ሰብሮ እንደመውሰድ ነው" ሲሉ የወንጀሉን ግዝፈት ለማሳየት ሞክረዋል።

የቤተ መጻሕፍቱ ሠራተኞች እንደዚህ ዓይነት በሐሰተኛ ቅጂዎች የተተኩ መጽሐፍትን ወዲያው አላስተዋሉም።
"ኮድ አለ፤ ተመሳሳይ መጠን ያለው መጽሐፍ አለ፤ በመደርደሪያው ላይ ምንም ክፍተት የለም" ብለዋል ፕሮፌሰር ግራላ።
ፕሮፌሰር ግራላ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በመጀመሪያው ላይ የመጣው የሌቦች ቡድን (የተለዩ መጽሐፍት ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ) እና በደንብ ተዘጋጅተው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ማጭበርበሮችን ፈጽመዋል" ብለዋል።
በዚህ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የተተገበሩት የቅርብ ጊዜ ማሻሻያዎች ለስርቆቶች ቁጥር መጨመር ሚና ተጫውተው ሊሆን ይችላል ብለዋል ፕሮፌሰር ግራላ።
በተለይም ውድ እና የማይገኙ አሮጌ መጽሐፍትን በሚጠቀሙ አንባቢዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር መላላቱ አስተዋጽኦ ሳያደርግ አልቀረም።
ይህ አሰራር የተዘረጋው ለአንባቢዎች የበለጠ ተደራሽ ለመሆን በሚል ዓላማ ነበር።
"አንዲት ትንሽ ማህተም'
በተለምዶ ሁሉም ቤተ መጻሕፍት መጻህፍቱ ላይ ማህተማቸውን ያሳርፋሉ። መጠናቸው እንደ አገሩ እና እንደ ቤተመጻሕፍቱ ይለያያል።
የማይገኙ መጽሐፍትን በመሰብሰብ የሚታወቁት ፒዮትር ድሩዝህኒን ሩሲያውያን "ደመቅ ያሉ ማህተሞችን" በማድረግ እንደሚታወቁ ይናገራሉ።
ባለሙያው እነዚህን ማህተሞች ዓይቶ ብቻ መጽሐፍቱ የተሰረቁ መሆናቸውን መለየት ይቻላል ባይ ናቸው።
ይህ ግን ሁሌም ይሆናል ማለት አይደለም። ቤተ መጽሐፍቱ በሶቪየት ዘመን እንደሆነው ቦታ ሲጠባቸው ካሏቸው ተመሳሳይ መጽሐፍት የተወሰነውን ቀንሰው ይሸጣሉ።
ወይም ቤተ መጽሐፍቱ ሊበተኑ እና ሊዘጉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በፔሬስትሮይካ ዘመን የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ሲዘጉ አጋጥሟል።
እንደ ድሩዝህኒን ከሆነ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን እና ከዚያም ቀደም ብሎ ያሉትን ደግሞ ማህተሞቻቸውን በመመልከት ብቻ መነሻቸው ከየት ነው የሚለውን መለየት አስቸጋሪ ነው።
"ማህተሞቹ የ18ኛው ወይም የ19ኛው ክፍለ ዘመን ከሆነ መጽሐፉ ምን እንደገጠመው አናውቅም። እውነት ነው መጽሐፉ ከቤተመጽሐፍቱ ነው የወጣው፤ ነገር ግን እንዴት እንደወጣ ማንም ሊያውቅ አይቸልም።"
ማህተሞቹ ኬሚካልን በመጠቀም ሊወገዱ ወይም ያረጁ ገጾች በአዲስ ሊተኩ ይችላል። እንደዚህ ዓይነት መረጃን የማጥፋት እርምጃ ሊጋለጡ የሚችሉት በባለሙያዎች ወይም የጠፉ መጽፍትን በሚያሰባስቡ ግለሰቦች ብቻ ነው።
አሮጌ መጽሐፍት ማህተም ላይኖራቸው የሚችለው አልፎ አልፎ ብቻ ነው። ምክንያቱ ደግሞ መጽሐፍቱ ላይ ማህተም መደረግ ከመጀመሩ በፊት ወደ መጽሐፍ ሰብሳቢዎች እጅ ገብተው ሊሆን ስለሚችል ነው።
በሺህዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች
ኢስቶኒያ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኘው ስሬኪዜ "60,000 ዶላር የሚያወጣ፣ ግማሽ ኪሎ ወርቅ በ22 የታጠቁ ፖሊሶች ይጠበቃል። 60,000 ዶላር የሚያወጡ ሁለት መጽሐፍት አውሮፓ ውስጥ በሚገኝ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፤ እናም አንዲት በዕድሜ በገፋች ሴት ይጠበቃሉ። ብዙ ጊዜ ደግሞ የደህንነት ካሜራ ክትትል እንኳን የለም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ስለዚህ ባልተለመደ መልኩ ለ19 ኛው ክፍለ ዘመን የሩሲያ ዘመን አይሽሬ መጽሐፍት ከፍተኛ ዋጋ ለማውጣታቸው እና ለስርቆቱ እየጨመረ መምጣት ምክንያቱ ምንድን ነው?
ድሩዝሂኒን ብርቅዬ የሩሲያ መጽሐፍት ላይ ስርቆት የተጧጧፈው እአአ በ2022 እና 2024 መካከል የአውሮፓ የወንጀል ማዕበል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት ነው ይላሉ።
ባለሙያዎች "ይህ የሚሸጠው ከግል ስብስብ እየወጣ እንዳልሆነ" ሊያውቁት ይገባ ነበር ብለዋል።
ድሩዝሂኒን የውድ መጽሐፍት ገዢዎች አነስተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ምናልባትም ሲገዙ እንደ የአገር ፍቅር ስሜት ተመልክተውት ሊሆን ይችላል ይላሉ።
"አሁን እነዚህ ጠቃሚ መጽሐፍት ወደ አገራቸው የተመለሱበት ወቅት ነው" ብለዋል።
በሰኔ ወር በሊትዌና ከሚገኘው የቪልኒየስ ዩኒቨርስቲ ቤተ መጻሕፍት ውድ መጽሐፍትን በመስረቅ እና በመሸጥ የተከሰሰውን ሌላውን የጆርጂያ ዜጋ ሚካሂል ዛምታራድዜን የተጭበረበሩ ሰነዶችን ተጠቅሞ የቤተመጻሕፍት አባል በመሆን 17 የማይገኙ መጻሕፍትን ወስዷል።
አብዛኛዎቹ ማህተሞች ነበሯቸው። ከዚያም 12 መጽሐፍትን በሌሎች ቅጂዎች ተክቷል፤ አምስቱን ደግሞ ከቤተ መጽሐፍት አውጥቶ አልመለሳቸውም።
የተሰረቁት መጽሐፍት አጠቃላይ ዋጋ ወደ 700,000 ዶላር ይገመታል።
ዛምታራዴዝ መጽሐፍቱን ከሞስኮ ትዕዛዝ ከተቀበለ በኋላ መስረቁን እና ወደ ቤላሩስ በአውቶብስ እንደላካቸው ገልፆ 30,000 ዶላር በክሪፕቶከረንሲ እንደተከፈለው ተናግሯል።
ከሞስኮ ሌሎች የመጽሐፉ ቅጂዎች እና ሐሰተኛ ሰነዶች እንደተላከለት የሚናገረው ዛምታራዴዝ፣ ደንበኛው በሞስኮ የጨረታ ማዕከል ውስጥ ከፍተኛ አባል የሆኑ ግለሰብ መሆናቸውንም ገልጿል።

የጨረታ ማዕከሎቹ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ስማቸው ሲነሳ ይህ የመጀመርያው አይደለም።
ከዋርሶ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት የተወሰዱ ቢያንስ አራት የተለያዩ መጻሕፍት ሊትፈንድ በተባለው የጨረታ ማዕከል ውስጥ በሞስኮ በ2022 መጨረሻ እና በ2023 ተሽጠዋል ሲሉ ፕሮፌሰር ግራላ ተናግረዋል።
ቢቢሲ፤ ፕሮፌሰር ግራላ ከጨረታ ማዕከሉ ድረ ገጽ የወሰዷቸውን ስክሪንሾቶችን ተመልክቷል።
በምስሉ ላይ ከዩኒቨርስቲው ቤተ መጻሕፍት እንደተሰረቁ የተገለፁት መጽሐፍት ይታያሉ።
ከመጻሕፍቱ አንዱ የፑሽኪን 'ዘ ቴልስ ኦፍ ኢቫን ቤኪን' ሲሆን በ19ኛው ክፍለ ዘመን የታተመ ማህተም በመጽሐፉ ፎቶዎች ላይ በግልጽ ይታያል።
ሌላው በዚሁ ጨረታ ላይ የቀረበው ባለ አራት ጥራዝ የፑሽኪን ግጥሞች ስብስብ ነበር።
አሁን በተዘጋው የጨረታ ማዕከሉ ድረ ገጽ ላይ ባሉ ምስሎች የዋርሶ ዩኒቨርሲቲ ማህተምም ይታያል።
የሊትፈንድ ዳይሬክተር ሰርጌይ በርሚስትሮቭ እንዳሉት ጨረታው የሚሠራው በሩሲያ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፤ እናም ማህተም ያረፈባቸውን መጽሐፍት ለሽያጭ አይቀበልም።
በርሚስትሮቭ አክለውም የመጽሐፉ ባለቤቶች ለጨረታ ተቀባይነት ያለው የትኛውንም መጽሐፍት ሕጋዊ አመጣጥ ለማረጋገጥ ከጨረታ ማዕከሉ ጋር ውል ይፈራረማሉ።
እያንዳንዱ መጽሐፍ ከጨረታው ማዕከሉ በመጡ ባለሞያዎች በቅርበት ምርመራ ይደረግበታል። በዚህም በስራ ላይ ካሉ ቤተ መጻሕፍት ጋር የተገናኙ ምንም ማኅተሞች ወይም ሌሎች ምልክቶች አለመኖራቸውን ያረጋግጣሉ።
የቆዩ ማህተሞች ሁልጊዜ ጥርጣሬን አያጭሩም።
በርሚስትሮቭ፤ "ከአብዮቱ በኋላ በነበሩት ዓመታት እጅግ በጣም ብዙ ከሩስያ ቤተ መጻሕፍት የወጡ መጽሐፍት በመላው ዓለም ተሰራጭተው በብዙ የመንግሥት እና የግለሰቦች ስብስብ ውስጥ ተካትተዋል። ስለዚህ በግለሰቦች እጅ ያሉ እንደዚህ ያሉ መጽሐፍት በዓለም ገበያ ላይ ተሰራጭተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ግራላ የድሮ ማህተሞች ጉዳይ ውስብስብ መሆኑን ያስረዳሉ።
"የዋርሶ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ታሪካዊ ማህተም ካለ እና የታሪካዊው ኮድ ተጠብቆ ከተቀመጠ፣ ይህ በራሱ እንደ ቅርስ ይቆጠራል። [ማንም ሰው] አዲስ ማህተም ወይም አዲስ ኮድ በላያቸው ላይ ማሳረፍ አይችልም። እነዚህ ማህተሞች ለ200 ዓመታት ያህል ኖረዋል፤ ከአክብሮት የተነሳ እንደገና አይታተሙም" በማለትም አብራርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ "ዘመቻ ፑሽኪን" ገና አልተጠናቀቀም። ቢያንስ አንድ ተጠርጣሪ እዚያ ከሚገኙ ቤተ መጻሕፍት መጽሐፍትን በመስረቁ በፈረንሳይ ፍርድ በመጠባበቅ ላይ ነው።
ባለሥልጣናቱም ብዙ ወንጀለኞች አሁንም አለመያዛቸውን እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ ውድ መጽሐፍት አለመገኘታቸውን ያምናሉ።















