ከ80 ዓመት በፊት በናዚዎች የተሰረቀ ስዕል በሪል ስቴት ማስታወቂያ ላይ ተገኘ

የተሰረቀው ስዕል ቤት ውስጥ ከሶፋ በላይ ተንጠልጥሎ

የፎቶው ባለመብት, Robles Casas & Campos

ናዚዎች በአምስተርዳም ከሚገኝ አይሁዳዊ የሥነ ጥበብ ነጋዴ ሰርቀውት የነበረ አንድ ታዋቂ የጣሊያን ስዕል፤ ከተወሰደ ከ80 ዓመታት በኋላ አርጀንቲና ውስጥ ቤት በሚያሻሽጥ የሪል ስቴት ወኪል ድረ ገጽ ላይ ተገኘ።

በወኪሉ ድረ ገጽ ላይ የተለጠፈ አንድ ፎቶግራፍ፤ በጁሴፔ ጊስላንዲ የተሳለ የአንዲት ሴትን የሚያሳይ የሥነ ጥበብ ስራ በቦነስ አይረስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ቤት ውስጥ ከሶፋ በላይ ተንጠልጥሎ አሳይቷል።

ቤቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ደቡብ አሜሪካ የተዛወረ ከፍተኛ የናዚ ባለሥልጣን ንብረት የነበረ ነው።

በጦርነቱ ወቅት የጠፉ የሥነ ጥበብ ውጤቶች በተሰበሰቡበት የመረጃ ቋት ውስጥ የተካተተው ይህ ስዕል፤ ሊገኝ የቻለው የባለሥልጣኑ ሴት ልጅ ቤቱን ለሽያጭ ባቀረበችበት ወቅት እንደሆነ የኔዘርላንዱ ጋዜጣ ኤዲ ዘግቧል።

ስዕሉ በጦርነቱ ወቅት አይሁዶች እንዲያመልጡ ሲረዳ ከነበረው የሥነ ጥበብ ነጋዴ ዣክ ጉድስቲከር ከተዘረፉት በመቶዎች ከሚቆጠሩ የሥነ ጥበብ ስራዎች መካከል ነው።

ጎድስቲከር ከኔዘርላንድስ በማምለጥ ላይ ሳለ ባጋጠመው አደጋ ባህር ላይ የሞተ ሲሆን ቀብሩ የተፈጸመውም እንግሊዝ ነው።

የጎድስቲከርን ህልፈት ተከትሎ ከነበረው የሥነ ጥበብ ስብስብ ውስጥ ከ 1,100 በላይ የሚሆኑትን ስራዎች ቤተሰቦቹ በግዳጅ ለከፍተኛ የናዚ ኃላፊዎች እንዲሸጡ ተደርጓል።

በዚህ መልኩ የሥነ ጥበብ ስራ ከገዙት የናዚ ኃላፊዎች መካከልም ከሂትለር ቀጥሎ ከፍተኛ ስልጣን የነበረው የሪችማርሻል ሄርማን ጎሪንግን ይገኝበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን ውስጥ የተገኙት የተወሰኑት ሥራዎች በአምስተርዳም ሪክሙዚየም ውስጥ የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ስብስብ አካል ሆነው እንዲቀመጡ ተደርገዋል።

በሕይወት የተረፈችው ጉድስቲከር ብቸኛ ወራሽ የልጁ ሚስት ማሪ ቮን ሳህር እ.አ.አ በ2006፤ 202 ያህል የሥነ ጥበብ ስራዎችን እንደተረከበች ተዘግቧል።

ነገር ግን ባሮክ ተብሎ በሚታወቀው የሥነ ጥበብ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአርቲስት ጁሴፔ ጊስላንዲ የተሳለ እና ኮንቴሳ ኮሌኦኒ የተባለች ሴት ስዕል እስከ አሁን ድረስ ጠፍቶ ቆይቷል።

በጋዜጣው ኤዲ የተደረገ ምርመራ ይፋ ያደረገው እንድ ሰነድ እንደሚያመለክተው፤ ስዕሉ በናዚ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መኮንን እና የከፍተኛው የናዚ ባለሥልጣን ሄርማን ጎሪንግን የፋይናንስ አማካሪ በነበረው ፍሬድሪክ ካድጂየን እጅ ነበር። የናዚ ኃላፊው በ1945 ወደ ስዊዘርላንድ ሽሽቶ የነበረ ሲሆን ኋላም ወደ ብራዚል እና አርጀንቲና ተዛውሮ ስኬታማ የንግድ ሰው ሆኖ ነበር። በ1979ም ሕይወቱ አልፏል።

ጋዜጣው፤ ስለ ሟቹ ናዚ ባለሥልጣን እና የጠፉ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በተመለከተ በቦነስ አይረስ የሚገኙትን ሁለት ሴት ልጆችቹን ለማነጋገር ለበርካታ ዓመታት ሙከራ ቢያደርግም እንዳልተሳካለት አስታውቋል።

ነገር ግን ከካድጂያን ሴት ልጆች አንዷ በአንድ ወቅት የአባቷ ንብረት የነበረውን ቤት፤ አርጀንቲና ውስጥ በውድ ቤቶች ሽያጭ ላይ በተሰማራ የሪል ስቴት ወኪል አማካኝነት ሽያጭ ማቅረቧን ተከትሎ ለዓመታት ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ጋዜጠኞች ዕድል ቀንቷቸዋል።

በኔዘርላንድ የባህል ቅርስ ኤጀንሲ የሚሰሩት እና የሥነ ጥበብ ስራውን የሚያሳዩ ፎቶዎችን የመረመሩት አንሊስ ኩል እና ፔሪ ሽሪየር ምስሎቹን "ቅጂ ሊሆኑ ይችላል ብሎ ለማሰብ የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም" በማለት ለጋዜጣው ተናግረዋል።

ሌላ የተዘረፈ የ17ተኛው ክፍለ ዘመን የሥነ ጥበብ ስራ ደግሞ በአንዷ የባለስልጣኑ ልጅ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ እንደታየ ኤዲ ዘግቧል።

ፎቶው ከታየበት ጊዜ አንሥቶ እህትማማቾቹን ለማነጋገር የተደረጉት ሙከራዎች በሙሉ እንዳልተሳኩ የኤዲ ዘገባ ያመለክታል። አንደኛዋ እህት "ከእኔ ምን መረጃ እንደምትፈልጉ አላውቅም፤ ስለየትኛው ስዕል እያወራችሁ እንደሆነም አላውቅም" ማለቷም ተዘግቧል።

የጉድስቲከር ወራሾች ጠበቆች ስዕሉን ለማስመለስ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የሥነ ጥበብ ነጋዴው ልጅ ሚስት ቮን ሳህርም "የቤተሰቤ ዓላማ ከዣክ ስብስብ የተዘረፉትን እያንዳንዱን የጥበብ ሥራዎች መልሶ ማምጣት እና የእርሱን ቅርስ መልሶ ማቋቋም ነው" ብላለች።