ኢትዮጵያን ከዓለም ልዩ የሚያደርጋትን ታሪክ የሚፈልገው ፀሐፌ ተውኔት - መልካሙ ዘሪሁን

ንጉሥ አርማህን ሆኖ የሚተውነው ተስፋዬ ገብረሃና (መሃል) እንደ ዣን አፊላስ ሆኖ የሚጫወተው ሄኖክ ዘርዓ ብሩክ (በስተግራ) እንደ ልዑል ፍሬ ሰናይ ሆኖ የሚጫወተው ሄኖክ ብርሀኑ (በስተቀኝ)
የምስሉ መግለጫ, ንጉሥ አርማህን ሆኖ የሚተውነው ተስፋዬ ገብረሃና (መሃል) እንደ ዣን አፊላስ ሆኖ የሚጫወተው ሄኖክ ዘርዓ ብሩክ (በስተግራ) እንደ ልዑል ፍሬ ሰናይ ሆኖ የሚጫወተው ሄኖክ ብርሀኑ (በስተቀኝ)

ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ በታሪካዊ ተውኔቶቹ ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ጋር የነበራትን ግንኙነት ይመለከታል። ወደ አውሮፓ ተሻግሮ ኢትዮጵያን ከታላቁ እስክንድር ጋር ያስተሳስራል።

በረዥም ልብ ወለዱም ቢሆን ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር ያስተያያል።

መልካሙ ዘሪሁን የንጉሥ አርማህ፣ የህንደኬ ታሪካዊ ተውኔቶች ፀሐፌ ተውኔት፣ ከዲያቢሎስ ጋር ድርድር የተሰኘ ረዥም ልብ ወለድ ደግሞ ደራሲ ነው።

እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች የታየው "የእኛ እድር" የተባለ ሳታየር ኮሜዲ ተውኔትም ጽፏል።

መልካሙ ዘሪሁንን ታሪክ ይስበዋል። ከታሪክም የአገሩ የኢትዮጵያ ታሪክ።

ገናና የነበረችው ጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ እና ሥልጣኔ፣ ከፋርስ፣ ከባዛንታይን፣ ከኦቶማን ቱርክ ጋር በንግድ የተሳሰረችው፣ በጦር ሠራዊትም እጅግ ገናና የነበረችው አገሩ ታሪክ ይነሽጠዋል።

በቀይ ባሕር፣ በዘይላ፣ በአዱሊስ፣ በሕንድ ውቅያኖስ እስከ የመን ዳርቻ የንግድ መስመሮች የነበሯት የኢትዮጵያ ታሪክ የፈጠራ ሥራዎቹ ማዕከል ናቸው።

ታዲያ ገናና በነበረችበት ዘመን ከተከሰቱት መካከል ሁለቱን በተውኔት መልኩ አቅርቦ ለመድረክ በቅተዋል።

ሰሞኑንም ከ24 ዓመት በፊት በብሔራዊ ቴአትር በማንያዘዋል እንዳሻው ተዘጋጅቶ ለዕይታ በቅቶ የነበረው ታሪካዊ ተውኔት፣ ንጉሥ አርማህ፣ ዳግም በተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) አዘጋጅነት ወደ መድረክ ተመልሷል።

ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ ዘሪሁን

የፎቶው ባለመብት, Gashaw Legesse

የምስሉ መግለጫ, ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ ዘሪሁን

ታሪክ እና መልካሙ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ታሪክ እና ሥነ ጽሑፍ በአንድ ላይ ያደሩበት ተውኔት መጻፍ ለመልካሙ "የከረመ ፍቅር" ነው።

በተውኔቱ የአባቶችን ዓለም ማሳየት፣ በታሪክ መስታወትነት የቀደመችውን ኢትዮጵያ መመልከት፣ ከታሪክ አብራክ ዛሬን መፈለግ የነፍስ ጥሪው ነው።

በታሪካዊ ተውኔቶቹ ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያን ያስሳል።

"ታሪክ ይስበኛል። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ በደንብ ተሠርቷል፣ ተጽፏል፣ ተተንትኗል ብዬ አላምንም" ይላል።

እናም በዚህ መነጽር ታሪክን የተመለከቱ ጥበባዊ ሥራዎች በብዛት አለመኖራቸውን ሲያስብ ቁጭት ይሰማዋል።

ለእርሱ በታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የጊዜ ውስኑነት የለውም። ለዚያም ነው ነገሥታቱን ከሚለካ ጊዜ አውጥቶ ወሰን የሚያሳልፋቸው።

ተውኔቶቹ በታሪክ የተቀነበቡ ቢሆኑም ትናንትን አቅርበው፣ ዛሬን ሚዛን ላይ አድርገው ያሳያሉ።

የንጉሥ አርማህ አዘጋጅ ተሻለ (ዶ/ር) "መልካሙ ጥሩ አድርጎ ነው የሚጽፈው" ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል።

አዘጋጅ እና ተዋናይ ተስፋዬ ገብረማርያም መጀመሪያ የንጉሥ አርማህ ድርሰት ወደ ብሔራዊ ቴአትር ሲመጣ ከገመገሙት መካከል ነው።

"ከተለመደው የኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ፣ የራቀ መሆኑን እና አጻጻፉን ነበር የወደድነው" ይላል።

ንጉሥ አርማህ ወደ አምስተኛው መቶ ክፈለ ዘመን ርቆ የሚሄድ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ለማሳየት ያን ያህል ርቆ መሄድ ለምን አስፈለገ?

መልካሙ ለዚህ መልስ ለመስጠት በወጣትነቱ ዘመን የነበረውን የፖለቲከኞች ክርክር ማስታወስ ይወዳል።

ያን ጊዜ የነበረው ወሬ ይላል መልካሙ፣ "አሁን ያለችው ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ታሪክ ነው ያላት" የሚል ነበር።

ይህ ደግሞ በወጣቱ መልካሙ ልቦና ውስጥ የጥያቄ ቋጥኝ ፈነቀለ። የበለጠ የማወቅ፣ የመመርመር ፍላጎት አደረበት።

ያገኘው መልስ "ኢትዮጵያ...ከ3000 ዘመንም በላይ ታሪክ ያላት አገር ናት" የሚል ነው።

ታዲያ ፖለቲከኞቹ ለምን አሳነሷት? ሌላ ጥያቄ ተወለደ። ይህንን ለመመለስ ሲጥር ንጉሥ አርማህን ከፊቱ አገኘ።

ንጉሥ አርማህ የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች በመካ ከቁረይሽ ጎሳዎች ከፍተኛ ተቃውሞና ግፍ በገጠማቸው ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩ ናቸው።

የሚደርስባቸውን ስቃይ ለመሸሽ የአካባቢውን አገራት ሲያማትሩ አንገቷ ረዝሞ፣ ግርማዋ ገንኖ የተገኘችው በንጉሥ አርማህ አስተዳደር ስር የነበረችው ኢትዮጵያ ናት።

ንጉሥ አርማህ እና ሕዝባቸው ስደተኞቹን በፍቅር እና በአክብሮት ተቀበሏቸው።

የቁረይሽ መኳንንት ስደተኞቹ እንዲመለሱላቸው ቢጠይቁም ንጉሡ ፍትሐዊ ውሳኔ በመስጠት እና የሙስሊሞችን የእምነት ነጻነት በማረጋገጥ ጥገኝነት ሰጧቸው።

ከዚያ በኋላ ንጉሥ አርማህን ጽፎ ለብሔራዊ ቴአትር በመስጠት ስመ ብዙዋ ኢትዮጵያ ታሪኳ ከ1500 ዓመትም በላይ መሆኑን ለማሳየት ቻለ።

"ኢትዮጵያም ለእስልምና የመጀመሪያ መሸሸጊያ እና የሰላም ምድር ሆና በታሪክ ተመዝግባለች" ይላል ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ።

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ለእስልምና በዓለም ላይ መኖር ከየትኛውም የዓለም ክፍል በበለጠ መልኩ ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረጓም የመልካሙን ብዕር አንዳች ነገር አምጦ እንዲወልድ አድርጓል።

የቴአትሩ አዘጋጅ ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) መጀመሪያ ንጉሥ አርማህን እንዳዘጋጅ ብሔራዊ ቴአትር ሲጋብዘኝ ከምንም በላይ የሳበኝ ይህ ታሪኩ ነው ይላል።

ይህ ታሪክ ደግሞ ለመጪው ትውልድ በተገቢው መንገድ፣ በጥበብ በኩል መተላለፍ አለበት የሚል "ኃላፊነት" እንደተሰማው ተሻለ ያስረዳል።

አዘጋጅ ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) (በስተግራ) እና ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ ዘሪሁን (በስተቀኝ)
የምስሉ መግለጫ, የንጉሥ አርማህ ታሪካዊ ተውኔት አዘጋጅ ተሻለ አሰፋ (ከግራ) እና ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ ዘሪሁን

ንጉሥ አርማህ እና ኢትዮጵያዊነት

ንጉሥ አርማህ የመጀመሪያውን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተቀብለው ማስተናገዳቸው በአረቡ ዓለም እና በአፍሪካ መካከል መሠረት ጣለ።

እንደ መልካሙ አገላለጽ ንጉሥ አርማህ በእስልምና የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያ መጥቶ የቆየበት እና ተመልሶ ወደ አረቡ ዓለም የሄደበት ነው።

መልካሙ አንዳንድ የእስልምና ምሁራን "እስልምና ከመካ በፊት ኢትዮጵያ ላይ አስር ዓመት ቀድሞ ተሰብኳል ይላሉ። ታሪኩን እጅግ የተለየ የሚያደርገው አንዱ ይሄ ነው" ይላል።

ሌላው ደግሞ የንጉሥ አርማህን ታሪክ ለየት የሚያደርገው "በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው የፖለቲካ ጥገኝነት ተጽፎ የሚገኘው በታሪክ የንጉሥ አርማህ ታሪክ ውስጥ ነው።"

ወገኖቻቸው አሳድደው ሊገድሏቸው የነበሩ ሰዎችን ተቀብለው፣ አስቀምጠው መልሰው በክብር የሰደዱት ንጉሥ አርማህ ናቸው።

ይህንን ኢትዮጵያዊ ታሪክ በመውሰድ፣ የአረቡ ዓለም እና የኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክ ማድረግ አለመቻላችን ለመልካሙ ይቆጨዋል።

"እኔን የሳበኝ ትልቅ የዓለም ታሪክ መሆኑ ጭምር ነው" ይላል። ሌላው በዚያ ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሥ ከሃይማኖቶቹ በላይ አገር የምትባለውን ማስቀደማቸው የመልካሙን ብዕር ካሞቁት መካከል ናቸው።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የአይሁድ እና የክርስትና እምነቶች ቦታ ነበራቸው።

ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመጡት የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ መጠለያ ሲፈልጉ ፊታቸውን ማዳመን፣ ድንበሮቻቸውን መዝጋት አልፈለጉም።

ከዚያ ይልቅ "ሥርዓት አክብራችሁ፣ ወጉን አክብራችሁ ተቀመጡ ነው ያሉት።"

መልካሙ በዚህች ቀዳዳ አጨንቁሮ በጥንታዊት ኢትዮጵያ በንጉሥ አርማህ ዘመን የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የክርስትናውም፣ የእስልምናውም፣ የአይሁዱም፤ ተቻችሎ፣ ተከባብሮ መኖር የሚችልበት አገር ለመፈጠር የተሠራውን ተመለከተ።

ይህ ደግሞ ትናንትን ተመልክቶ ከዛሬ ለማቀራረብ እና ለትውልዱ ለማስተላለፍ የመልካሙ ብዕርን እንዲነሽጠው አድርጓል።

ተሻለ ይህን ተውኔት እንዲያዘጋጅ ኃላፊነቱን ሲረከብ የራሱን ትናት አድርጓል። በዚህም የተረዳው ኢትዮጵያውያን ቀይ ባሕርን ተሻግረው እንደሚገበያዩ፣ እንደሚዋጉ፣ ከአረብ አገራት፣ ከሕንድ፣ ከፋርስ ጋር የንግድ ትስስር እንደነበራቸው በአጠቃላይ ያቺ ጥንታዊት ኢትዮጵያ የግዛት ወሰኗ ሰፊ፣ ከዚህ ተመልሽ የማትባል የታፈረች እና የተከበረች መሆኗን ነው።

ይህንንም በዝግጅቱ ወቅት በአልባሳት፣ በቁሳቁስ እና በኪነ ሕንጻ ለማሳየት መሞከሩን ይናገራል።

ንግሥት ሆና የምትተውነው እታፈራው መብራቱ እና የንጉሡን ገፀ ባህሪ የሚጫወተው ተስፋዬ ገብረሃና

የፎቶው ባለመብት, Acapella Creative

የምስሉ መግለጫ, ንግሥት ሆና የምትተውነው እታፈራው መብራቱ እና የንጉሡን ገፀ ባህሪ የሚጫወተው ተስፋዬ ገብረሃና

ንጉሥ አርማህ ለዚህ ዘመን

ንጉሥ አርማህ ከ24 ዓመት በፊት ልክ እንደ ዛሬው በብሔራዊ ቴአትር ሲመደረክ ያዘጋጀው ማንያዘዋል እንዳሻው ነው።

በወቅቱ በተውኔቱ ላይ ከተሳተፉ ተዋንያን መካከል አሁን በዚህ ቴአትር ላይ የሚተውኑት ተስፋዬ ገብረሃና እና ቅድስት ገብረሥላሴ ብቻ ናቸው።

ተስፋዬ ገብረሃና ያኔ የንጉሡን የወንድም ልጅ ዣን አስፋህን ሆኖ ሲተውን፣ ቅድስት ገብረሥላሴ ደግሞ ልዕልት ናፓታን ሆና ነበር የተጫወተችው።

ተሻለን የማንያዘዋለን ዝግጅት አይቶት እንደሆን ሲጠየቅ አለማየቱን ይናገራል።

"አለማየቴ በአንድ በኩል ጠቅሞኛል እላለሁ። ምክንያቱም ማንያዘዋል ትልቅ አዘጋጅ ነው። ያኔ አይቼው ቢሆን ኖሮ ሳላውቀው የእርሱ ተጽዕኖ ሊያድርብኝ ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ።"

አሁን አጠቃላይ ከአጃቢ ተዋንያን እና ከተወዛዋዦቹ ጋር ከ70 በላይ ተዋንያን የሚሳተፉበትን ቴአትር "በነጻ አእምሮ በራሴ መንገድ ነው የሠራሁት" የሚለው ተሻለ፤ ከአዳዲስ ተዋንያን ጋር መሥራቱ ጉልበት የሰጠውን ያህል ተግዳሮትም እንደነበረው ይናገራል።

መጀመሪያ ላይ በቀደመው ቴአትር ላይ የተሳተፉ በርከት ያሉ ሰዎች ተካትተውበት እንደነበር የሚጠቅሰው ተሻለ፣ ከ24 ዓመት በፊት ሲሠራ የነበረውን ስሜት እና ዝግጅት በማስታወስ ወደዚያ የመሳብ ትግል እና ሙግት ነበር።

ከዚያ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ከዚያ ስሜት ወጥተው የአሁኑን ንጉሥ አርማህን እንደ አዲስ ሥራ፣ በአዲስ መልክ መሥራታቸውንም ያስረዳል።

መልካሙ ይህንን ታሪካዊ ተውኔት ሲጽፍ፣ ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) ደግሞ ሲያዘጋጅ የኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ ግዙፍ መሆኑን ተምረዋል።

መልካሙ ደግሞ አሁን እየገባኝ የመጣው "ታሪክን ባለማወቃችን ምን ያህል ስህተቶች እየሠራን እንዳለን ነው" ይላል።

ንጉሥ አርማህን ሆኖ የሚጫወተው ተስፋዬ ገብረሃና ደግሞ ይህ ተውኔት ዳግም ሊሠራ መሆኑን ሳውቅ ከቤተሰቤ ጋር ተነጋግሬ ነው ከአውስትራሊያ የመጣሁት "እንኳንም መጣሁ፤እንኳንም አላመለጠኝ የሚያስብል ሥራ ነው" ይላል።

ይህ ቴአትር ከ24 ዓመት በኋላ ነው ዳግም ለመድረክ የበቃው።

ይህ ትውልድ ይላሉ ደራሲው መልካሙ እና አዘጋጁ ተሻለ "ንጉሥ አርማህን አያውቀውም።"

መልካሙ ደግሞ "ንጉሥ አርማህ ቴአትሩን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ንጉሥ አርማህ የሚባል መሪ ነበራት ወይ የሚለውን ራሱ ያውቃል ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ።"

በዚህ ሃሳብ ተሻለም ይስማማል። ስለዚህ ለዚህ ትውልድ ቴአትሩ ዳግም ኅልው ሆኖ በመድረክ ላይ መታየት መጀመሩ ትልቅ አጋጣሚ ነው።

ከ1500 በፊት የነበረን "እንዲህ ዓይነት አኩሪ ታሪክን መልሰን ትውልዱ እንዲያውቅ የምናደርግበት አንዱ መንገድ ጥበብ፣ ተውኔት ነው" የሚለው መልካሙ እስካሁን ባሉት የቴአትሩ የዕይታ ጊዜያቶችም ይህንን እውነት መመልከቱን ይናገራል።

አዘጋጁ ተሻለ (ዶ/ር) ቴአትር በድጋሚ ማቅረብ ተገቢ የሚሆንባቸው ምክንያቶች አሉ በማለት የታየበት ዘመን ርቀት አንዱ መሆኑን ያስረዳል።

እንደ ንጉሥ አርማህ ዓይነት ተውኔቶችን ወጣቱ ትውልድ አላያቸውም። "እንኳን ወጣቱ፣ ጎልማሳውም ቢሆን ጥቂቱ ነው ያየው ማለት ይቻላል። ለእነሱ ድጋሚ ሳይሆን አንደ አዲስ ነው የሚሆነው።"

ሌላው የምትደግምበትም መንገድ ይወስነዋል የሚለው መራሄ ተውኔት ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) አንዳንዴ የቅርብም ሆኖ በተለየ ዕይታ ይዘኽው የምትመጣ ከሆነ ተመልካች እንደ አዲስ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ይመለከተዋል በማለት ንጉሥ አርማህን በተለየ መንገድ አዘጋጅቶ መቅረቡን ይናገራል።

ንጉሥ አርማህ ቴአትር በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ሲቀርብ

የፎቶው ባለመብት, Desta Production

የምስሉ መግለጫ, በፀሐፌ ተውኔት መልካሙ ዘሪሁን የተደረሰው እና በተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) የተዘጋጀው ንጉሥ አርማህ ቴአትር

ንጉሥ አርማህን ለዘመኑ ተመልካቾች

ቴአትሩ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ለመድረክ ሲበቃ የነበረው ተመልካች እያንዳንዷን ቃለ ተውኔት አጣጥሞ የሚሰማ፣ የተዘናከተ ጊዜ የነበረው ነው።

ለዚህም ይመስላል በወቅቱ ቴአትሩ በመድረክ ላይ ሲቀርብ ከ2፡45 እስከ 3፡00 ይፈጅ የነበረው።

ፀሐፌ ተውኔቱ የተጠበበበትን ኪነጥበባዊ ሥራ ለዳግማዊ ልደቱ ለማብቃት፣ ረቂቁን ወደ ተተግባሪ ኪናዊ ክዋኔ ለውጦ ከሰው ፊት ለማቅረብ፣ ጠቅላላ ሂደቱን የሚመራው ተሻለ (ዶ/ር) የተውኔቱን ታሪክ፣ ድርጊያዎቹን፣ ሙዚቃውን፣ ውዝዋዜውን፣ የቋንቋውን ትርጉም በዚህ ዘመን ተመልካች ልክ ለመሥራት አቅዶ ተነሳ።

መራሔ ተውኔቱ ፊታውራሪነቱን ተጠቅሞ የተውኔቱን ረቂቅ በመረዳት አንድምታውን፣ ድምፀቱን እና ድባቡን መተርጎም ጀመረ።

ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) የመጀመሪያው የቴአትሩ ጽሑፍም ወደ 91 ገጽ ብዛት እንደነበረው ያስታውሳል።

መልካሙ እና ተሻለ (ዶ/ር) ይህንን ታሪካዊ ተውኔት ለዚህ ዘመን እንዲሆን አድርገው የማጣጣም ሥራ ሠርተዋል።

በተለይ አዘጋጁ አሁን ያለው ተመልካች ድሮ የምናውቀው ዓይነት ረዣዥም ቃለ ተውኔቶችን መስማት እና ረዣዝም ፋታዎችን ማየት የሚፈልግ አይደለም በማለት አንዳንድ ውሳኔዎችን ማሳለፉን መልካሙ ያስታውሳል።

አሁን ያለው ተመልካች 'ጊዜ በረርክ በረረክ ግና ምን አተረፍክ' የሚል ሳይሆን፣ ከጊዜ ጋር አብሮ የሚከንፍ "የቲክቶክ ዘመን ትውልድ ነው" በማለት ቴአትሩ አጠር እንዲል መደረጉን አመልክቷል።

በዚህም ተውኔቱን ከ95 ገጽ ወደ 54 ገጽ፣ ከሦስት ሰዓት ወደ ሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ የመሰብሰቡን ከፍተኛ ሥራ አዘጋጁ ተሻለ መሥራቱን ይናገራል።

መልካሙ "ጊዜውን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ዕይታውን ሊይዙ የሚችሉ ነገሮችን ማምጣት፣ የታሪክ ፍሰቱ በጣም ፈጣን እና ተመልካቹን የሚይዝ ማድረግ ተችሏል" ይላል።

41 ገጽ የወጣለት ተውኔት ታሪኩ ሳይንገጫገጭ ለተመልካች ማድረስ ግን የታሰበውን ያህል ቀላል አልነበረም።

ስለዚህ ፀሐፌ ተውኔት መልካሙን ከጎን በመያዝ እርምት ማድረግ እንዲሁም "መጀመሪያ መልካሙ ብሔራዊ ቴአትር ለግምገማ የሰጠው ድርሰት እንደ አጋጣሚ እኔ ጋር ነበር። እርሱ ከረዥሙ አጠር ይላል። እርሱን እንደ ዋና መነሻ አድርጌ ከ24 ዓመት በፊት ከተሠራው የሚጠቅሙንን በመውሰድ አዳብረን የ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ አደረግነው።"

ከዚያ ከዚህ ቀደም ከተሠራው በአንድ ሰዓት አጥሮ ፈጣን ተውኔት ሆነ።

ተመልካች ሁለት ሰዓት ያህል ቁጭ ብሎ ሲመለከት ግን ዓይኑንም፣ ቀልቡንም የሚይዘው ነገር ያስፈልጋል።

ይህንን በማድረግ በኩል ደግሞ እንደተሳካለት የመጀመሪያው ቴአትር ላይ በግምገማ እንዲሁም በትወና የተሳተፈው ተዋናይ እና አዘጋጅ ተስፋዬ ገብረማርያም ይመሰክራል።

ተሻለም የበለጠ ዓይንን እና ቀልብን ሊይዝ የሚችል፣ በድርጊት የተሞላ፣ ከአንዱ ድርጊት ወደ ሌላው ድርጊት ሳይናጠብ እንዲሄድ አድርገን ነው የሠራነው ብሏል።

ንጉሥ አርማህ እስካሁን ባለው የመድረክ ቆይታ ተመልካች ሞልቶ ሲመለስ ተመልክተዋል።

አብዛኛው ተመልካች ወጣት መሆኑንም የተመለከቱት ፀሐፌ ተውኔቱ እና አዘጋጁ ውሳኔያቸው ትክክል እንደነበር አረጋግጠዋል።

ተስፋዬ ገብረሃና በበኩሉ "እስካሁን አብዛኛው የመጣው ወጣቱ ነው። አቀባበሉ ደግሞ የበለጠ ያስደስታል" ሲል የእነ መልካሙን ሃሳብ ያጠናክራል።

በተለይ ደግሞ በሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የቴአትሩ መግቢያ ቲኬት በ"ሁሉ በእጄ" መተግበሪያ ላይ በኦንላየን ሽያጭ መጀመሩ ለዘመኑ ተመልካች ቀለል ብሎ እንዲቀርብ አድርጎታል ይላል ፀሐፌ ተውኔት መልካሙ ዘሪሁን።

ንጉስ አርማህ ቴአትር ላይ ውዝዋዜ የሚያቀርቡ ተወዛዋዦች

የፎቶው ባለመብት, Desta Production

የምስሉ መግለጫ, ንጉስ አርማህ ቴአትር ላይ ውዝዋዜ የሚያቀርቡ ተወዛዋዦች

ተመልካች ምን ይዞ ይሂድ?

የቴአትሩ ፀሐፌ ተውኔት እና አዘጋጁ ተመልካቹ ከዚህ ቴአትር "የአገራችንን ከፍታ እንዲያዩበት" እንፈልጋለን ይላሉ።

ተስፋዬ ገብረሃና ደግሞ ቴአትሩ አሁን አጣነው የምንለውን ፍቅር፣ አንድነት ሰላምን የኢትዮጵያ ከፍታን ነው የሚያሳየው ይላል።

"እንዲህ ነበርን እንዴ? የቱ ጋ ነው የጠፋነው? ለሚል ጥያቄ መልስ ያገኝበታል" በማለት፤ የተጻፈውም የተመደረከውም እርሱን በሚያሳይ፣ እርሱን በሚመጥን መልኩ መሆኑንም ይናገራሉ።

መልካሙ እንደ ደራሲ ተመልካቹ ውስጥ እንዲቀር የሚፈልገው ደግሞ "የዚህችን አገር ታላቅነት በወሬ ሳይሆን በተግባር አይቶ፣ ሰምቶ፣ ዳስሶ ኢትዮጵያ ይህቺ ነበረች፤ አሁን ደግሞ ይህቺ ናት ብሎ እንዲወጣ ነው።"

ተሻለ ተመልካች ብቻ ሳይሆን እኛ ስንሠራው ራሱ ይህ ስሜት ነበረን ይላል።

"ስንሠራው እንደዚያ ዓይነት ስሜት ስለሚሰማን። ተመልካችም ያ ስሜት እንዲሰማው እና በራሱ እንዲኮራ፣ በራሱ ከፍ እንዲል ያንን እመኛለሁ።"

ከቤተ ተውኔቶች ጠፍቷል የሚባለው ተመልካች በብዛት እየመጣ በመሆኑ ለሌሎች ቴአትሮች መነቃቃት እንደሚፈጥር እና ፈጣን ሕይወት ውስጥ ያሉ ወጣቶች ቴአትሩን ለመመልከት መምጣታቸው ለቴአትሩ ፊት አውራሪ ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) ትልቅ ደስታን ፈጥሮለታል።

"ንጉሥ አርማህን ለማየት ወጣት ልጆች መጥተው ሳይ በጣም ልብ የሚያሞቅ ነገር ነው። ታሪኩን ፈልጎ እዚያ ውስጥ ያለን ነገር ለመውሰድ የመጣ ወጣት ትውልድ ስታይ ትልቅ ተስፋ ነው የሚታይህ።"

የንጉሥ አርማህ ቴአትር ተዋናዮች እና ደራሲው መልካሙ ዘሪሁን በመድረክ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Desta Production

የምስሉ መግለጫ, የንጉሥ አርማህ ቴአትር ተዋናዮች እና ደራሲው መልካሙ ዘሪሁን በመድረክ ላይ

ሌሎች ታሪካዊ ተውኔቶች

በርካታ ተውኔቶችን ያዘጋጀው ተሻለ አሰፋ ንጉሥ አርማህ "ትልቁ ታሪካዊ" ሥራው እንደሆነ እና ተውኔቱ ቀላል የማይለው "ተጽዕኖ እንዳሳደረበት" ይናገራል።

ከዚያ በፊት በሀገር ፍቅር የውድነህ ክፍሌ ድርሰት የሆነውን ቤርሙዳ የተሰኘውን የበዓሉ ግርማ ታሪክ ቀመስ ተውኔትን ያዘጋጀው ተሻለ፣ የአዶኒስ ትርጉም ሥራ የሆነውን የአና ማስታወሻ ለተመልካች ላቀረበው ተሻለ በንጉሥ አርማህ ተፈትኗል።

"እንደዚህኛው እነዚያ ብዙ አልፈተኑኝም። ይኼኛው የበለጠ ፈትኖኛል። እና በዚያ ውስጥ ተምሬያለሁ። በአገሬ ታሪክ እና ባለው ነገር ኮርቼያለሁ። ከፍ ብያለሁ።እና በጥሩ ሞቅታ በጥሩ ስሜት ነው ቴአትሩን የሰራሁት።"

ይህ ሞቅታ ደግሞ ሌላም ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ ቴአትሮች ብሠራ ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል።

"የእኔን የዝግጅት አካሄድ እንደ አዲስ በሌላ አቅጣጫ ለመሄድ እስከማስብ ድረስ ነው ተጽዕኖ ያደረገብኝ። እንደውም ሰሞኑን ሌላ ታሪካዊ ቴአትር ያላችሁ ፕሮዲውሰሮች ካላችሁ እያልኩ በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች ስጠይቅ ነበር። በዚህ ልክ ነው ተጽዕኖ ያደረገብኝ።"

ለታሪካዊ ተውኔት ፀሐፌ ተውኔቱ መልካሙ አሁንም ብዕሩ የኢትዮጵያ ታሪክን ለመንገር አይሰንፍም።

በቅርቡ "ወህኒ አምባ" የሚል ታሪካዊ ቴአትር በሀገር ፍቅር ለዕይታ ይበቃል ብሎ ይጠብቃል።

በመካከለኛ ኢትዮጵያ ዘመን የልዑላውያን ወህኒ ቤት በመባል ይታወቅ የነበረው ወህኒ አምባ፣ ለዘውድ ፉክክር የሚደረገውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቀረት፣ ባይቻል እንኳ ለመቀነስ ተብሎ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ወይም ልዑላዊያንን በዚህ ወህኒ አምባ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር።

ልዑላውያኑ ወገን ለይተው ለሥልጣን እንዳይሻኮቱ በወህኒ አምባ ማቆየት የኢትዮጵያ አንዱ ልዩ ታሪክ ነበር ይላል መልካሙ።

"የሚታሰሩት አንደኛ አብዮት እንዳይፈጥሩ ነው። የሥልጣን ፉክክር ለማስቀረት ነው። ሌላኛው ደግሞ እዚያው ውስጥ ገብተው አካላዊ፣ ሃይማኖታዊ ሌላውንም ትምህርት ቀስመው ተራቸው ሲደርስ ከዚያ ተመርጠው ይነግሣሉ።"

ይህንን ልዩ የኢትዮጵያ ታሪክ ወህኒ አምባ በሚል ርዕስ ጎንደር ላይ የነበረ አንድ ታሪክ ወስዶ እንደጻፈው እና ተውኔቱ በቅርቡ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይወጣል ብሎ እንደሚጠብቅ ይናገራል።