"እንደ እኔ እምነት የወንጌላውያን አማኝ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ በጭራሽ ሊገባ አይገባውም" - ዮናስ ጎርፌ

ዮናስ ጎርፌ

የፎቶው ባለመብት, Yonas Gorfe

የፊልም እና የሙዚቃ ባለሙያው ዮናስ ጎርፌ ሁለተኛ መጽሐፉን ለንባብ ካበቃ ሰንበትበት ብሏል።

ይህ 'ፕሮቴስታንታውያን በኢትዮጵያ ፖለቲካ - ከዐጼ ፋሲለደስ (1632) እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (2010-20. . .)" የተሰኘው መጽሐፍ በኢትዮጵያውያን የወንጌል አማኞች ዘንድ ለበርካታ ዓመታት የኖረውን አሉታዊ የፖለቲካ አመለካከት በስፋት ይዳስሳል።

መጽሐፉ በተለያዩ ዘመናት ለወንጌል ስብከት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሚሲዮናውያን ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ያለምንም ተቃውሞ ስለሚደግፉ ጴንጤ ቆስጤያውያን ያብራራል።

ዮናስ በ60ዎቹ የወንጌል አማኞች ትውልድ እና እርሱን በወረሰው የ80ዎቹ እና የ90ዎቹ ትውልድ ላይ ጠንከር ያለ ትችት ይሰነዝራል።

ለውይይታችን እንዲመቸን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች እያልን ለመጥራት ተስማምተን ጥያቄያችንን ጀመርን።

ቢቢሲ - መጽሐፍህን አንብቤ ስጨርስ የረዥም ጊዜ መብሰልሰል እና ቁጭት ታይቶኛል። ለምን ወንጌላውያን አማኞች ያለ ጥናት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ዘው ብለው ገቡ የሚል። ልክ ነኝ?

ዮናስ - አዎ፤ አሁን ለምን ዘው ብለው ገቡ? እስከ ዛሬ ድረስ የት ነበሩ? የሚል ነው። መጽሐፉ ላይ እንዳነበብከው ሌንጮንም ስጠይቀው፣ እነ ቄስ ኢተፋንም ሳናግር ሌሎቹም እንዳልነበሩበት እና አሁን ግን በድንገት እንደመጡበት ነው። በአንድ በኩል። ግን ይኼ ሙሉ እውነት አይደለም።

ከዚህ በፊትም በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈው ያውቃሉ፤ ግን ሁል ጊዜ መንግሥትን በሚደግፍ ወገን በደርግ ጊዜም ነበሩበት። የኢሠፓ አባልም ነበሩ። የቀበሌም ካድሬ ሆነው ብዙ የተሳተፉ የቤተክርስትያን ሕብረትን ያስወረሱ የወንጌል አማኞች ነበሩ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢህአዴግ ጊዜም የተለያዩ የብሔር ፖለቲካን በማቋቋም በጣም ተሳትፈዋል፤ በተለይ በደቡቡ። በዚህኛው ጊዜ ግን በሥልጣን ላይ በብዛት ይታያሉ ከሌላው ጊዜ በባሰ።

ይህን ግን ሌላ ቦታ አጽንኦት እንደምሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳደረገው ይህ ማለት ግን መንግሥቱ የወንጌል አማኞች፣ የፕሮቴስታንቶች ወይንም የጴንጤቆስጤዎች አይደለም። በግለሰብ ደረጃ ግን ከዚህ በፊት ከነበረው ቁጥር በጨመረ፣ ወሳኝ በሆነ ሁኔታ ዘው ብለው ገብተዋል።

ቢቢሲ - ከዚህ ተነስተን የወንጌል አማኞቹ ወደ ብሔር ፖለቲካ ዘው ብለው መግባታቸው ነው ችግር የሆነው ማለት ነው?

ዮናስ - የወንጌል አማኞች ሁል ጊዜ ራሳቸውን እንደሚገልፁት፣ እኛ ሁሉን ነገር መጀመሪያ በክርስቶስ ወንጌል መዝነን፣ ፀልየን፣ ተግተን ከዚያ በኋላ ወደ አንድ ነገር እንመጣለን ይላሉ። ይህ እንግዲህ በግልም፣ በማኅበራዊም ሕይወታቸው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ግን የጻፉት ነገር የለም።

እኔ የማወራው ስለ ብሔር ፖለቲካ ነው። የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ልክ ነው ወይ? የሥነ መለኮት እሳቤ ሠርተውለት አይደለም የገቡት። በቃ ዝም ብለው ግር ብለው ነው የመጡት። ራሳቸውንም አልጠየቁም።

ስለዚህ የእኔ መከራከሪርያ ያለው ከጉዲና ቱምሳ ጋር ነገሩን በማነጻጸር እርሱ ሶሻሊዝም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ኮሚኒዝም ሲመጣ ለይቶት የወንጌል አማኙም ሶሻሊዝምን ሊደግፍ ይገባል። ምክንያቱም ክርስቶሳዊ ነው። ድሃውን ለመታደግ የሚነሳ፣ ጭቆናን የሚያስወግድ ነው። ኮሚኒዝምን እንቃወማለን ምክንያቱም እግዚአብሔር የለም ብሎ ስለሚነሳ። ሶሻሊዝም የሚለው ሃሳብ ግን ጥሩ ሃሳብ ነው ብሎ እንዲህ ለይቶት ነበር።

አሁን ያሉት ፕሮቴስታንቶች ግን፣ ባለፉት ሰባት ዓመታትም ሆነ በመለስ ዜናዊ ጊዜ የነበሩት ግን ስለ ብሔር ፖለቲካ ምንም ያሉት ነገር የለም።በ1983 ዓ.ም. ላይ የብሔር ፖለቲካ ወደ መድረኩ ሲመጣ፣ 85 ላይ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ስለ ብሔር ፖለቲካ ምንም ያሉት ነገር የለም። እስቲ ይኼ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንዴት ይታያል? ብለው ያደረጉት ነገር የለም። ስለዚህ አባላት ሁሉ በተለያየ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ እየገቡ፣ በተለይ 97 እኮ ይህ በደንብ ታይቷል።

አንዳንዱ በብሔር ፖለቲካ ውስጥ ገባ፤ ሌላው በአገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥ ገባ። በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግር ነበር። የብሔር ፖለቲካውም እንዲሁ ለሁለት ከፈላቸው። የኢህአዴግ የብሔር ፖለቲካ እና የተቃዋሚው የብሔር ፖለቲካ በሚል። ይሄ የሆነው በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድ የመዘምራን ቡድን ውስጥ ነው። ይህ የሚያሳየው እንዳላሰቡበት ነው።

. . . አሁንም እኮ የብሔር ፖለቲካ፣ ልክ ነው ልክ አይደለም የሚለው ጥያቄ ቢነሳ አብያተ ክርስቲያናቱ ወይንም በግላቸው ቃለ ሕይወት፣ መካነ ኢየሱስ፣ ወይም መሠረተ ክርስቶስ ወይንም ሌሎች ትልልቅ ቤተ እምነቶች ቆም ብለው እስቲ ይህ ነገር ምንድን ነው? ብለው የሰጡት መልስ የለም። ያንን ነው ያየሁት።

ዮናስ ጎርፌ

የፎቶው ባለመብት, Yonas

ቢቢሲ - በመጽሐፍህ ውስጥ በአብነት የምታነሳቸው ቄስ ጉዲናን ነው። በተለይ ሶሻሊዝምን በመተንተን፣ ስለ ጭሰኛው በመከራከር፣ የመሬት ስሪት እንዲስተካከል በመወትወት በርካታ ነገር መሥራታቸውን ትጠቅሳለህ። ቄስ ጉዲና የነበሩበትን ዘመን ስንመለከት ግን የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቁጥር ከጠቅላላ የአገሪቱ ሕዝብ አንድ በመቶ ብቻ ነበር ። ከዚያ አንጻር ካየነው በዚያ ዘመን በተለየ ቄስ ጉዲና ተጽዕኗቸው በቤተክርስቲያኒቷ ላይ የጎላው የእምነቱ ተከታዮች አነስተኛ ቁጥር ስለነበራቸው ነው ማለት አንችልም?

ዮናስ - ቁጥራቸው ትንሽ ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያኒቷ ጠንካራ ነበረች። የተማረው ሰውም ቁጥር ትንሽ ነው። ያ የተማረውም ሰው ደግሞ በደንብ የተማረ እና ዓለም አቀፋዊ በሆነ ነገር ላይ ራሱን ያሳተፈ ነው። በአፍሪካ ውስጥ ካየን በ60ዎቹ ውስጥ የነጻነት እንቅስቃሴ በጣም ጉልህ ነበር።

ቄስ ጉዲና የተማረበት አሜሪካም የማርቲን ሉተር ኪንግ የጥቁሮች መብት አንቅስቃሴ ጉልህ ነበር። ጉዲና አሜሪካ በተማረበት ወቅት የሲቪል ራይት ሙቭመንት በጣም ጠንካራ ነበር። ስለዚህ ንቃተ ሕሊናው ነበረው። ግን ያ ሳይሆን የማኅበራዊ ኃላፊነቱ ትልቅ ነበር።

ይህንን የምታው ሌላ ቦታ የምሥራች የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ነው፤ ብሥራተ ወንጌል። ሬዲዮ ጣቢያው አሁንም አለ፤ በዚያ ጊዜ የነበረው የሬዲዮ ጣቢያ የማኅበራዊ ጉዳዮችን በጣም ያነሳ ነበር። ስለ ፓርላማው፣ ስለመንግሥት፣ ኃይለ ሥላሴን በቀጥታ አይንቀፍ እንጂ ስለ ፖለቲካው ብዙ ነገር ያወራ ነበር።

ያንን አሁን ካለው ጋር ብታነጻጽረው የወንጌል አማኞች ሚዲያ አሁን ብዙ ነው። በተለይ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮም አላቸው ግን ምንም ነገር ግን አያነሳም። ስለ ወንጌል፣ ስለ መንፈሳዊ ነገር እንጂ የማኅበራዊ ጉዳይም ይመለከተናል ብሎ ሲያነሳ አታይም።

ስለዚህ ይመስለኛል በወቅቱ የነበረው የሉተራዊ አስተሳሰብ ጠንካራ ስለነበር፣ ሉተራውያን ደግሞ በአፈጣጠራቸው ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ በጣም ስለሚሳተፉ በአፍሪካ የነጻነት እንቅስቀሴ ላይም ብዙ ተሳትፎ እና ባሕል ነበራቸው።

የእኔ መከራከሪያ ያ ባሕል ተበረዘ የሚል ነው። በኋላ በኋላ ጴንጤ ቆስጤዎቹ የወንጌላውያን አስተምህሮን በጣም እየዋጡት ሲመጡ እነርሱ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ባሕል ስለሌላቸው ሁሉ ነገር ለብ ለብ ሆነ። እና ያኔ ጥቂት ሆነው ያንን ሥራ የሠሩበት ምክንያት ጥቂት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ራሷ ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራት አመለካከት ነው።

ለምሳሌ ወንድማማቾቹን ባሮ ቱምሳን እና ጉዲና ቱምሳን በቤተክርስቲያን ሕዝብ በተሰበሰበበት አከራክራለች። ይህ የሚያሳይህ ቤተክርስቲያኒቷ ምን ያህል ክፍት እንደሆነች ነው። ራሱ ጉዲና ይጽፋቸው የነበሩት መፈክር እንበል አንበል፣ የሠራተኛ ማኅበር ትክክል ነው አይደለም? መሬት ላራሹን እንዴት እንመልከተው? ይኼ ሁሉ ይተነተን ነበር? በስብሰባዎቹ ላይ እየቀረቡ ይነጋገሩባቸዋል። ይኼ የሚያሳይህ ማኅበራዊ ንቃተ ሕሊና (ሶሻል አዌርነስ) ከሉተራውያን ባሕል የመጣው ገና አዲስ ነበር በኋላ ነው የጠፋው።

ቢቢሲ - አሁንም ስትመልስልኝ በመጽሐፍህም ውስጥ ክርስትናን ከፍትሕ እና ከማኅበራዊ ኃላፊነት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ለማሳየት የምትጠቅሰው ቄስ ጉዲናን ነው። በእርግጥ ቄስ ጉዲና የተማሩበት አገር፣ የነበሩበት ዘመን እና ያደጉበት ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ አድርጓል። አሁንም ግን እንደ እርሳቸው ውጪ ሄደው የተማሩ በርካታ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሉ። ታድያ ቤተ ክርስቲያን እርሳቸው የነበሩበትን ንቃት፣ እና አቋም ያላገኘችው ለምንድን ነው?

ዮናስ - ያንን ንቃት ያጣነው ቤተ ክርስቲያኒቱ በስደት ጊዜ፣ በይበልጥ የምናወራው መካነ ኢየሱስን ነው እንግዲህ፣ በስደት ጊዜ በጴንጤ ቆስጤዎቹ መዋጧ ነው። ከዚያ በኋላም ውጪ ሄደው ተምረው የመጡትም ያው የማኅበረሰቡን መልክ ነው ለመያዝ የሞከሩት። ከዚያ በኋላ ሁሉ ነገር ወደ መንፈሳዊ እንጂ የማኅበራዊ ጉዳይ ምንም ትኩረት የማንሰጥ ሆንን።

ለዚህ ምክንያቱ እኔ የአስተምህሮት ችግር ነው ነው የምለው። የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያንን በመጨረሻ ላይ አሸንፎ የወጣው የጴንጤ ቆስጤው አስተምህሮት ነው።. . . ብዙ ሰው የማይረዳው ፕሮቴስታንቱ ብዙ ሺህ ቅርንጫፍ እንዳለው ነው። መቶ አይደለም ሺህ ቅርንጫፍ አለው። ከእነዚያ ሺህ ቅርንጫፎች ውስጥ አንደኛው ጴንጤ ቆስጤ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ጴንጤ ቆስጤ በአስተምህሮቱ በአስተሳሰቡ በመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎሙ በዚያ የተነሳ ውጪ ሄደው የተማሩትም ሲመጡ በዚያ ተጽዕኖ ውስጥ ገቡ።

. . . ለምን እንደ ቄስ ጉዲና ዓይነት መሪዎች አላገኘንም ለሚለው በተለይ ከሰባዎቹ ጀምሮ የአስተምህሮ ምልከታ ተለወጠ። ከሰባዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የቤተክርስቲያኒቱ የቲዮሎጂ አመለካከት በጴንጤ ቆስጤዎቹ አመለካከት ጭምር የእነርሱ ሆነ ማለት ነው። ለዚህ ይመስለኛል።

ቢቢሲ- የወንጌል አማኞች የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ገብተዋል ትላለህ። አንተም አሁን እንደጠቀስከው የወንጌል አማኞች የአስተምህሮ አለመታወቅ ወይንም መሳከር አብዝተው የሚጮሁለት ጉዳይ ነው። ይህ ነው ፖለቲካዊ ቅርቃር ውስጥ የከተታቸው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

ዮናስ - የወንጌል አማኞቹ የአስተምህሮ ቅርቃር ውስጥ ገብተናል እኮ የሚሉት የተወሰነችው እና የፕሮስፔሪቲ ወንጌል ምናምን ነው። ሀብታም ትሆናለህ ምናምን የሚሉት ላይ ነው።. . . የእኔ ግን እንደርሱ አይደለም። የእኔ ዋና መሠረታዊ የሆነ መሳከር በኢትዮጵያ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ውስጥ ተፈጥሯል።

እዚህ አፍሪካ ውስጥ የትኛውም ቦታ ብትሄድ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲናት የራሳቸውን መስመር ለይተው ነው የሚሄዱት። ሉተራኖቹ ምን እንደሚያስተምሩ ያውቃሉ።. . . የአስተምህሮቱ መሳከር የመጣው መሠረታዊ በሆነው ዲኖሚኔሽናል መስመር ላይ በመደበላለቃችን ነው።. . . ያ መሳከር አሁን ያለንበት ግራ መጋባት ውስጥ ጨምሮናል። ስለዚህ ይህንን ነገር ማጥራት አለብን።

ዮናስ ጎርፌ በመጽሐፍ ምረቃ ወቅት ፊርማውን ሲያኖር

የፎቶው ባለመብት, Yonas Gorfe

ቢቢሲ - የ60ዎቹ እና የዚያ ተተኪ የሆነው ትውልድ የብሔር ፖለቲካ ዋነኛ አቀንቃኝ መሆኑን አጥብቀህ ትተቻለህ። አሁን ደግሞ እንደምትለኝ ሥነ መለኮታዊ መሠረት መጣል ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለምንድን ነው ይህ ትውልድ ይህንን ማድረግ ያልቻለው? አሁንም የዶክትሪን ችግርን ነው የምናነሳው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?

ዮናስ - አሁንም ቢሆን የዶክትሪን ችግር ነው።. . . አስተምህሮቱ ሁልጊዜም የሚያተኩረው ሰውን ለሰማይ ቤት ማብቃት ስለ ምድር ምንም አለመሳብ፣ ወደ ሰማይ ነው ማሰብ ያለብን የሚል ነው። ይህኛው ኃላፊ ነው የሚል ነበር።

አሁን ደግሞ ይህ ተገልብጦ በአሜሪካም ካየኽው እኛ ካልያዝነው የዓለምን ኢኮኖሚ እና አስተምህሮት ዓለም ትጠፋለች። ኢኮኖሚውንም መያዝ ያለበት ወንጌል አማኙ ነው። አምስት ተቋማት የሚሏቸውን...መቆጣጠር የሚል አዲስ አስተምህሮ ያመጡት አለ። እነዚያን በሙሉ የወንጌል አማኙ መቆጣጠር አለበት። ካልተቆጣጠረው ዓለም ወደ መጥፎ ሁኔታ ትሄዳለች የሚል ሌላ ጽንፍ አስተምህሮ ይዘዋል።

ያንን ጽንፍ በመያዛቸው ነው ናይጄሪያ፣ ዛምቢያ፣ ብራዚል ውስጥ አሁን ደግሞ በትራምፕ እንዲህ ዓይነት ትርምስ ውስጥ የገባነው። በሌሎች የአፍሪካ አገራት ውስጥም የዚህ ዓይነት ጽንሰ ሃሳብ እያቆጠቆጠ ነው።...ስለዚህ መሠረታዊ የሆነ የአስተምህሮት ችግር አለ። ያንን ችግር የያዘው ቤተ እምነት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል። ስለዚህ ዶክትሪናችንን ሁሉ የሚቀርጸው ያ አስተምህሮት ነው።

ቢቢሲ - የወንጌል አማኞች በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፏቸው ምንድን ነው መሆን ያለበት?

ዮናስ - እንደ ግለሰብ በጣም ሊሳተፉ ይገባል። አስበውበት ይጠቅማል በሚሉት የፖለቲካ መስክ መሳተፍ አለባቸው። እንደ እኔ እምነት ወንጌላዊ አማኝ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ በጭራሽ ሊገባ አይገባውም። ምክንያቱም ክርስቶሳዊ አይደለም። የክርስቶስ ፖለቲካ ለሁሉም ሰው ነው።

ክርስቶስ የሞተው ለሁሉ ሰው ነው። አንድ ክርስቲያን ደግሞ ወደ ፖለቲካ ሲገባ ለሁሉ ሰው በእኩልነት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ማገልገል ያለበት። የወንጌል አማኞች በግለሰብ ደረጃ ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ ሊበረታቱ ይገባል። ወደ ፖለቲካው ሲገቡ ግን ሁሉን አቀፍ፣ ለሁሉ በፍትሕ፣ በእኩልነት የቆመ ፖለቲካ ነው መሆን ያለበት።

...ቤተክርስቲያን ግን በምንም መመዘኛ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለባትም። መግባት ያለባት የሰው ልጆችን እኩልነት በሚያሳይ፣ እንደ የሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ ነው።

ቢቢሲ - ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ሕሊና መሆን አለባት እያልከኝ ነው?

ዮናስ- በትክክል! ሉተርም ያለው እርሱን ነው።. . . ቤተክርስቲያን የመንግሥት ሕሊና እንጂ የመንግሥት አካል አይደለም መሆን ያለባት። ሕሊናው ነው መሆን ያለባት። የምትቆጠቁጠው ነው መሆን ያለባት። እርሱን ስትስት ነው ከዚያ በኋላ አንሶላ ተጋፈፈች የምትባለው።

ቢቢሲ - የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ፖለቲካም ከፋፍለህ ግዛ ነው። ከዚህ ተነስተው ፖለቲካ ቆሻሻ ጨዋታ ነው የሚሉ አሉ። አንተ ደግሞ ክርስቶሳዊ ፖለቲካ የምትለው አለ። በፖለቲካ ውስጥ ወንድምን እንደራስ አድርጎ መውደድ የሚታሰብ አይለም። ታድያ የወንጌል አማኞች እዚህ ውስጥ አጣብቂኝ ውስጥ አይወድቁም?

ዮናስ - እንደ ግለሰብ ለሕሊናቸው ከሠሩ አይወድቁም። ምክንያቱም ፖለቲካ ሁልጊዜም ቆሻሻ ብቻ አይደለም። ቆሻሻውንም ማጽዳት ይችላል። በስካንዴኔቪያ አገራት አይተናል። አውሮፓም ውስጥ በብዙ አገራት አለ። እርግጥ ነው ፖለቲካ ውስጥ ሁልጊዜም ማመቻመች አለ። እሠራዋለሁ ያልከውን ሁሉ ትሠራለህ ማለት አይደለም። ስታመቻምች ግን መሠረታዊ የሆኑ የማትለውጣቸው ነገሮች አሉ። ለዚህ እኮ ነው የተለያዩ ፓርቲዎች የኖሩት።

ቢቢሲ - አሁን ያሉትን የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናትን ስናይ በእርግጥ ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ሊሉ የሚችሉበት የፀና መሠረት ላይ ናቸው?

ዮናስ- አይደሉም። ግን ጥያቄው ለምን አይደሉም ነው። በታሪካችን ውስጥ ምሳሌ አለን ወይ? አዎ አለን። ያንን ምሳሌ ወደ ኋላ ሄደን ቆፍረን ለምን አናወጣውም ነው የእኔ መከራከሪያ። በአፍሪካም ውስጥ ምሳሌዎች አሉን። የእኛን የተለየ የሚያደርገው ምንም ምክንያት የለም።

. . . በርካታ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ኢፍትሐዊ የሆነን ነገር በጣም ነው የሚሞግቱት. . . ብትፈልግ ላቲን አሜሪካ ውስጥ ሄደህ ማየት ትችላለህ። ጠንካሮች ናቸው። የእኔ ጥያቄ ለምን የኢትዮጵያ እንደዚህ ሆነ? ለምን የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ደካማ ሆኑ ነው? የእኔ ግምገማ ለራሱ ጠንካራ ቲዎሎጂ ያልሠራ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ አሁን ያለንበት ሁኔታ ውስጥ ወደቅን የሚል ነው።

ቢቢሲ - የወንጌላውያን አማኞች በአፄዎቹ ዘመን፣ በደርግ፣ በኢህአዴግ ዘመን ከነበራቸው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሚና አንፃር አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘመን ጭፍን ድጋፍ ማሳየታቸውን ተችተሃል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የብልጽግና ወንጌል ብዙ ቦታ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ለዚህ ይሆን ለብልጽግና ፓርቲ የወገኑት?

ዮናስ - የፓርቲው ስም እና የብልጽግና ወንጌል ዝም ብሎ የስም መመሳሰል እንጂ ለእኔ አይገናኝም። የብልጽግና ወንጌል የሚያወራው ዝም ብለህ ሃብታም ትሆናለህ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ግን፣ አሁን እኔ የማወራው ስለተጻፈው እና በግልጽ ስለሚታዩት ነገሮች ነው፣ በሥራ ያምናል።

ይህንን የሚያነብ የዐቢይ ደጋፊ ሊል ይችላል። እርሱ አይደለም ነጥቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ሰው ነው። ሠርቶ አሳይቷል።ሥራው ትክክል ነው አይደለም፤ ቅድሚያ መስጠት ላለበት ሰጥቷል አልሰጠም፤ እርሱ ሌላ ጉዳይ ነው። ግን በሥራ ልናማው አንችልም።...ድህነትን የጠላ ብልጽግና፣ ማደግን የናፈቀ ትውልድ መፍጠር አለብን ነው የሚለው። ያንን ግን ብሎ ዝም አላለም። በሥራ ሊያሳይ ነው የሞከረው። ቅደም ተከተል ላይ መለያየት ሊኖር ይችላል። ከብልጽግና ወንጌል ጋር ግን የሰውየው አካሄድ በፍፁም አብሮ አይሄድም።...የእኔ ትችት መደመር ብሎ የብሔር ፖለቲካን እንዴት አብሮ ማስኬድ ይቻላል የሚል ነው።