የመንግሥት እና የሃይማኖቶች ፍጥጫ በኢትዮጵያ

ፖሊስ እና ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ እምነት ዘርፎች ስር ጥብቅ ሃይማኖታዊ ትስስር እንዳላቸው ይነገራል። ይህም በተለያዩ የዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ውስጥ በጉልህ የሚታይ ነው።

አስከ ንጉሡ ሥርዓት መውደቅ ድረስም በነበረው ጊዜ የአገሪቱ መንግሥታት ከሃይማኖት በተለይም ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው ይታወቃል።

ወታደራዊው እና የኢህአዴግ መንግሥት ግን በይፋ ሕግን መሠረት አድርገው እራሳቸውን ከየትኛውም ሃይማኖት ቢያርቁም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በዕምነት ውስጥ ሲገቡ ወይም እምነቶች ተጽእኖ ሲያደርጉባቸው ቆይተዋል።

በካናዳ ካልጋሪ ውስጥ መምህር፣ ተመራማሪ እና አጥኚ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖት እና መንግሥት ይለያያሉ የሚባለው በተግባር ዕውን አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

“በእርግጥ ከደርግ ሥርዓት ጀምሮ ሃይማኖት እና መንግሥት በሕግ ደረጃ ተለያይተዋል። በተግባር ግን የለም” ይላሉ።

በሕገ መንግሥት ከመስፈሩ በፊትም መንግሥት እና ሃይማኖት መደበላለቅ ብቻ ሳይሆን፣ አንዱ ለአንዱ ተባባሪ በመሆን ሲተጋገዙ መኖራቸውንም ያስታውሳሉ።

“በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰፊ መሬት ባለቤት በመሆን ግብር እስከ መሰብሰብ የደረሰችበት እና ከንጉሦች ጋር ተባብራ ስትሠራ የኖረችበትን ታሪክ ነው የምናገኘው። መንግሥት እና ቤተክርስተያኒቱ ለሁለት ሺህ ዓመታት ያክል ስር የሰደደ ግንኙነት ነበራቸው” ይላሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ሥርዓቶች ሥልጣናቸውን ለማራዘም የሃይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር የተለያየ ስትራቴጂ እንደሚጠቀሙም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይናገራሉ።

ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባሉ።

“በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያላቸው ብቸኛ አደረጃጀቶች የሃይማኖት ተቋማት ናቸው። ከእዚህ ተከትለው ነው አነስተኛ አደረጃጀቶች የሚመጡት፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ‘ጥልቅ ሃይማኖተኛ ሕዝብ’ መኖሩ ነው” ይላሉ።

ሕገ መንግሥት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም ሳቢያ የሃይማኖት ተቋማትን መያዝ ለፖለቲካ የበላይነት ይጠቅማል የሚሉት አቶ ያሬድ፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆነው መጥፎ ተግባራትን የሚተቹ ሲሆን ደግሞ “መጥፎ የሚባል አገዛዝ ላይኖር ይችላል” ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና የፌደራሊዝም ሥርዓት መምህር የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ጂማም፣ በሁለቱ ሃሳብ ይስማማሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንደሚለው ሃይማኖት ከፖለቲካ፤ ፖለቲካ ደግሞ ከሃይማኖት ነጻ ናቸው። ነገር ግን ይህ አልሆነም ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ የመንግሥት እና የሃይማኖት መተሳሰር ባለፉት ጥቂት አስር ዓመታት ቢላላም አልተበጠሰም።

ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት ከሆነ ደርግ እና ኢህአዴግ ከሃይማኖት ርቀታቸውን ለመጠበቅ ጥረዋል።

“አሁን ባለው መንግሥት ግን የሃይማኖት መሪዎች ወደ ፖለቲካ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የመንግሥት ሰዎች ወደ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ገፍቶ የመግባት ሁኔታ ይታያል” ይላሉ።

በሁለቱም ወገን ጥቅም የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቁመው “አንዱ ሌላኛውን ሽፋን ማድረግ ስለሚፈልጉ በብዙ መልኩ መደባለቅ ይታያል” ብለው ያምናሉ።

ከነገሥታቱ ዘመን ጀምሮ ባለሥልጣናት እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ መዋቅር ያላቸውን ቤተ እምነቶች መቆጣጠር ከቻሉ “የፈለጉትን ነገር የማድረግ ዕድል እንደሚኖራቸው ያውቃሉ” ሲሉም ያስረዳሉ።

አቶ ያሬድ ደግሞ ተቋማቱን ከመቆጣጠር አልፎ ሃይማኖቶችን መከፋፈል እንደተያዘም “ሙሉ ለሙሉ በማፍረስ፣ የፖለቲካ አደረጃጀት እንዲይዙ ተደርጓል” በማለት ይጠቁማሉ።

“መንግሥት በአንድ ወይንም በሌላ መንገድ የሃይማኖት አቀንቃኝ ሆኖ ይታያል። ተነስተው አፍጢር በዚህ ዓመት እኔ ነኝ የማዘጋጅላችሁ ይላል። ተነስቶ መስቀልን እኔ ነኝ እንዲህ የማደርግላችሁ ይላል። የፖለቲካው መሪዎቹ የሃይማኖት ዋና ፈትፋች እየሆኑ መምጣታቸው ነገሩን እያበላሸው እና አሁን ደግሞ ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲሄድ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል” ሲሉ አቶ ያሬድ ይገልጻሉ።

የሃይማኖት መሪዎች ናቸው ወደ ፖለቲካው እየሄዱ ያሉት ወይስ ፖለቲከኞቹ ወደ ሃይማኖቶች የሚለውን ፕሮፌሰር ጌታቸው በሁለት መንገድ ያዩታል።

“አንደኛው ሃይማኖትን እንደመሸጋገርያ በመጠቅም ወደ ፖለቲካው ዘልቀው የገቡ አሉ። ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት የራሱን ሰዎች በሃይማኖቶች ውስጥ ያስገባበት ሁኔታ ይታያል” ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖት እና ፖለቲካ የመደበላለቅ ሁኔታ በስፋት እየታየ በመሆኑ ለመለያየት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ሃይማኖት በፖለቲካ ውስጥ

ለአቶ ያሬድ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካው እና ሃይማኖት እርስ በእርስ ተጽዕኖ አላቸው።

“ፖለቲካውን ማወክ ከፈለግክ ሃይማኖትን መንካት ነው። እነዚህን ተቋማት ሲነኩ ሠላም ይጠፋል፤ ፖለቲካው ይደፈርሳል። ለብዙ ግጭቶችም ምክንያት ይሆናል” ይላሉ።

በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ሰዎች ተገድለዋል፤ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን እና በቅርቡ የመስጊዶች መፍረስን ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞ በዋቢነት ያነሳሉ።

ይህ ጣልቃ ገብነት ለብዙ ጥያቄዎች መነሳት እንዲሁም እስከ ግጭት የሚደርስ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት እንደሚሆኑ ይገለጻል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው “የሃይማኖት መሪዎቹም መንግሥትን ከያዙ ወይም ‘የእኛ’ የሚሉት ሰው በመንግሥት ስልጣን ውስጥ ካለ የሚፈልጉትን ነገር ማስጠበቅ እንደሚችሉ ነው የሚያምኑት” ይላሉ።

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ‘ከመከላከያ ጎን ነን፤ ከመንግሥት ጋር እንቆማለን!’ ሲሉ የተደመጡ የሃይማኖት መሪዎች መኖራቸውንም ያነሳሉ። ይህንንም “ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ አቋም ነው” ይላሉ።

“አማኞቹ [ትግራይ ውስጥ ያሉ] ‘ችግር ደርሶብናል’፣ ‘ተገደልን’፣ ‘ጠፋን’ እያሉ በሚማፀኑበት ጊዜ ቤተክርስትያኒቱ አልሰማቻቸውም። የሃይማኖት መሪዎች እስከ ጦር ግንባር ሲገቡም አይተናል። ስለዚህ የመንግሥት እና የሃይማኖት መሪዎች እከክልኝ ልከክልህ’ ሲባባሉ ይታያል” በማለት አክለዋል።

ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ችግር በተከሰተበት ጊዜ ለጸሎት የተሰባሰቡ ምዕመናን

የፎቶው ባለመብት, EOTC

የምስሉ መግለጫ, ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ችግር በተከሰተበት ጊዜ ለጸሎት የተሰባሰቡ ምዕመናን

ፖለቲካ በሃይማኖት ውስጥ

ይህ ደግሞ መፍትሔ ያሻዋል ሲሉ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ለአቶ ያሬድ “የመንግሥት ሰዎች ሲሻቸው ዋና የፖለቲካ ተዋናይ ይሆናሉ። ሲሻቸው ደግሞ ዋና የሃይማኖት ተዋናይ ይሆናሉ። እሱን ትንሽ ሥርዓት ማስያዝ በሕግ አግባብ መምራት ያስፈለግላል።”

የሃይማኖት ተቋማትን ነጻነት መስጠትም ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ።

“ልክ እንደ ሌላ አገር የሃይማኖት ተቋማትን እንደ ማጥቃት አይደለም። የሃይማኖት ተቋማትን ስትነካ ኢትዮጵያ ውስጥ የንቡን ቀፎ እንደመምታት ነው” ሲሉ ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

ስለዚህ መንግሥት ሕገ ወጥ ነገሮች በእምነት ተቋማት ቢከናወኑ እንኳን መነጋገረን ቀዳሚ አማራጭ ማድረግ አለበት ሲሉ ይገልጻሉ።

“ዝም ተብሎ ገና ለገና እኔ ነኝ አገር የምመራው ተብሎ የተፈለገውን ነገር ማድረግ፤ ሕገ ወጥም ቢሆን እንኳን የሕዝብን ንብረት ማፍረስ ማውደም አይቻልም። የተረጋጋ ፖለቲካ የሚፈልግ መንግሥት ከሆነ ማኅበረሰቡን ማማከር፤ የመፍትሔ ሃሳብ ከሕብረተሰቡ እንዲመነጭ ማድረግ አለበት። ይህንን ማድረግ ያቃተው ይመስለኛል የብልጽግና አስተዳደር” ይላሉ።

ከእነዚህ ስህተቶች የማይማር ከሆነ ሥርዓቱ ጭምር አደጋ ውስጥ እንደሚገባም ይጠቀማሉ።

የፖለቲካ እና እምነትን አለመግባባትን መቅረፍ የሚቻለው የሕግ የበላይነትን በማስከበር መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ ይገልጻሉ።

መንግሥትም የእምነት ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡን መረበሽ የለበትም፤ የእምነት ተቋማትም ፖለቲካ ውስጥ ለሚገቡት መንግሥት ድንበር ማበጀት እንዳለበት ተናግረዋል።

በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ልዩነቶች በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት ለማሸማገል ጥረቶች ሲደረጉ ተስተውሏል።

“በሃይማኖት ተቋማቱ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች መነሻቸው ሃይማኖታዊ ነው ወይስ ፖለቲካዊ የሚለውን ለመመለስ ሰፊ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል” የሚሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ናቸው።

የመስጂዶችን መፍረስ በመቃወም ባለፈው ሳምንት ተቃውሞ ያሰሙ ሙስሊም ምዕመናን

የፎቶው ባለመብት, MINBER TV/FB

የምስሉ መግለጫ, የመስጂዶችን መፍረስ በመቃወም ባለፈው ሳምንት ተቃውሞ ያሰሙ ሙስሊም ምዕመናን

“የማስጠንቀቂያ ደወል”

በተለይ መንግሥት በሃይማኖቶች ውስጥ እጁን ማስረዘሙን ለግጭቶች መበራከት እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ በቅርቡ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ወደ ግጭት የገቡበትን አጋጣሚ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

መንግሥት “በአገሪቱ መረጋጋት እና ሰላም ሳይኖር ግጭቶች ሲፈጠሩ ለአገዛዙ ይጠቅመኛል ብሎ የሚያምን ከሆነ” እጅግ አስከፊ ውጤት እንደሚያስከትል ፕሮፌሰሩ ያምናሉ።

“በሃይማኖት ውስጥ ለእምነትህ መስዋዕትነት መክፈል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን” ጠቅሰው መንግሥትም በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ፍላጎቱን ለማሟላት እንዳይሞክር ይመክራሉ።

የሃይማኖት አባቶችም በእምነት ስም ፖለቲካቸውን ለማስፈፀም ባይሞክሩ ሲሉም ያክላሉ።

አቶ ያሬድ እንደሚሉት ፖለቲከኞች “የሚዘነጉት ወይንም ለአፍታ ቆመው የማያስቡት” ኢትዮጵያ የጸናችው በገዢዎቿ በጎነት ወይም መልካም ሥራ አለመሆኑን ነው።

“ይህ ሁሉ የዘር ፖለቲካ የጥላቻ ፖለቲካ በዘር ላይ ተመሠረተ ፖለቲካ በተሰበከበት አገር ይህን ሕዝብ አንድ አድርገው ያቆዩት እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት ናቸው እንጂ የፖለቲካ ድርጅት ወይም መንግሥት ወይም ሌላ ነገር አይደለም” ሲሉ ይሞግታሉ።

በሁሉም የእምነት ተቋማት ብሔርን ጨምሮ የተለያዩ ልዩነቶች ያሏቸው ተከታዮቻቸው ሁሉንም ረስተው በየቤተ እምነታቸው በጋራ ፈጣሪያቸው ፊት ይቀርባሉ።

ይህንን መሠረት አድርገው ነው “ኢትዮጵያ የጸናችንበት ምሰሶ ከስር ገዝግዘው እንደመናድ ማለት ነው” የሚሉት አቶ ያሬድ።

ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የእምነት ተቋማት እና ተከታዮቻቸው በጎላ ሁኔታ ከመንግሥት ጋር ወደ ፍጥጫ እና ውዝግብ የገቡት ባለሥልጣናት በውስጥ ጉዳያቸው ሲገቡ እንደሆነ ይታወሳል።

በኢህአዴግ የመጨረሻ ዓመታት የእስልምና እምነት ተከታዮች መንግሥት በእምነቱ አስተዳደር ውስጥ እያደረገ ነው ያሉትን ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ “ድምጻችን ይሰማ” በሚል ተከታታይ ተቃውሞወችን ማድጋቸው እና በርካቶችም ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ፣ መንግሥት የሚጠበቅበትን አላደረገም በሚል በክስተቱ ውስጥ በተዘዋወሪ እጁ እንዳለበት ሲከሱ ቆይተዋል።

አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ውስጥ በፈረሱ በርካታ መስጂዶች ምክንያት የእስልምና እምነት ተከታዮች መንግሥት ለእምነት ተቋማቸው ጥበቃ አላደረገም በሚል እየወቀሱ ነው።

አቶ ያሬድ እንዲህ ያሉት የመንግሥት እና ምዕመናን አለመተማመን እና ፍጥጫዎች ሌሎች የፖለቲካ ችግሮች እንዲጨምሩ፣ ሌላ ነውጥ፣ ሌላ የሰው ሕይወት መቀጠፍን ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።

ምሳሌ ብለው የሚያቀርቡት ደግሞ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሥርዓቴ ውስጥ ጣልቃ ተገብቶብኛል ብላ ተቃውሞዋን የገለጸችበትን መንገድ ነው።

አሁን ደግሞ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መንግሥትን እየተቃወመ ነው። “እነዚህን ለመንግሥት የተሰጡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያዎች አድርጌ ብወስዳቸው ይቀለኛል። በቃ የማንቂያ ደውሎች (አላርም) ናቸው” ብለዋል።