የትግራይ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለመመለስ ምን ይላሉ?

የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ

የፎቶው ባለመብት, Dimtsi Woyane

በትግራይ የተቀሰቀውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በትግራይ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሯል።

የትግራይ ቤተ ክህነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጥም የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነትን መስርቷል።

የትግራይ ሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስን ለፌደራሉ መንግሥት በመወገን የሚከሷት ሲሆን፣ ንጹሃን እና ካህናት ሲገደሉ፣ የዕምነት ተቋማት ላይ ውድመት ሲደርስ፣ ቅርሶች ሲዘረፉ ሲኖዶሱ ዝምታን መርጧል ብለዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም በቤተ ክህነት መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በዕርቅ ለመፍታት ቢሞከርም ፍሬ አላፈራም።

ውዝግቡ እልባት ባላገኘበት ሁኔታ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት በቅርቡ 10 “ኤጲስ ቆጶሳትን” በሀገር ውስጥና በውጭ እንደሚሾም አስታውቋል።

በዚህ ሹመት ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ምንም ዓይነት አስተያየት ባይሰጥም ከዚህ ቀደም የትግራይ ቤተ ክህነት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ እና በአውስትራሊያ በሚገኙ ሃገረ ስብከቶች ለሚገኙ ምዕመናን ኤጲስ ቆጶሳት መሾሙን ባስታወቀበት ወቅት ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ በትግራይ ቤተ ክህነት ላይ የቤተ ክርስቲያኗን ጸንቶ የቆየ ተቋማዊ አንድነት እና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚንድ መልኩ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” ጽ/ቤት የሚል አዲስ መዋቅር ማቋቋሙ ሕገወጥ ነው ብሎ ነበር።

የኤጲስ ቆጶሳት ሹመቱንም በተመለከተ ቀኖና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን የጣሰ ሲል ፈርጆታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስን ቢቢሲ ትግርኛ አናግሯቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ፡ የትግራይን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተነጠለችው የትግራይ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ 10 "ኤጲስ ቆጰሳትን " በአገር ውስጥ እና በውጭ እንደምትሾም አስታውቃለች። ይህ የአዳዲስ ጳጳሳት ሹመት ፋይዳው ምንድነው?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ እነዚህ ጳጳሳት አባት ሆነው የሚመሩ፤ ሕዝብን የሚመክሩ እና የሚገስፁ፤ ቀሳውስት እና ዲያቆናትን የሚሾሙ እንዲሁም የቅስና ማዕረግ የሚሰጡ ናቸው።

ቢቢሲ፡ የትግራይ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሰራር በተለየ አቅጣጫ ነው እየሄደች ያለችው፣ ይህ ለምን ሆነ?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ ውሳኔው ለሕዝባችን ደስታ ነው። እራስን ማስተዳደር፤ ትግራይ በልጆቿ እንድትገለግል የሚያደርግ ነው። በውስጥም በውጭም ያለው የትግራይ ሕዝብ እንባውን አፍስሷል። ስለዚህ የሕዝባችን እንባ የሚያብስ፤ የሕዝባችንን ልብ የሚያረሰርስ ነው የሚሆነው።

ቢቢሲ፡ በአንዳንድ ዞኖች ለምሳሌ በደቡብ ትግራይ ዞን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሾሙ ጳጳሳት እንደነበሩ ይታወቃል። ታድያ በእነዚህ አካባቢዎች አዲስ ሹመት የምታካሂዱበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ በዚያ የነበሩ [ሃይማኖታዊ አባቶች] ሕዝቡን ከድተው ጥለውት ስለሄዱ፤ ሲጨፈጨፍ ስላልደረሱለት እና እግዚአብሔር ያፅናችሁ ስላላሉት ነው። በልጆቻቸው ላይ ስለጨከኑ፤ ሕዝቡ በከበባ ውስጥ በነበረት ጊዜ ይሁን ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ‘አይዞን’ ስላላሉት፤ ሕዝቡ ራሱ ‘አባቶች ይመደቡልን’ በማለቱ ነው የመደብነው።

ቢቢሲ፡ በአሁኑ ወቅት በሰሜን አሜሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የታካሂዱት ሹመት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ምደባ ባደረገባቸው ሃገረ ስብከቶች ነው ወይስ አዲስ በትግራይ ተወላጆች የተቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናትን ነው የሚወክሉት?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ በውጭ ያሉ ምዕመናን አዲስ አበባ ባለው ሲኖዶስ ነበር ሲመራ የቆየው። ነገር ግን የትግራይን ጦርነት ተከትሎ ጭፍጨፋ ሲፈጸም የትግራይ ተወላጆች ተለይተው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን አቋቋሙ።

እልቂቱ፣ ስቃዩ እና ሞት ሲበዛ፣ ‘ካልረዱን ራሳችንን ችለን እንለያለን’ አሉ። የሚገርመው በእየሩሳሌም ሲገለገሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ከቤተክርስቲያን በአድማ ከተባረሩ ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጥሯል። ችግር ውስጥ ናቸው። ስለዚህ መከራ ሲበረታበት ነው የተለየው። [በውጭ አገር] የተቋቋሙት አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ ቀሳውስት አሏቸው። ጳጳሳት ስለሚያስፈልጋቸው ተመካክረን ምደባውን አካሂደናል።

ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትን ራሷ እንደምትሾም ነው የሚታወቀው፤ ታዲያ የእናንተ ሹመት ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ የሚቀበለው እና የማይቀበለው የትግራይ ሕዝብ ነው። ‘ይሾምልን፤ አባት ያስፈልገናል” እያለ ያለ ህዝብ ነው’ኮ የሚቀበለው። ከሌሎች አካላት ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። በሕዝባችን ዘንድ ግን ተቀባይነት አለው።

ቢቢሲ፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ትግራይ ሲመጡ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ጉዳይ አንስተውላችሁ ነበር?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ ስለዚህ ጉዳይ አላናገሩንም። አንድ አባት ሞተው ለቀብር ነበር የመጡት። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተውም ወዲያው ነበር የተመለሱት።

ቢቢሲ፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመገንጠል እንደ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመቋቋም የራሳችሁን ካህናትና ጳጳሳት በመሾማችሁ የሚደርስባችሁ ጫና ይኖር ይሆን?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ እስከ ዛሬ ምንም አይነት ጫና አልደረሰብንም። ቀጥሎ የሚሆነውን እናያለን። በርግጥ ውሳኔያችን ለአንድ ወገን ደስታ፣ ለሌላው ደግሞ ሐዘን ነው። ፖለቲካና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው። እኛ ሕዝባችን ብለን በመንፈሳዊነት ቤተ ክርስቲያናችንን ማስተዳደር እንችላለን። እኛ በሚያዋጣን መንግሥትም በሚያዋጣው መንገድ መሄድ እንችላለን። ሁለቱም የተለያዩ ናቸው።

ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነቱን ወደ ቀድሞው ለመመለስ ከዚህ ቀደም ደብዳቤ ልካ ነበር። እንደገና አንድ የመሆን ዕድል ይኖር ይሆን? አቋማችሁ ምንድን ነው?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ አቋማችንን ከዚህ ቀደምም አሳውቀናል። ከመጀመሪያውም ስናብራራ ቆይተናል። በጦርነቱ ወቅት ‹ሰይጣን ይሻለናል› የሚሉ ሊቀ ጳጳሳት ስለነበሩ በእኛ በኩል ‘እነዚህን አደብ አስገዙ፤ ቀኖና እዘዙላቸው፤ ካልሆነ ግን እራሳችንን ችለን እንገነጠላለን’ ስንል በተደጋጋሚ መግለጫዎችን አውጥተን ነበር። ይሁን እንጂ መግለጫዎቻችንን ሊቀበሉት አልቻሉም። ከዚህ በመነሳትም ‘ሰይጣን ይሻለናል’ ከሚሉ ሰዎች ጋር መኖር አንችልም በማለት ዶግማን፣ ቀኖናን እና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት በማድረግ ተለያየን።

ቢቢሲ፡ እርቅ እና መግባባት እንዲፈጠር እንዲሁም ወደ ቀድሞው እንድትመለሱ የምታስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ይኖሯችሁ ይሆን?

አቡነ መርሐ ክርስቶስ፡ የለም! የለም! . . . ከአሁን በኋላ ምንም ቢፈጠር ወደ ኋላ ተመልሰን አብረናቸው የምንሄድበት መንገድ የለም።