ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ሦስት አስርታት የገጠሟት አበይት ጉዳዮች ሲቃኙ

በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው ችግር መፍትሄ ካገኘ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, ebc

የምስሉ መግለጫ, በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው ችግር መፍትሄ ካገኘ በኋላ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአገሪቱ ከፍተኛ ተጽእኖ ካላቸው የእምነት ተቋማት መካከል አንዷ ናት።

ቤተክርስቲያኗ ከአብዮቱ መምጣት በፊት በነበሩት ንጉሣዊ አስተዳደሮች ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ሆና የቆየች ሲሆን፣ ወታደራዊው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ግን የነበራት ተጽእኖ በእጅጉ ቀንሷል።

ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ውስጥ ቤተክርስቲያኗ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈች ሲሆን፣ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ የመጡት ለውጦችም በተለያየ መልኩ ተጽኗቸውን አሳርፈውባታል።

በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት ጊዜ በውስጧ እና ከውጪ በገጠሟት የተለያዩ ፈተናዎች ምክንያት ችግሮች እና ጫናዎች ገጥመዋት ነበር።

በቅርቡም ለእምነቱ መስፋፋት እንቅፋት የሆኑ ናቸው የተባሉ የቋንቋ እና የአሳታፊነት ጉዳይን ባነሱ አባቶች አማካይነት በቤተከርስቲያኗ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ተፈጥሮ፣ ከሳምንታት ውዝግብ እና ፍጥጫ እንዲሁም የሰው ሕይወት አስከጠፋባቸው፣ አስራትን ካስከተሉ ክስተቶች በኋላ በስምምነት መፍትሄ ማግኘቱ ተነግሯል።

በዚህ የቅርብ ጊዜ ክስተት አማካይነት በተለይ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በቤተክርስቲያ ውስጥ ያጋጠሙ ጉልህ ክስተቶችን መለስ ብለን ቃኝተናል።

የሰሞኑ ቀውስ ጅማሬ

ውጥረቱ የጀመረው ከኦሮሚያ የተገኙ ሦስት ጳጳሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ሲኖዶስ ልዩነትን የማያስተናግድ እና አካታች አይደለም በማለት በድንገት አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ሲሾሙ ነው።

ለረዥም ዘመናት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በተወሰነ አካባቢ የበላይነት ስር ቆይታለችም ያሉት አባቶች፤ ኦሮሚኛን ጨምሮ በሌሎችም ቋንቋዎች ቅዳሴ እና ስብከት መካሄድ አለበት ይላሉ።

ቤተክርስትያኗ በበኩሏ ይህ እየተከናወነ ነው ትላለች። የሃይማኖት ተቋማትን እና አገልግሎቶችን እያሰፋች መሆኗን ብትገልጽም ይህ በቂ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።

ማፈንገጡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እና ሕግ ከመጣሱ ባሻገር አንድነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው ሲል ሲኖዶሱ አውግዞታል።

በአቡነ ሳዊሮስ ይመራል ተበወሎ የነበረው ‘የኦሮሚያ እና ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ’ “በእግዚአብሔር ፊት ሁሉም ቋንቋ እኩል ነው” ከማለት ባለፈ በማንነታቸው ምክንያት አድሎዎ እንደደረሰባቸውም ሲያነሳ ነበረ።

በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩት አባቶች መካከል አብዛኛዎቹ ከኦሮሚያ ክልል የተገኙ ናቸው።

የተከተለው ውግዘት

የአዲሱን ሹመት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ያለ ቤተክርስቲያኗ ዕውቅና ‘ጳጶሳትን’ በመሾም የተሳተፉ 29 ቀሳውስትን አወገዟል።

እገዳው ወሊሶ ላይ 26 አዲስ ‘ጳጳሳትን’ በመሾም የመሪነት ሚና የነበራቸው ሦስት ጳጳሳትንም ያካተተ ነበር።

እነዚህም ጳጳሳት አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና አቡነ ዜና ማርቆስ ናቸው።

በዚህ መሠረት ከሃይማኖታዊ ኃላፊነታቸው ከመነሳት ባለፈ፣ ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያንን ሃብት እንዳይጠቀሙ ታግደዋል።

ይህ ውሳኔ ግን የአዲሱን ሲኖዶስ እንቅስቃሴ የሚያስቆም አልነበረም። በዚህም ግጭቶችን ያስከተለውን ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወደሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ልከው ነበር።

ጳጳስ ሆነው ከተሾሙት መካከል አባ ጸጋ ዘአብ አዱኛ ቤተ ክርስቲያኗን ይቅርታ ጠይቀው በኋላ ላይ ተመልሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት

ውጥረቱ እየተባባሰበት በነበረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ላይ በተላላፈ ውይይት “ቤተ ክርስቲያን ችግሩን በውይይት መፍታት አለባት” ሲሉ ተናገሩ።

የካቢኔ አባሎቻቸውን በቤተክርስቲያኗ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ከማስጠንቀቅ ባለፈ ሁለቱም ወገኖች “እውነታ አላቸው” አሉ።

“ሕህጋዊ ላልሆነው እና የሥልጣን ጥማት ላለው ቡድን” ዕውቅና ሰጥቷል ሲል ሲኖዶሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት ተቸ። አንዳንዶቹ የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተያየቶችም “አሳሳች ናቸው” ሲል ሲኖዶሱ አክሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቤተክርስቲያኒቱም ሆነ የራሳቸውን አዲስ ሲኖዶስ የመሠረቱት አባቶች “እውነት” ይዘዋል ማለታቸውን ሲኖዶሱ ተቃውሞታል።

“የምንደግፈው ወይም የምናወግዘው ቡድን የለም። ሁለቱም ኦርቶዶክሶች ናቸው...” በማለት ሕዝብ በራሱ ቋንቋ የሚጠቀምበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

አክለውም “በኦሮሚያ ያሉ አማኞች በአፋን ኦሮሞ ልገለገል ይገባኛል ብለው የጠየቁትን ይህን ‘አታግኝ’ ማለት አልችልም” ብለዋል።

ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን በአስተዳደራቸው እና በቤተ ክርስቲያኗ መካከል የነበረው ግንኙነት መልካም የሚባል ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የእምነቱ ተከታዮች ዒላማ መደረጋቸውን ይገልጻሉ። በትግራይ ጦርነት ወቅት አቡነ ማትያስ በክልሉ “የዘር ማጥፋት” ተፈጽሟል ማለታቸው ግንኙነቱን ይበልጥ አሻክሮታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቤተከርስቲያኗ መሪዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, ebc

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቤተከርስቲያኗ መሪዎች ጋር

ቤተክርስቲያኗ ምላሽ እና ጥሪ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት ተከትሎ የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉትን የሃይማኖት አባቶች ይደግፋል ሲል ከሷል።

መንግሥት በቤተክርስቲያኗ እና በእምነቱ ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና እንዲያስቆም የነነዌ ጾምን አስመልክቶ የእምነቱ ተከታዮች ጥቁር በመልበስ ጸሎትማ ምህላ እንዲያካሂዱ ጥሪ ቀረበ።

በሌላ በኩል አዲሱ ሲኖዶስ የሾማቸውን አባቶች በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወደሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መላኩን ቀጠለ።

የፀጥታ ኃይሎች ሻሸመኔ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ላይ ጥይት ሲተኩሱ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ ቪዲዮ ያሳያል።

በሻሸመኔ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ቤተክርስትያን ውስጥ በከፈቱት ተኩስ ከአምስት ሰዎች በላይ ህይወታቸው ማለፉንና በርካቶች መቁሰላቸውን ቤተክርስቲያኗ ምንጮች እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገልጸዋል።

አዲሱ ሲኖዶስ በፀጥታ ኃይሎች ተደግፎ የኃይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራ ነው ስትል ቤተክርስቲያኗ ስትከስ ነበር።

በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ተከታዮቿ ላይ የጅምላ እስራት መፈጸሙን ከመግለጽ ባለፈ በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ችግር መፈጠሩንም ቤተክርስቲያኗ ገልጻለች።

አፈንግጠው የነበሩት የሃይማኖቱ አባቶች በኦሮሚያ ውስጥ “ከፍተኛ” ድጋፍ እና ተቀባይነት እንዳላቸው ሲናገሩ ነበር።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ስለ ቤተክርስቲያኗ ክስ እና ተከሰቱ ስለተባሉት ሁከቶች ምንም አላለም። ነገር ግን በስም ያልጠቀሳቸው አካላት አገሪቱን አንድነት ለመናድ መሞከራቸውን እና አሁንም ችግሩን ለማባባስ እየሠሩ ነው ሲል አክሎ አስጠንቅቋል።

በርካታ ታዋቂ ሰዎች ለቤተክርስቲያን ያላቸውን አጋርነት የሚያሳይ መግለጫ አውጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ጥቁር ለብሰው የሚያሳዩ ምስሎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ አጋርተዋል።

የኢንተርኔት ገደብ

በቤተክርስቲያኗ አማካይነት ሊደረግ ታቅዶ የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍን ተከትሎ ባለሥልጣናት ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እና የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን አገልግሎት ገድበዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ የተባለ ድርጅት እገዳው በፌስቡክ፣ በሜሴንጀር፣ በቴሌግራም እና በቲክቶክ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስታውቋል።

አርብ ዕለት የቤተክርስቲያኑ መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ ሲኖዶሱ ለእሁድ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፎች ለሌላ ጊዜ ማራዘሙን ገለጸ።

አንዳንድ ምዕመናን ውዝግቡ የአገሪቱን የዘር ተኮር አለመግባባት የደረሰበት ደረጃን የሚያንጸባርቅ አድርገው ሲመለከቱ፣ ሌሎች ደግሞ የፖለቲካ ፍላጎት ከጀርባው መኖሩን ይናገራሉ።

ይህም ከብሔር ጋር የተያያዙ ግጭቶች እየተባባሰ ባለባት አገር አለመግባባትን ሊያባብሰው ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር።

መቼ ምን ተፈጠረ?

  • ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት የሆነው በ4ኛው ክፍለ ዘመን ነበር
  • ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን አካል የነበረች ሲሆን እአአ እስከ 1959 ድረስም ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አልነበራትም።
  • አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው እአአ በ1959 ተሾሙ።
  • ኦርቶዶክስ እስከ ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ ዘመን ድረስ የመንግሥታዊ ኃይማኖት ሆና ቆይታለች።
  • ደርግ ንጉሠ ነገሥቱን ገልብቶ ሥልጣን ከተቆናጠተ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ የመንግሥት ሃይማኖት መሆኗ ከማክተሙም በላይ ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷ።
  • አቡነ ቴዎፍሎስ እአአ በ1979 ተገደሉ

ባለፉት ሰላሳ ዓመታት

በ1983 ዓ.ም ኢሕአዴግ ወታደራዊውን መንግሥት በመገርሰስ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያኗ ለሁለት ተከፈለች።

የወቅቱ የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ በፖለቲካ ጫና ምክንያት ከአገር ተሰደው ወደ አሜሪካ በመሄድ በስደት አዲስ ሲኖዶስ አቋቋሙ።

ሁለቱ ሲኖዶሶች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተለያይተው ቆዩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሁለቱ ሲኖዶሶች እንዲታረቁ ማሳመን ችለዋል።

ነሐሴ 2010 ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በአገር ውስጥ እና በውጪ ለሁለት ተከፍሎ የነበረው የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ ተዋህዶ አንድ ሆነ።

አቡነ መርቆርዮስ ከስደት ተመልሰው ሁለተኛ ፓትርያርክ ሆነው በ2014 ዓ.ም ህይወታቸው እስኪያልፍ አገልግለዋል።

ነሐሴ 2012፡ የኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት አስተዳዳሪዎች ጥሪ

በ2012 ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች አዲስ የክልል ሰበካ አስተዳደር እንዲቋቋም የሚጠይቅ ኮሚቴ አቋቋሙ።

በቀሲስ በላይ የሚመራው ኮሚቴ ምዕመናን አዲስ ክልላዊ ቤተክህንት እንዲመሠረት ምክንያት የሆናቸው የተሻለ አስተዳደር መፈለግ እና ቋንቋቸውን ለመንፈሳዊው አገልግሎት ለመጠቀም መሆኑ ተገልጾ ነበር።

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች የኮሚቴውን አባላትን ከማባረር ባለፈ ቤተ ክርስቲያንን እና አገርን ለመከፋፈል እየሞከሩ ነው በማለት ከሰዋቸዋል።

ከወራት በኋላ ሁለቱም ወገኖች ችግሮቹን ለመፍታት ተስማሙ።

ጥር 2014፡ የትግራይ ኦርቶዶክስ መሪዎች

በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተጀመረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ የትግራይ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጡ።

ቅዱስ ሲኖዶሱ “ጦርነቱን ከመደገፍ ባለፈ ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ሲጠቁ ዝም ብሏል” ሲሉ የትግራይ የሃይማኖት አባቶች ከሰዋል።

ቤተክርስቲያኑ በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠችም። በጦርነቱ ወቅት አቡነ ማትያስ መንግሥት በትግራይ ተወላጆች ላይ “የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል” ሲሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቀቀ። በኋላም መልዕክቱ የፓትርያርኩ ብቻ ነው በማለት ሲኖዶሱ ውድቅ አድርጎታል።

በቅርቡም ቤተክርስቲያኗ ከትግራይ አባቶች ጋር ያለውን መራራቅ ለማጥበብ እንደምትፈልግ ደብዳቤ የጻፈች ቢሆንም፣ አባቶቹ ቀደም ሲል በያዙት የመለየት አቋማቸው ጸንተው እንደሚቀጥሉ ተዘግቧል።