በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ግድያዎችና እስሮች መፈጸማቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

የነነዌ ጾም

የፎቶው ባለመብት, social Media

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ የመንግሥት የፀጥታ አባላት ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል በጥይት እና በድብደባ ግድያዎችን መፈጸማቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ።

ቤተክርስቲያኗ ሕገወጥ ነው ባለችው ሹመት አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አገረ ስብከቶችን መያዛቸውን የተቃወሙ ምዕመናን ላይ ላይ በመንግሥት የፀጥታ አባላት ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል በጥይት እና በድብደባ ግድያዎች ተፈጽሟል ብሏል - ኢሰመኮ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ ሥርዓትን የጣሰ ነው ባለችው የጵጵስ እና ሹመት እና ከአዲስ ሲኖዶስ ምሥረታ ጋር ተያይዞ ሃያ ስድስት አባቶችን ሹመታቸውን በመሻር በውግዘት መለየቷ ይታወሳል።

አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን ያሳወቁ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ አገረ ስብከቶችን መያዛቸውን ያስታወቀው ኢሰመኮ፣ በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎችም ጭምር ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጿል።

በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘውን ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ለመያዝ በሚሞክሩበት ወቅት እርምጃውን የተቃወሙ ሰዎችን ለመበተን የመንግሥት የፀጥታ አባላት ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ወስደዋል ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው።

ከመንግሥት የፀጥታ አባላት በተጨማሪ ከፀጥታ አባላቱ ጋር በተባበሩ አካላት ስምንት ሰዎች በጥይት እና በድብደባ መገደላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን አስታውቋል።

በሻሸመኔ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች የሟቾቹ ቁጥር 13 መሆኑን መግለጻቸውን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ የማጣራት ሂደቱ ቀጥሏል ብሏል። በተጨማሪም ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም መታሰራቸውንም አስታውቋል።

በተለያዩ ቦታዎችም አዲሱን “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል ያሉትን ጳጳሳት በተቃወሙ ምዕመናን እና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጪ እስራት ተፈጽሟል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶሱ የነነዌን ጾም በምህላ እና ጥቁር በመልበስ እንዲያሳልፉት በጠየቀው መሠረት ጥቁር የለበሱ ሰዎች እስር፣ ወከባ፣ ከሥራ ቦታ እና አገልግሎት ተነፍገዋል ብሏል።

እነዚህ ጥሰቶች ከቦታ ቦታ ቢለያዩም በተለይ በነቀምቴ፣ በግምቢ፣ በደምቢ ዶሎ፣ በሻምቡ፣ በአሰላ፣ በሻሸመኔ፣ በጭሮ፣ በያቤሎ፣ በጅማ፣ በቡሌ ሆራ እና በነጌሌ ቦረና ከተሞች ከሕግ ውጪ እስራት እና ተመሳሳይ የማዋከብ ድርጊቶች መፈጸሙን ማረጋገጡን ነው በዛሬ መግለጫው ያስታወቀው።

ኢሰመኮ ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል የተፈጸሙ ግድያዎች፣ እስሮች፣ መንገላታቶች “ፍጹም ተገቢ ያልሆኑ እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ በነጻነት ሃይማኖታቸውን እና ሐሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚፃረሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው” ብሏል።

አክሎም “መንግሥት የተሟላና ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ እና የተጎዱትንም ሊክስ ይገባል። በተጨማሪም የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ኃይል ከመጠቀም፣ ከማንገላታት፣ ከሕገ ወጥ እስር እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያለበቂ ምክንያት ከመገደብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥት የሚጠበቅበትን ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን አልተወጣም፣ እንዲያውም ለሕገወጥ ቡድን ድጋፍ እየሰጠ ነው ስትል ወቅሳለች።

መንግሥት ባለፉት ቀናት የተከሰተውን ቀውስ አስመልክቶ ባወጣቸው መግለጫዎች በችግሩ ውስጥ የትኛውንም ወገን ደግፎ እጁን እንዳላስገባ በመግለጽ፣ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚፍልግ መግለጹ ይታወቃል።

ከፓርትርያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ 26 ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት የጵጵስና ማዕረጉን የሰጡትን እንዲሁም የተሾሙትን የማውገዝና ሹመታቸውም ተሽሮ እንዲለዩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

የቤተ ክርስቲያኗ አካሄድ አካታች እንዳልነበረ እና ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እንዳልቻሉ በመግለጽ አዲስ ሲኖዶስ መቋቋሙን የገለጹት ጳጳሳት ውሳኔውን በማውገዝ በእርምጃቸው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

ቤተክርስቲያኗ አውግዛ የለየቻቸው ግለሰቦች ወደ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እንዳይደርሱ እንዲሁም ንብረቶቿን እንዳይጠቀሙ የእግድ አቤቱታ ለፍረድ ቤት ያቀረበች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ለዛሬ አርብ የካቲት 03/2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።