በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተጠራው ሰልፍ ፈቃድ እንደሌለው መንግሥት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, EOTC Broadcasting Service Agency
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሞኑ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያያይዞ ለየካቲት 05/2015 ዓ.ም. የተጠራው ሰልፍ ፍቃድ እንደሌለው የፀጥታ እና ደኅነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕገወጥ ነው ካለችው የጵጵስና ሹመት እና አዲስ ሲኖዶስ መመስረት ጋር ተያይዞ መንግሥት ጣልቃ በመግባት እንዲሁም ድጋፍ በመስጠት ወረራዎች፣ እስሮች፣ ማዋከቦች እና ግድያዎች ተፈጽመዋል በሚል ሰልፍ ጠርታለች።
በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች በሚል የተቋቋመውም አዲሱ ሲኖዶስ በተመሳሳይ ቀን እና ስፍራ አዲስ አበባ ውስጥ ሰልፍ ጠርቶ እንደነበር ግብረ ኃይሉ ካወጣው መረጃ መረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 27/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የካቲት 5 ዕለት በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የሚገኙ ካህናት እና ምዕመናን ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በመነሳት በመስቀል አደባባይ እና በሌሎች ስፍራዎች ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ውሳኔ ማስተላላፉ ይታወቃል።
ግብረ ኃይሉ ሰበሰብኳቸው ባላቸው መረጃዎች “በተመሳሳይ ቀን እና ቦታ ሕገወጥ የሰልፍ ጥሪ በማድረግ የዜጎች ሕይወት የሚቀጠፍበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ቅስቀሳዎች እየተደረጉ እና ሌሎችም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል” ብሏል።
ሰልፎቹን እንደ ሽፋን በመጠቀም ከውስጥ እና ከውጭ ተቀናጅተው አገሪቷን ለማፍረስ ለሚሰሩ ፀረ ሰላም ኃይሎች በር እየከፈተ መሆኑንም በመጠቆም የዕምነቱ ተከታዮች ግንዛቤ ውሰዱ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ሰልፎቹ ፍቃድ እንዳልተሰጣቸውና ይህንን ተላልፎ ሰልፉን ያካሄዱ ማንኛውም አስተባባሪዎች ወይም ተሳታፊዎች ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ ይሆናሉ ሲል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
ግብረ ኃይሉ “ለዜጎች እና ለአገር ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ሲባል ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ” አስጠንቅቋል።
በየክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎችም በየአካባቢያቸው “ሕገወጥ ሰልፎች” እንዳይካሄዱ አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርጉም ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
ቢቢሲ የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያን ለመጪው እሁድ አቅዳው ስለነበረው ሰልፍ በተመለከተ ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በሻሸመኔ ከተማ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ አምስት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በቤተ ክርስቲያኗ እና በመንግሥት መካከል ያለው ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እና ዕሁድ በተለያዩ ቦታዎች የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ሰላሳ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህ አሃዝ ምንም አይነተኛ ገለልተኛ ማረጋገጫ አልተገኘም።
ሲኖዶሱ ከሰኞ ጥር 29 ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የነነዌ ጾምን በጸሎት፣ በምህላ ምዕመናኑ እንዲያሳልፉ የተወሰነ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ቀናት በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ጥቁር ልብስ እንዲለብሱ ታዘዋል።
ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች በሦስት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ጥቁር ለብሰው በየቤተ ክርስቲየኑ አገልግሎት ሲከታተሉ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የወጡ ምስሎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች አሳይተዋል።
ጥቁር የለበሱ የዕምነቱ ተከታዮች በተለያዩ ስፍራዎች አገልግሎት እንደተነፈጉ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሎችም ወደ ሕዝብ ተቋማት እንዳይገቡ ሲከለክሉ እንደነበር ተገልጿል።
ቢቢሲ ለማረጋገጥ ባይችልም በፀጥታ ኃይሎች ምዕመናንን ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮዎችም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ወጥተዋል።
ግብረ ኃይሉ በስም ያልጠቀሳቸው ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ የሽብር ኃይሎች፣ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ከሚሹ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት ሃገሪቷን ወደያማባራ ብጥብጥ ለመክተት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው ያለው በመግለጫው የዕምነቱ አባቶችና ምዕመናን የዚህ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳትሆኑም ሲል አሳስቧል።
"ሕገወጥ እንቅስቃሴዎቹ ደም አፋሳሽ እንዲሆኑ ታቅዶ ችግሩ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎችበርካታ የጦር መሣሪያዎች ሲዘዋወሩ የነበሩ ሲሆን ግብረ ኃይሉ ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሸን ከአዘዋዋሪ የደም ነጋዴ እንዲሁም ሽብርተኞች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይገልፃል” ብሏል።
ከፓርትርያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ 26 ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗን ስርዓትና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት የጵጵስና ማዕረጉን የሰጡትን እንዲሁም የተሾሙትን የማውገዝና ሹመታቸውም ተሽሮ እንዲለዩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።
የቤተ ክርስቲያኗ አካሄድ አካታች እንዳልነበረና ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እንዳልቻሉ በመግለጽ አዲስ ሲኖዶስ መቋቋሙን የገለጹት ጳጳሳት ውሳኔውን በማውገዝ በእርምጃው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
ቤተክርስቲያኗ አውግዛ የለየቻቸው አባቶች በአብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እንዳይደርሱ እንዲሁም ንብረቶቿን እንዳይጠቀሙ የእግድ አቤቱታ ለፍረድ ቤት ያቀረበች ሲሆን ፍርድ ቤቱም ትናንት በዋለው ችሎት ለየካቲት 3፣ 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።












