የተወገዙት አባቶች ወደ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይገቡ ለፍርድ ቤት የእግድ ጥያቄ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, MAHBERE KIDUSAN
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አውግዛ የለየቻቸው ወገኖች በአብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እንዳይደርሱ እንዲሁም ንብረቶቿን እንዳይጠቀሙ የእግድ አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠበቆቿ ለቢቢሲ ገለጹ።
ቤተክርስቲያኒቱን ከወከሉ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አንዷለም በዕውቀቱ ገዳ እንደተናገሩት እግዱ የተጠየቀው ኤጲስ ቆጶሳቱን በሾሙት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ጠበቃቸው እና ቃለ አቀባያቸው ኃይለሚካኤል ታደሰ ላይም ጭምር ነው።
ጠበቃው እንዳሉት የእግድ አቤቱታውን ባለፈው ዓርብ ጥር 26/2015 ዓ.ም ያቀረቡ ሲሆን፣ ችሎቱ ለትናንት ሰኞ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው በቀረቡት አቤቱታዎች ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ችሎት በሰኞው ውሎውም፣ ቤተክርስቲያኒቱን የወከሉ አስር ጠበቆች ተገኝተው እግዱ ለማን መሠጠትና በምን መልኩ መፈፀም እንዳለበት ማብራሪያ መስጠታቸውን ጠበቃ አንዷለም በዕውቀቱ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ በድምጽ የቀረበው አቤቱታ ወደ ጽሑፍ ተለውጦ እንዲቀርብለት አስቸኳይ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ለረቡዕ የካቲት 01/2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
“የእግድ አቤቱታውን ያቀረብነው እየተፈጠረ ካለው ቀውስ ያድናል ብለን ስላሰብን ነው” የሚሉት ጠበቃው፣ በቀጣይ ግን በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ላይ የተቀመጡ መብቶችን በጣሱ ግለሰቦች፣ አዲስ በተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት፣ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በፌደራል ተቋማት ላይ ጭምር ክስ እንመሰርታለን ብለዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ መሠረታዊና መብቶች እና ነጻነቶች ችሎት የሃይማኖት ነጻነት፣ የንብረት፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የመንቀሳቀስ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አለመግባትን የተመለከቱ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መብቶች ሲጣሱ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን አለው።
ባለፉት ቀናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እውቅና ውጪ የተሰጠ ሹመትን ተከትሎ አለመግባባቶች መፈጠራቸው ይታወሳል።
ይህ አለመግባባት የተፈጠረው በኦሮሚያ ክልል ከፓትሪያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጪ የ26 ጳጳሳት ሹመት መሰጠቱ ከተሰማ በኋላ ነበር።
ይህንን ሹመት የሰጡት አባቶች “ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም እና ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም” በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ድርጊቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት እና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት ሹመቱን የሰጡ እና የተቀበሉትን አውግዞ እንዲለዩ አድርጓል።
ለሁለት ሳምንታት ያህል ዝምታን መርጦ የነበረው መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በኩል አቋሙን ያሳወቀ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ መንግሥትን በወገንተኝነት በመውቀስ አቋሙን በይፋ ተቃውማለች።
መንግሥት ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ የጠየቀ ቢሆንም፣ ቤተክርስቲያኗ ግን መንግሥት ሕገወጦችን የሚያበረታታ አቋም በመያዝ ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ችላ ብሏል ስትል አጥብቃ ወቅሳለች።
ጠበቃ አንዷለም እንደሚሉት በሚያቀርቡት ክስ ተከሳሾችን የመለየት ሒደት ወደፊት የሚታይ እንደሚሆን አመልክተዋል።
“የፌደራል መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውም አካል ወደ ክሱ ሊገባ ይችላል። የሕግ ኮሚቴው የሚወስነው ነው የሚሆነው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ ሰኞ ዕለት ባስቻለው ችሎት ባቀረቡት የዕቅድ አቤቱታ ላይ ተጠሪዎችን ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የእግድ አቤቱታው ተጠሪ የተደረጉ ሲሆን፤ “ወደፊት በሚሰባሰበው ማስረጃ መሠረት ተከሳሽ ሊሆኑም ይችላሉ” ብለዋል።
ጠበቃው የሕይወት እና የአካል ደኅነንትን በተመለከተ እንደተናገሩት “የተወገዙት እና የተገለሉት አቡነ ጤዎስታቴዎስ በተለያዩዩ ቦታዎች በሰጧቸው መግለጫዎች አገረ ስብከቱ፣ ካህናትና ጳጳሳት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የሚቀሰቅስ ንግግር አድርገዋል” ብለዋል።
በዚህም በነጻነት መብት ጥሰት፣ የመልካም ሥም እና የክብር መብት ጥሰት፣ የእኩልነት፣ የንብረት መብት፣ የሃይማኖት ነጻነት፣ የመንቀሳቀስ መብት ጥሰትን ጨምሮ ሌሎች የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ክሶችን እንደሚመሰርቱ አመልክተዋል።
ተጥሰዋል ሲሉ ለዘረዘሯቸው መብቶችም የሲኖዶሱን ስም ማጠልሸት፣ በተለይ በመንግሥት በሚደገፉ ሚዲያዎች ፍትሐዊ የሆነ የሚዲያ ሽፋን አለማግኘት፣ እኩል የደኅነንት ጥበቃ አለመደረግ፣ ወደ ጅማ አገረ ስብከት ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ጥር 21 በነበረ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ጥር 20 ወደ ጂማ ያቀኑት አቡነ እስጢፋኖስ ከአየር ማረፊያ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ጠበቃው እንደ አብነት ጠቅሰዋል።
ችሎቱ በቤተክርስቲያኗ ጠበቆች የቀረቡለትን የዕግድ አቤቱታዎችን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ረቡዕ የካቲት 01/2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
በቤተክርስቲያኗ ላይ የተፈጠረውን ይህንን ችግር በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባዘዘው መሠረት ከጥር 29/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚኖረው የነነዌ የጸሎት መርሐ ግብር ላይ ምዕመናን ጥቁር የሐዘን ልብስ በመልበስ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የጸሎት ሥነ ሥርዓቶች ላይ እየታደሙ ነው።
በአንዳንድ ከተሞች ይህንን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች እና አርቲስቶችም ጥቁር በመልበስ ከቤተክርስቲያኗ ጎን እንደሚቆሙ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለጹ ነው።












