መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት በውይይት መፈታት አለበት አለ

የፎቶው ባለመብት, Government Communication
የፌደራሉ መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው መለያየት በውይይት እና በቤተ ክርስቲያኒቱ አሠራር መሠረት መፈታት አለበት አለ።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጸ/ቤት ከሰሞኑ በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ከዚህ ቀደም በተቋማት ችግሮች መንግሥት የሚጠበቅበትን ሲወጣ ቆይቷል ያለ ሲሆን አሁንም ይህንን ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
“አማኞች ችግሩን ከማወሳሰብና ለሌሎች መጠቀሚያ ከመሆን በመታቀብ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይገባል” ያለው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤቱ የፀጥታ አካላትም ግጭት የሚያባብሱ ወፈኖችን ሥርዓት ማስያዝ አለባቸው ብሏል።
በተመሳሳይ ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በንግግር መፈታት አለበት ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከቤተ ክርስቲያኗ ጠንካራ ተቃውሞን ባስከተለባቸው ንግግራቸው የቤተክርስቲያኗ መሪዎች የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበው፤ በተለየ የምንደግፈው በተለየ የምንቃወመው ኃይል የለም ማለታቸው ይታወሳል።
“ሁለቱም ኃይሎች ኦርቶዶክሶች ናቸው። ሁለቱም ጋር ጥያቄዎች እና እውነቶች አሉ። . . . የሕዝብን መብት፣ የሕዝብን በራስ ቋንቋ የመጠቀም ፍላጎት ሳያፍኑ መፍታት ይቻላል። ያንን ካደረጉ ለእነርሱም ለእኛም እንደ አገር ጠቃሚ ነው” ብለው ነበር።
ነገር ግን የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ለዚህ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላነሷቸው ጉዳዮች በሰጠው ምላሽ ላይ፣ ንግግራቸውን አጥብቆ በመቃወም “ወገንተኛ እና ሕገ ወጦችን የሚያበረታታ ነው” ነው በማለት መንግሥት ሕግ እና ሥርዓትነ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።
ቤተክርስርቲያኗ ሕገወጥ ነው በማለት ያወገዘችው የጳጳሳት ሹመት ከተከናወነ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግረ ውጪ በመንግሥት በኩል በይፋ ስለጉዳዩ መግለጫ ሳይሰጥ ሁለት ሳምንት ከሆነው በኋላ ነው ዛሬ እሁድ ጥር 28/2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ ያወጣው።
ይህ መግለጫም ውዝግቡ እየተባባሰ እና ቤተክርስቲያኗ እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙ ባለበት ጊዜ ነው።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት ቅዳሜ ጥር 27/2015 ዓ.ም. ቤተክርስቲያኗ የእምነት አባቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ሲኖዶሱ ‘ሕገ-ወጥ’ የሚላቸው ቡድን በመንግሥት እየተደረገፉ በቤተ-ክርስቲያን ላይ ወረራ እየፈጸሙ ነው ብሏል።
ሲኖዶሱ በመግለጫው የቤተክርስቲያኗ ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የእምነቱ ተከታዮች በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. ጠዋት ከየአጥቢያቸው በመነሳት የጥምቀተ ባሕር ወይም የመስቀል በዓል በሚከበርበት አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፏል።
ሲኖዶሱ በመግለጫው ቅዳሜ በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቤተክርስቲያንን ከወረራ ለመጠበቅ በወጡ ምእመናን ላይ “ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል ተፈጽሟል” በማለት በቁጥር ያልታወቁ ምእመናንም ላይ ከፍተኛ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክቷል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ በመግለጫው ትናንት ቅዳሜ ጥር 27/2015 ዓ.ም. በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ስላጋጠመው ያለው ነገር ባይኖርም “ችግሩን ለማባባስና በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር፡ በሚጥሩ አካላት ላይ መንግሥት የሕግ የማስከበር እምጃ ይወስዳል” ብሏል።
የፈረንሳይ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ትናንት በሻሸመኔ ባጋጠመው ክስተት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ለቤተክርስቲያኗ ቅርብ የሆነውን ተዋህዶ ሚዲያ ማዕከልን ጠቅሶ ዘግቧል።
ባለፉት ቀናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እውቅና ውጪ በሦስት ጳጳሳት የተሰጠ ሹመትን ተከትሎ አለመግባባቶች መፈጠራቸው ይታወሳል።
ይህንን ሹመት ያካሄዱት የሃይማኖት መሪዎች ‘ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም እና ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም’ በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
በፓሪያሪኩ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ደግሞ ከቤተክስቲያኗ ሥርዓት እና ሕግ ውጪ ተሰጥቷል ያለውን የጳጳሳት ሹመት ተከትሎ ጥር 18/2015 ዓ.ም. የጵጵስና ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ከቤተክርስቲያኒቷ ተወግዘው እንዲለዩ መወሰኑ ይታወሳል።












