የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተቃወመ

ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ

የፎቶው ባለመብት, MAHBERE KIDUSAN

የምስሉ መግለጫ, ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለካቢኔ አባሎቻቸው ሰሞኑን ሰጡትን ማብራሪያ በመቃወም መግለጫ ሰጠ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብ አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል በምትገኝ አንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ በሦስት ጳጳሳት አማካይነት በተሰጠ የ26 ጳጳሳት ሹመትን ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶሱ የውግዘት ውሳኔ ማሳለፉ እና የተወገዙት አባቶችም ተቃውሟቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከካቢኔ አባሎቻቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ከመናገራቸው በፊት በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የተከሰተውን ቸግር በተመለከተ መንግሥት በይፋ ምንም ሳይል ቆይቶ ነበር።

በስብሰባው ላይ ከተደረጉት ውይይቶች ተለይቶ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከተከሰተው ጉዳይ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ጠቅላይ ሚኒስተሩ ብቻ የተናገሩት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ.ም. ምሽት ከቀረበ በኋላ ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ የሰጠው።

በመግለጫው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በመጥቀስም ማብራሪያ በመስጠት ስህተቶች ናቸው ያሏቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርማት እንዲሰጡበት አሳስቧል።

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በካቢኔ ስብሰባው ላይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ቀላል እና በንግግር የሚፈታ ነው በማለት የተደረጉ ሙከራዎች እንዳለ ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቅዱስ ሲኖዶሱ ግን ይህንን በቤተ ክርስቲያኗ “አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና የምታስተላልፋቸውን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ ነው” በማለት እንደተራ ግጭት እና የግለሰቦች አለመግባባት አድርገው ማቅረባቸውን ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የካቢኔ አባላት አንዳችሁም በዚህ ጉዳይ [በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ] እጃችሁን ማስገባት አይፈቀድላችሁም። . . . አንድም ሰው በእዚህ ጉዳይ እጁን እንዳያስገባ” በማለት የሰነዘሩትን ሃሳብንም “መንግሥት ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን ችላ ያለበት ነው” በማለት ተችቷል።

በካቢኔ ስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ መሞከሩን ጠቅሰው የነበረ ሲሆን “ምክራችን አልተደመጠም፤ አልተተገበረም” በማለት፣ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበው “በተለየ የምንደግፈው፣ በተለየ የምንቃወመው ኃይል የለም። ሁለቱም ኃይሎች ኦርቶዶክሶች ናቸው። ሁለቱም ጋር ጥያቄዎች እና እውነቶች አሉ” ብለው ነበር።

ነገር ግን ይህ ሁለቱንም ወገኖች በአቻነት ያቀረቡበትን መንገድ የሲኖዶሱ መግለጫ ተችቶ፣ “በሕጋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተነሱትን ሕገ ወጥ ቡድኖች በአቻ ዕይታ ተመልክተው ሊወያዩ ይገባል በማለት የሰጡት ማብራሪያ ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ፣ ለሕጋዊ ተቋማት መንግሥት ያለበትን የመጠበቅና ዋስትና የመስጠት ኃላፊነቱን ወደ ጎን ያደረገ ነው” ብሏል።

በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት አባላቱ ሊቃነ ጳጳሳት ከአየር ማረፊያ መታገታቸውን እንዲሁም ለሃይማኖታዊ አምልኮ የተሰበሰቡ ምእመናን እንዲበተኑ መደረጋቸውን በመጥቀስ “ለአንድ ሊቀጳጳስ የማይመጥን እንግልት እና ማዋከብ” መድረሱን መግለጫው ጠቅሷል።

በተቃራኒው ደግሞ ቤተክርስቲያኗ ሕገወጥ ያለችው ቡድን አባላት በምዕራብ ወለጋ፤ በምሥራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ እና በሆሮጉድሩ ዞኖች “በኦሮሚያ ክልል የልዩ ኃይል አባላት ልዩ እጀባ እና እንክብካቤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ተቋማት ተደፍረው እንዲገቡ ተደርጓል” በማለት ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ መደረጋቸውን ገልጿል።

ስለዚህም የቤተ ክርስቲያኒቱ የአምልኮ እና የአስተዳደር ተቋማት እንዲሁም ንብረቶች አስፈላጊው ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤ አባቶች እና የአስተዳደር ሠራተኞች የሕይወት ዋስትና እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አሳስቧል።

መግለጫው ጨምሮም የቤተ ክርስቲያኒኗን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ አሠራር በመጣስ “መፈንቅለ ሲኖዶስ” ፈጽመው ተወግዘው ከተለዩት አባቶች ጋር በእርቅ እና ድርድር እንዲደረግ የቀረበው ሃሳብ “ሃይማኖታዊ መመሪያችሁን ጥሳችሁ ቀኖናዊ ሥርዓታችሁን አፍርሳችሁ፤ አስተዳደራዊ መዋቅራችሁን ንዳችሁ ተቀበሏቸው እንደማለት የሚያስቆጥር ነው” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

በአማራ እና በትግራይ ውስጥ የእምነቱ ተከታዮች በቋንቋቸው እንደሚገለገሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ኦሮሚያ ውስጥ በኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎት ይሰጠን ብሎ የሚጠይቅን ምዕመን አይሰጥህም ልለው አልችልም። እኔ አይደለሁም በቋንቋው የመጠቀም መብት ያጎናፀፍኩት” ብለዋል።

ይህንንም በተመለከተ ሲኖዶሱ በሰጠው ምላሽ ቤተክርስቲያኗ “የቋንቋ አገልግሎትን በሕጎቿ እውቅና የሰጠች” መሆኗን በመጥቀስ በተለይ በኦሮምኛ ቋንቋ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በዝርዝር በመጥቀስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቤተክረስቲያኗ “የቋንቋ አገልግሎትን እንደተቃወመች እና በሯን እንደዘጋች የሚያስቆጥር እና ከእውነታው የራቀ ነው” ብሏል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ለቤተክርስቲያኗ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ባብራሩበት ወቅት፣ ከሌሎቹ የዕምነት ተቋማት በብዙ እጥፍ በበለጠ ሁኔታ ባለፉት አራት ዓመታት ሰፊ ይዞታ እንደተሰጣት የገለጹበትን ማብራሪያ መግለጫው “ፍጹም ስህተት ነው” በማለት ተቃውሞታል።

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያገኘችው ይዞታ “ለሌሎች ቤተ እምነቶች በድምሩ ከተሰጠው በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ እና አዲስ ይዞታ እንደተሰጠ ተደርጎ በማስመሰል የተሰጠው ማብራሪያ ፍጹም ስህተት እና ሕዝብን የሚያሳስት በመሆኑ ሊታረም ይገባል” በማለት ይህም በካርታ ተረጋግጦ እንዲሰጥ ስትጠይቅ የቆየች ንብረቷ እንጂ እንደ አዲስ ያገኘችው አለመሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ያሉ አባቶች ከዓመት በፊት በጦርነቱ ወቅት ከማዕከላዊው ሲኖዶስ መለየታቸውን ባሳወቁበት ወቅት አሁን ኦሮሚያ ውስጥ የታየውን አይነት ተቃውሞ አለመቅረቡን አንስተው በካቢኔ ስበሰባው ላይ ተችተው ነበር።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ለዚህም በሰጠው ምላሽ ላይ በትግራይ ያሉት አባቶች “የቤተክርስቲያኗን ሕጎች እና ቀኖናዎች ጥሰው ሕገወጥ ሲኖዶስ አልመሠረቱም፣ ጳጳሳትንም አልሾሙም” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር “አሁን የተፈጸመውን ሕገወጥ ሹመት እና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን እንዲኖረው ለማድረግ” የሚያስመስል እና ሁለቱ የማይገናኙ ድርጊቶችን በንጽጽር መናገራቸው ተቃውሟል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው ላይ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር እና ቤተክርስቲያኗን እንዲጠብቅ መጠየቃቸውን አስታውሶ ነገር ግን “በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉት አካላት” በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ወዳልተፈቀደላቸው የአገልግሎት ቦታዎች በመግባት በቤተክርስቲያኗ ላይ “ሁከት እየተፈጠረ መሆኑን ለመረዳት ችለናል” ብሏል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንግሥት ያቀረበችው ሕግን የማስከበር እና የዜጎችን ሰላም የማስፈን ሥራ ጥሪ ተቀብሎ በሕገወጦች ላይ የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ እንደሌለ በመጥቀስ፣ መንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና በማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ጨምሮም ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የሚሳተፉበት አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ፣ ችግሩ ተፈትቶ “የቤተ ክርስቲያኒቱ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ እስከ ሕይወት መስዋዕትን ድረስ በመክፈል” ችግሯ እንዲታወቅ እንደሚያደርጉ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።