ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ከቤተክርስቲያኗ ተወግዝው እንዲለዩ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Mahibere Kidusan/FB
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ የጵጵስና ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ከቤተክርስቲያኗ ተወግዘው እንዲለዩ ወሰነ።
በፓትሪያርኩ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ካካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በኋላ እንዳስታወቀው በቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመልክቶ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።
ባለፈው እሁድ በሦስት የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት አማካይነት ከአዲስ አበባ ውጪ በተከናወነ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፓትሪያርኩ እና ከቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ 26 ኤጲስ ቆጶሳት መሾማቸው ይታወቃል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ስብሰባም “የተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር በሕገ ሰብእም ሆነ በሕገ እግዚአብሔር ሚዛን የተወገዘ ከመሠረተ እምነት የተለየ፣ በአበው ቀኖና፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በአጠቃላይ ተቀባይት የሌለው ነው” በማለት በሂደቱ በተሳተፉት ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ አሰልፏል።
በዚህም መሠረት ሹመቱን የሰጡት አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣቴዎ እና አባ ዜና ማርቆስ “የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ሥልጣን 26 ኤጴስ ቆጰሳትን በመሾም እና ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለት” ሙሉ ሥልጣነ ክህነታቸው ተሽሮ ተወግዘው ከቤተክርስቲያኗ መለየታቸውን አሳውቋል።
በተጨማሪም “የቅዱስ ሲኖዶሱን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ” ግለሰቦች በኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት 25 መነኰሳትም “በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ” ሥልጣነ ክህነታቸው ተሽሮ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያኗ እንዲለዩ መወሰኑ ተገልጿል።
ነገር ግን ይህ የቤተ ክርስቲያነወ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦች “በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ” ቤተ ክርስቲያኗ በቀኖናዋ መሠረት የምትቀበላቸው መሆኑ ተጠቅሷል።
የቅዱስ ሲኖዶሱ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ሲሆን፣ ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለቤተክርስቲያኗ አባቶች፣ ለምእመናኑ እና ለሌሎችም ምልዕክትና ጥሪ አስተለልፏል።
ባለፈው እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. ወሊሶ አቅራቢያ በምትገኝ አንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለ26 ጳጳሳት የተሰጠው ሲመት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ውዝግብ እና ቁጣን አስከትሏል።
በዚህም ሳቢያ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ ድርጊቱ ከቤተክርስቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት ውጪ የተፈጸመ ጥፋት መሆኑን በመግለጽ፣ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት በአገሪቱ ውስጥ እና በመላው ዓለም የሚገኙ ጳጳሳት ወደ አዲስ አበባ በአስቸኳይ እንዲመጡ ጠርተዋል።
በዚህም መሠረት ረቡዕ ዕለት ከሰዓት በፀሎት የተጀመረው የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጽመዋል በተባሉት አባቶች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ጉባኤውን ሐሙስ ዕለት አድርጎ ውሳኔውን አሳውቋል።
በድንገት በዋናነት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲሁም በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ያገለግላሉ ያሏቸውን ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾም የውዝግቡ መነሻ የሆኑት አባቶች፣ ቤተክርስቲያኗ አካታች አይደለችም ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነቱን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም በማለት እርምጃውን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
ይህ ውሳኔያቸውም በቅዱስ ሲኖዶሱ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ ሲኖዶስ ማቋቋም እና ጳጳስ እስከ መሰየም የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ ያሳወቁ ሲሆን፣ ድጋፍም ተቃወሞም እየቀረበባቸው ይገኛል።
ከሕግ ውጪ ተደረገ በተባለው ሂደት ከተሰየሙት ጳጳሳት መካከል አንደኛው ይቅርታ በመጠየቅ መመለሳቸውን የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አስካሁን በግለሰብ ደረጃ ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት በክስተቱ ላይ አስተያየት የሰጡ ቢሆንም፣ ከመንግሥት በኩል ግን ምንም አይነት አስተያየት አልተሰጠም።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ እና የቤተክርስቲያኗን ንብረቶች እንዲሁም መገልገያዎችን በማስከበር በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ጥሪ ቀርቧል።












