የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሊቃነ ጳጳሳቷ አስቸኳይ ጥሪ አቀረበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ተሰጥቷል የተባለውን የጳጳሳት ሹመትን በተመለከተ የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ጥሪ አቀረቡ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም እሁድ ከሰዓት በኋላ በቤተክርስቲያኗ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ስለተከሰተው ሁኔታ ለመነጋገር በተለያዩ አካባቢዎች ላሉ ጳጳሳት፣ ለመንግሥት እና ለምዕመናን ጥሪ አቅርበዋል።
አቡነማቲያስ እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. ጠዋት ተሰማ ባሉት “ሕገ ወጥ ሲመተ ጳጳሳት” ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ በሕገ ወጥነት የተከናወነ መሆኑን በመግለጽ በዚህ ዙሪያ ቤተክርስቲያኗ የምትወስደውን ቀጣይ እርምጃ በተመለከተ ተናግረዋል።
በዚህም በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ምዕመናን ቤተክርስቲያኒቷን በንቃት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
በተጨማሪም መንግሥት “ክስተቱ በአገር ላይ ጭምር የሚያስከትለውን ጉዳት ተመልክቶ” በጉዳዩ ላይ ሕጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ፓትሪያርኩ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመግለጫው ላይ ክስተቱ የቤተክርስቲያኗን አንድነት የሚያናጋ ሕገወጥ ሲመት መፈጸሙን “ታላቅ ሐዘን” እንደፈጠረ ተናግረዋል።
አክለውም የተፈጠረው ሁኔታ “የውስጥ ፈተና” መሆኑን ከማመልከት ባሻገር “የጳጳሳት ሹመቱ” በማን፣ እንዴት እና የት እንደተፈጸመ ከሁለቱም የቤተክርስቲያኗ አባቶች የተሰጠ ዝርዝር ነገር የለም።
ቢቢሲ ተከሰተ ስለተባለው ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ቢጠይቅም በደፈናው ከሚሰማው ነገር ውጪ አስተማማኝ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን ከተከሰተው ሁኔታ አንጻር መረጃውን የሚያውቁ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ በእርግጥም ከቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ የጳጳሳት ሹመት ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ውስጥ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።
ይህም የሆነው በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ሶዶ ዳጬ ወረዳ ሐሮ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ውስጥ እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. ጠዋት የጳጳሳት ሹመት መሰጠቱን አንድ ምንጭ መረጃው እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይም “የጳጳሳቱን የሹመት ሥነ ሥርዓተ” የሚያሳዩ እና “አዲስ ተሾሙ ናቸው የተባሉትን ጳጳሳት” የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እሁድ ከሰዓት ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ሹመቱን ከፈጸሙ እና በጉዳዩ ውስጥ ከተሳተፉት ወገኖች ስለሁኔታ ምንነት እና ስለተከናወነው ሥነ ሥርዓት በይፋ ሳይገልጽ ቆይቶ፣ እሁድ ምሽት ተሾሙ የተባሉት ጳጳሳት በተገኙበት ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል።
ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እና ደንብ ውጪ የጳጳሳት ሹመትን ፈጽመዋል የተባሉት አባቶች ሰጡት በተባለ የቪዲዮ መግለጫ ላይ እሁድ ምሽት ቀርበው ክስተቱን አረጋግጠዋል።
ሦስት አባቶች ከፊት በመሆን በተነበበው መግለጫ ላይ አሁን ባለው የቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ ውስጥ “በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር አልቻልንም፣ ሲኖዶሱ ከአንድ አካባቢ ብቻ የተዋቀረ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ምዕመናን በአፍ መፍቻቸው ቋንቋቸው ወንጌልን ለመማር እና ሥርዓትተ አምልኮ፤ ለመፈፀም እንዲሁም ለመገልገል እና ለማገልገል ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤት ድረስ ጥያቄ ቢቀርብም” ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን አሉ ላሏቸው የቤተ ክርስቲያኗ ችግሮች እና የአሰራር ክፍተቶች ላለፉት 60 ዓመታት መቆየታቸውን በመጥቀስ ይህም “ለምዕመናን እምነት መዳከም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንዳደረገ እና ሕዝቡን የቅድስት ቤተክርስቲያን ባይተዋር አድርጓት ቆይቷል” ብለዋል።
በመግለጫው ላይ በአገረ ስብከቶች የጳጳሳት ሹመት ላይ ቅሬታ እንዳላቸው አመልክተው በተለይ የቋንቋን ጉዳይ አንስተዋል “ሁሉም በሚባል ደረጃ ከአንድ ወገን ብቻ በመመደብ ከምዕመናን ጋር በቋንቋ እና ባሕል ሳይግባቡ በመቅረታቸው በርካታ ምዕመናን ባለፉት ዘመናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስትያንን ለቅቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።"
እንዲህ ያለው ሁኔታ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲሁም በደቡብ አካባቢ እንዳለ የገለጹት አባቶቹ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በክልሎቹ የመቀጠል አደጋ ተጋርጦባት እንደሚገኝ ስለተገነዘብን የጠፉትን ለመሰብሰብ ያሉትን ለማጽናት ሲባል እኛ እና መንፈስ ቅዱስ ይህንን ታሪካዊ ውሳኔ ወስነናል” ብለዋል።
ውሳኔያቸውም “አሁን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ከ85 በመቶ በላይ ከአንድ ወገን ተዋቅሮ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ሲኖዶስ ነው ብሎ መቀበል ባለመቻሉ ሁሉንም የአገሪቱን ሕዝቦች ያቀፈ ቅዱስ ሲኖዶስ" አቋቁመው በይፋ ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ለ26 የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች የተለያዩ ሹመቶችን የሰጡ ሲሆን፣ ተሾሚዎቹ ያገለግሉባቸዋል ያሏቸው ቦታዎች አብዛኞቹ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ የደቡብ ክልል አካባቢዎችም ተካተውባቸዋል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዘር ለመክፈል የተኬደው ርቀት አደገኛም አሳዛኝም ነው” በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ጨምረውም “ሕገ ወጥ የጳጳሳት ሹመት ገጠር ውስጥ ተደብቆ በመፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ኃጢአት ተሠርቷል” ክስተቱን ለማስቆም የሚችሉ አካላት “ለማስቆም ባለመፈለጋቸው በሰማይም በምድርም ተጠያቂ ናቸው” ሲሉ በውል ያልጠቀሷቸውን አካላት ወቅሰዋል።
እንዲሁም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) “ከአንዱ የቤተክህነታችን ክፍል ዛሬ የሰማነው ድርጊት አሳዛኝ ዜና ነው” በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ከምድራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ትውፊት እና ቀኖና ጋር የሚጋጭ የትኛውም ድርጊት መጨረሻው የሰመረ ሊሆን አይችልም” በማለት አባቶች በትዕግሥት እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ችግሩን ይፈቱታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ፓትሪያርኩ ጉዳዩን በተመለከተ ባስተላለፉት ጥሪ መሠረት በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት በቀጣይ ቀናት የሚሰበሰብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ውሳኔም ያሳልፋል ተብሏል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የኦሮሚያ ክልል ቤተክህነትን የመመሥረት እንቅስቃሴ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፣ ጉዳዩ በስፋት መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል ውይይቶች ተደርጎ እልባት እንደተሰጠው መገለጹ ይታወሳል።












