አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ውይይት አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአገሪቱ ስላሉ ጉዳዮች መነጋገራቸውን የቃል አቀባያቸው ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ቅዳሜ ጥር 13/2015 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በውጭ ጉዳይ ኃላፊው መካከል በተደረገው ውይይት ላይ ዋነኛው ጉዳይ የነበረው በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ባስቆመው ስምምነት ትግበራ ላይ ነው።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አጠቃላይ ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ቃል አቀባይ እንዳለው በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ግጭትን የማቆም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ወታደሮች መውጣት መጀመራቸውን ጨምሮ የስምምነቱ ትግበራን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት መነሳቱ ተገልጿል።
በሁለቱ ባለሥልጣናት መካከል ውይይት ስለመደረጉ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን የተባለ ነገር የለም።
የሁለቱ ባለሥልጣናትን ንግግር በተመለከተ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ጦርነቱን ለማስቆም ከተደረሰው ውሳኔ በኋላ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት “ከፍተኛ እርምጃ” እያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሷል።
አንቶኒ ብሊንከን እየታዩ ያሉት እርምጃቻዎችን በበጎ እንደሚቀበሏቸው በመጥቀስ፣ እነዚህም በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፍን ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለመመርመር እንዲቻል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ እንድትፈቅድ ብሊንከን ጠይቀዋል።
የተባባሩት መንግሥታት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን ማቋቋሙ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ባወጣው ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር።
መርማሪ ቡድኑ ሲቋቋም ጀምሮ ተቃውሞውን ያሰማው የኢትዮጰያ መንግሥት በተፈጸሙ በደሎች ዙሪያ ተጠያቂነትን ለማስፈን የራሱን የሽግግር ፍትህ ሥርዓት ዘርግቶ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን በመግለጽ የሌሎችን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበል አሳውቆ ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አገራቸው በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሰሜን ኢትዮጵያው የሰላም ሂደት ድጋፏን እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን የቃል አቀባዩ መግለጫ አመልክቷል።
አሜሪካ በትግራይ የተካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ልዩ መልዕክተኛ በመሰየም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ጥረት ስታደርግ መቆየቷ የሚታወስ ሲሆን፣ በሂደቱ ከፍተኛ ሚና እንደነበራት ይነገራል።
በተያያዘም የውጭ ጉዳይ ኃላፊው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ውይይት ላይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለቀጠለው አለመረጋጋት አንስተው መወያየታቸው ተጠቅሷል።
ባለፉት ዓመታት በምዕራብ እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ከሚንሳቀሰው መንግሥት ሽብርተኛ ቡድን ብሎ ከሰየመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር እየተካሄደ ባለው ግጭት እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው።
ባለፉት ወራትም በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ በመሄዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ለሞት ተዳርገው፣ በአስር ሺዎች ደግሞ መፈናቀላቸው የሚወጡ ሪፖርቶች አመክልተዋል።
የፈደራል መንግሥቱ እና የክልሉ መስተዳደር ከቀናት በፊት እንዳሉት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ላለው አለመረጋጋት “ሁሉንም አይነት አማራጮች” ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀው ነበር።
በዚህም ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ለሚፈልጉ ታጣቂዎች የመንግሥት በር ክፍት መሆኑን ከዚህ ውጪም የሚንሳቀሱ ካሉ የፀጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ማሳወቁ ይታወቃል።












