መንግሥት ‘በሸኔ ላይ ሁሉንም አማራጮች ያካተተ እርምጃ’ እየወሰደ እንደሚገኝ ገለጸ

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Government Communication Service/fb

የምስሉ መግለጫ, የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

መንግሥት ሸኔ የሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ‘ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ያካተተ እርምጃ’ እየወሰደ እንደሚገኝ ገለጸ።

የኢትዮጵያ መንግሥትኮሚዩኒኬሽን በሰጠው መግለጫ በታጣቂ ቡድኑ የታጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ አማራጮችን እየተጠቀመ መሆኑን አስታውቋል።

በሽብር ቡድንነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ እና በአጎራባች አካባቢዎች እንዲሁም በአጠቃላይ በአገር ደረጃ የፈጠረውን የሰላም ስጋት ለመግታት “ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የተቀናጀ አንቅስቃሴ” እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው ቡድን እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች ወደነበሩበት ሰላማዊ የሆነ ማኅበራዊ እና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እንዲመለስ “የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ግብረ ኃይል ተደራጅቶ. . . ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ያካተተ እርምጃ” እየተወሰደ ይገኛል ሲል ገልጿል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ረቡዕ ጥር 10/2015 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ሸኔ በንፁሃን ሕይወት እና ንብረት “የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ” ይገኛል።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የፖለቲካ እና የሰላም ጥረቶች መደረጋቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ጥረቶች “የመጀመሪያ እርምጃ ተደረግው በመንግሥት በኩል ተወስደዋል” ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከሆነ ከዚህ ቀደም ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ያደረገው ጥረት ያልተሳካው በዋነናነት “በሸኔ መሠረታዊ ችግር ምንክንያት ነው።”

“ሸኔ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ እኩይ ድርጊቱን እንዲያቆም እና የኦሮሞ ወጣት እልቂት ማብቂያ እንዲያገኝ መላው ሕዘብ ግፊት ማድረግ አለበት” ብለዋል።

መንግሥት በኦሮሚያ ከሚገኙ አመራሮች እና ከሕብረተሰቡ ከተውጣጡ አካላት እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር “የሰላም አማራጭ ላይ” ውይይት እያካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ወጣቶች በሰላም ለመንግሥት እጃቸውን ሰጥተው የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ “የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መንግሥት እየሠራ” መሆኑንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

በዚህም በርካታ ወጣቶች እጃቸውን ለመንግሥት እየሰጡ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ሁኔታዎች መንግሥት የኃይል እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኸነዋረዊዎች ጋር ሲወያዩ

የፎቶው ባለመብት, BKO

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ከወለጋ ነዋሪዎች ጋር ምን ተወያዩ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን የሸኔ ታጣቂዎች ወደሚንቀሳቀሱበት የወለጋ ዞኖች በመጓዝ ከሕዝቡ ጋር ውይይት አካሂደዋል።

ፕሬዝዳንቱ በምስራቅ ወለጋ ነቀምት፣ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ፣ በቄለም ወለጋ ደግሞ ደምቢዶሎ በመገኘት ከሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

ከመንግሥት ጋር እየታገለ የሚገኘው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በስፋት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በእነዚህ ዞኖች ውስጥ ነው።

ፕሬዝዳንት ሽመልስ ከአካባቢው ማሕብረሰብ ጋር በሰላም እጦት፣ በመሰረተ ልማቶች ግንባታ እና በስራ አጥነት ዙሪያ መወያያታቸውን የቄለም ወለጋ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሶ ዳባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ በዳሶ የደምቢዶሎ ከተማ አየር ማረፊያ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሙሉ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሳይሰጥ መቆየቱን ያነሳሉ።

ከፕሬዝዳንት ሽመልስ ጋር በነበረው ውይይትም ይህ ጉዳይ እንደተነሳ እና መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስራ ለማስጀመር ቃል መግባቱን አቶ በዳሶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዞኑ የመብራት የውሃ እና የመንገድ አገለግሎቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አንዳነሱ አቶ በዳሶ ጨምረው ያብራራሉ።

መንግሥትም ለእነዚህ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ መናገራቸውን አቶ በዳሶ ያብራራሉ።

“ከሁሉም በላይ በዞናችን አስተማማኝ ሰላም ማምጣት እንዳለበት ተወያይተናል። ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን እንዲቆም እና መንግሥትም የሕዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ እንዲሰራ ተወያይተናል” ይላሉ አቶ በዳሶ።

በነበረውም ውይይት ሕዝቡ አበክሮ ያነሳው ነገር መጀመርያ ሰላም መረጋገጥ እንዳለበት መሆኑን አቶ በዳሶ ተናግረዋል።

“እስከመቼ ከሰው በታች እንሆናለን። እስከ መቼ በኢኮኖሚ እንጎዳለን የሚሉትን ችግሮች ተሳታፊዎች አንስተዋል” ይላሉ አቶ በዳሶ።

አቶ በዳሶ አክለውም ፕሬዝዳንት ሽመልስ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ለመግባት የሚፈልጉትን ታጣቂዎች መንግሥት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

“መንግሥት በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ ገብተው፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል። አሁንም ቢሆን በሰላማዊ መንግድ ከሚገቡት ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን አቶ ሽመልስ አንስተዋል” ይላሉ አቶ በዳሶ።

“በሰላማዊ መንድ የሚገቡትን እንቀበላቸዋልን እምቢ ያሉትን ደግሞ የሕግ የበላይነት ማስከበር ግድ ስለሆነ መንግሥት ኦፕሬሽን ያካሄዳል” ፕሬዝዳንቱ ማለታቸውን አቶ በዳሶ ተናግረዋል።

አቶ በዳሶ ዞናቸው አሁን ያለበትን ሁኔታ ሲያስረዱ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የቁጥጥር ስር ያለ ምንም ዓይነት ወረዳ እንደሌለ ተናግረዋል።

“በምን ኃይላቸው ነው ተቆጣጥረው የሚቆዩት ከተማ ከገቡም ከአንድ ሰዓት በላይ አይቆዩም። ዘርፈው ነው የሚወጡት ተቆጣጥረው የቆዩት ቦታ የለም።”

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በሚፈጠሩ ሁከቶች ዋነኛ ተሳታፊዎች መንግሥት ‘ሸኔ’ እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የአማራ ታጣቂዎች ናቸው ማለቱ ይታወሳል።

ላለፉት አራት ዓመታት በመንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ሸኔ) መካከል በተደረጉ ግጭቶች ሳቢያ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል፤ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።