በምዕራብ ጉጂ ከማረሚያ ቤት ያመለጡ ከ400 በላይ እስረኞችን ለመያዝ አሰሳ እየተደረገ ነው

ጦር መሳሪያ ያነገቡ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው ከእስር ቤት ያስመለጧቸውን ከ400 በላይ እስረኞችን መልሶ ለመያዝ አሰሳ እየተደረገ መሆኑን የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከአንድ ሳምንት በፊት ጥቃቱን የፈጸሙት መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው እና በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ በሆሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በሚገኝ ማረሚያ ቤት ላይ ተኩስ ከፍተው አምስት የፖሊስ አባላትን ከገደሉ በኋላ እስከ 480 የሚደርሱ እስረኞችን አስመልጠው ነበር።

የዞኑ ዋና ከተማ ቡሌ ሆራ ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ጊርጃ ኡራጎ ለቢቢሲ ሲናገሩ ከማረሚያ ቤት ያመለጡ እስረኞችን መልሶ ለመያዝ “የመንግሥት ፀጥታ ኃይል አሰሳ እያካሄደ በማሳደድ ላይ ነው” ብለዋል።

ከእስር እንዲያመልጡ የተደረጉት የሕግ ታራሚዎች በተለያዩ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው የቅጣት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ የነበሩ ናቸው።

ካመለጡት መካከል ሽብርተኛ ተብሎ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈረጀው የዚሁ ቡድን አባላት ይገኙበታል።

ከቡሌ ሆራ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የዞኑ ማረሚያ ቤት ላይ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈጸሙት በገና በዓል ዕለት ቅዳሜ ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም. ነው።

ታጣቂዎቹ ተኩስ ከከፈቱ በኋላ አምስት የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት እና አንድ የአካባቢው ነዋሪን መገደላቸውን እና ሁለት ሰዎች ማቁሰላቸውን ምክትል ከንቲባው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በማረሚያ ቤቱ ላይ ጥቃት በተሰነዘረ ወቅት ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የአከባቢው ባለሥልጣናት ጥቃቱን የፈጸሙት ሸኔ ብለው የሚጠሯቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ናቸው ቢሉም፣ ታጣቂዎቹ እስካሁን እስረኞችን ስለማስመለጣቸው ያሉት ነገር የለም።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም የታጣቂ ቡድኑ አባላት ‘የፖለቲከኛ እስረኛ ያሏቸውን’ ታራሚዎች በደቡብ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች አስመልጠው ነበር።

የቡሌ ሆራ ምክትል ከንቲባ አቶ ጊርጃ ኡራጎ በማረሚያ ቤቱ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ “ሁሉም ታራሚ ማምለጡን” ተናግረዋል።

“ሁሉም ናቸው የወጡት። እስከ 480 እስረኞች ይሆናሉ ብለን እንገምታለን። አሁን ላይ በዚያ ማረሚያ ቤት ውስጥ ታስሮ የሚገኝ ትክክለኛ የታራሚ ቁጥር የለንም። ነገር ግን ያመለጡት ከ400 በላይ ይሆናሉ” ብለዋል።

በማረሚያ ቤት ላይ ጥቃት በመክፈት እስረኞችን የማስመለጡ ዜና የተሰማው መንግሥት ሸኔ በሚለው ታጣቂ ቡድን ላይ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን እየገለጸ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነው።

ባለፈው ሳምንተ የአገር መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ እና ምሥራቅ ጉጂ እንዲሁም በቦረና ዞኖች በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የነበሩ አካባቢዎች ነጻ ማውጣቱን ገልጾ ነበር።

መንግሥት የታጣቂ ቡድኑን ለማጥፋት በሚል በሚወስዳቸው እርምጃዎች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ተጎጂ ስለመሆናቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።