በዓለም ዙሪያ የኦቲዝም ክስተት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

እናት እና ልጅ ቁጭ ብለው ከውሻቸው ጋር ሲጫወቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኦቲዝም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እየታወቀ እንዲሁም ሰዎች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ ነው።

ይህ ግን ኦቲዝም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤም ፈጥሯል።

ሻነን ዴስ ሮቼስ ሮዛ ልጇን ኦቲዝም ያስመረመረችበትን ጊዜ በማስታወስ ዕድለኛ እንደሆነች ትናገራለች።

የኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር (ASD) በግለሰቦች እና በቡድኖች መካከል በጣም ሊለያይ ይችላል።

ብዙውን ጊዜ የሴቶች ምልክቶች ከወንዶች ይለያል።

ሊዮ ገና በልጅነቱ የሌሎችን ዓይን ማየት ይፈራል።

በመዋዕለ ሕፃናት በሚማርበት ወቅት እንደ ሌሎች እኩዮቹ ለንግግር ምላሽ አይሰጥም።

እጆቹን ማወዛወዝ እና ልብሱን ማኘክ አዘውትሮ የሚያሳያቸው ባህሪያት ነበሩ። በቀላሉ ይጨናነቃል፤ ይረበሻል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003፣ በሁለት ዓመቱ፣ ምርመራ ሲደረግለት ስለ ጤና ሁኔታው ለማወቅ አስቸጋሪ አልነበረም።

ሮዛ በቀጣይ ማድረግ ስላለባት ነገር ተገቢውን መመሪያ አልተሰጠችም።

በካሊፎርኒያ የምትኖረው እና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ሮዛ "በጣም ግራ የመጋባት ስሜት ተሰማኝ" ስትል ትናግራለች።

"በእውነት ተናድጄ ነበር" እንደሌሎች ብዙ ወላጆች ከምንም በላይ ማወቅ የፈለገችው ልጇ ለምን ኦቲዝም እንዳለባት ነው። በኦንላየን ላይ እንደ እርሷ በግራ መጋባት ውስጥ ያሉ እና ተመሳሳይ መልስ የሚፈልጉ ወላጆችን አገኘች።

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በክትባት ምክንያት ለዚህ ሁኔታ እንደተጋለጡ ያምኑ ነበር።

በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ሕጻናት ላይ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች በክትባት እና በኦቲዝም መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት አላገኙም።

ያ ብቻም ሳይሆን የተከተቡ ሕጻናት ካልተከተቡት የበለጠ በኦቲዝም የመያዝም ዕድል የላቸውም። ነገር ግን ሊዮ ለምን የኦቲዝም ተጠቂ እንደሆነ በግልጽ ሳትረዳ፣ ሮዛ ሌሎች ልጆቿን ላለማስከተብ ወሰነች።

ዓመታትን በፈጀ ሂደት ሮዛ እንደተሳሳተች ተገነዘበች።

ሮዛ በክትባት ላይ ያላትን ተቃውሞ ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ለመርዳት የኦቲዝም ግንዛቤ የሚሰጥ ድረ ገጽ ጀመረች።

"በዚህ ነገር ለሚያምኑ ሰዎች አዝናለሁ ምክንያቱም እኔም እንደርሱ ስለነበርኩ" ትላለች። "አሁን ግን ያ የተሳሳተ መረጃ መሆኑን አውቄያለሁ።"

ይህ የሮዛ ታሪክ የኦቲዝም ምርመራን ተከትሎ አንዳንድ ቤተሰቦች ግልጽ የሆኑ መልሶችን ምን ያህል እንደሚፈልጉ ማሳያ ነው።

በጥር ወር አካባቢ የአሜሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር ከመስከረም 2025 በፊት የኦቲዝም "ወረርሽኝ" ሲሉ የጠሩትን ለመረዳት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶችን ያሳተፈ "ትልቅ" የምርምር ጥረት ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን በኦቲዝም ላይ የተደረጉ አሥርት ዓመታት የፈጁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት መንስኤዎቹ ውስብስብ እና በአብዛኛው በዘር የሚተላለፉ ናቸው።

ኦቲዝም የነርቭ ዕድገት መዛባት ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ የአስተሳሰብ መንገድን፣ የስሜት ሕዋሳት ሂደትን፣ የግንኙነት እና የማኅበራዊ መስተጋብር ልዩነቶችን ያካትታል።

ምንም እንኳን ብዙ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ በቂ መረጃ ባይኖርም የኦቲዝም ሥርጭት በተጠናባቸው አገራት ከ1 በመቶ እስከ 3 በመቶ ይገመታል ።

ይህንን መረጃ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲከታተሉ በነበሩ አገራት፣ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የኦቲዝም ምርመራዎች የማያቋርጥ ዕድገት አሳይተዋል።

በጤና እና በትምህርት መዛግብት መሠረት ከ2000 እስከ 2022 (እአአ) በአሜሪካ የኦቲዝም ሥርጭት ከ150 ሰው አንድ ሰው ወደ ከ31 ሰው አንድ ሰው አድጓል።

በአውስትራሊያ፣ በታይዋን እና በሌሎች አገራት የሥርጭት መጠኑም ከፍ ብሏል።

"ይህ [የስታቲስቲክስ አውድን] ለማያውቁ ሰዎች አስደንጋጭ ሊመስል ይችላል" ይላሉ የኦቲስቲክ ሰዎች መብት ተሟጋቹ ዞይ ግሮስ።

"የኦቲዝም ጉዳዮች እየጨመሩ ሄደው አይደለም፣ ይልቁንም ምርመራዎች ናቸው የጨመሩት" ሲሉ ያብራራሉ።

ካለፉት 45 ዓመታት ወዲህ የኦቲዝምን የመመርመሪያ መስፈርት በአግባቡ እየደረጀ መጥቷል።

በአውሮፓውያኑ 2013 በተለይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ኦቲዝም እና ሌሎች ተመሳሳይ የዕድገት እና የባህሪይ ውስንነት ስር ያሉ ንዑስ ምድቦችን ዘርዝሮ አስቀምጧል።

ከዚህ ቀደም የኦቲዝም ምርመራ ያላደረጉ ሰዎች አሁን መስፈርቶቹን የማሟላት ዕድላቸው ሰፊ ነው።

በአሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ እና በተለያየ ምክንያት በታሪክ ችላ ተብለው በሚታለፉ ቡድኖች ውስጥ የመመርመሪያ ልዩነቶች እየጠበቡ መጥተዋል።

በእርግጥ ዛሬም ቢሆን፣ አንድ ሰው በሚኖርበት አካባቢ የተነሳ የሚያገኘው ምርመራ መጠን በጣም ሊለያይ ይችላል።

ለምሳሌ፣ ኦቲዝም በቴክሳስ በሚያዝያ 2025 ከ1 በመቶ ባነሱ የ8 ዓመት ሕጻናት ውስጥ ታይቷል።

ነገር ግን በካሊፎርኒያ ከ5 በመቶ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ዘንድ የተደራሽነት ልዩነት መኖሩ ተመዝግቧል።

የኦቲዝም ምርመራዎች ከመንግሥት ጥቅማ ጥቅሞች ለማግኘት ወይም ለፈተናዎች ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ስለሚረዱ ባለፉት አስርት ዓመታት ከነበሩት ይልቅ በርካቶች ምርመራ ማድረግ የመፈለግ ዝንባሌ አሳይተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኦቲዝም ምርመራዎች ይበልጥ እየተሻሻሉ በመምጣታቸው ብዙ ሕጻናት ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት በተሻለ ቀደም ብለው እየተመረመሩ እና ያሉበትን ደረጃ እያወቁ መጥተዋል።

በኦቲዝም ተጠቂዎች ላይ የሚደርሰው መገለል ቀስ በቀስ እየቀነሰ መምጣቱ በሕጻናት እና ጎልማሶች ዘንድ ምርመራ ለማድረግ የመፈለግ ግንዛቤን አሳድጓል።

የሕብረተሰቡም ሆነ የጤና ባለሙያዎች ስለ ኤኤስዲ መገለጫዎች የበለጠ ግንዛቤ አግኝተዋል።

በተለይም ሰዎች ኦቲዝም ሊታዩ ስለሚችሉባቸው የተለያዩ መንገዶች የተሻለ ግንዛቤ አላቸው።

"ባለፉት ዓመታት ያልታወቁ ምናልባትም ብዙም የድጋፍ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎችን" ጨምሮ ሲል ግሮስ ሃሳቡን ያጠናክራል።

ይህ በብዙ የዓለም ክፍሎች እውነት ነው። በኮሪያ የሕጻናት ማኅበራዊ ልማት ተቋም ዋና የምርመራ ባለሙያ ዩን-ጁ ኮህ እንዳለችው በኮሪያ ብዙ ወላጆች ስለ ኤኤስዲ ከማኅበራዊ ሚዲያ እየተማሩ ወደ ክሊኒኳ ቀድመው መምጣት ጀምረዋል።

ይህ ሁሉ ማለት ተደብቀው የሚቀሩ የኦቲዝም ተጠቂዎች ጥቂት ይሆናሉ ማለት ነው።

"የኦቲዝም ተጠቂዎች ሁልጊዜም በዙሪያችን ነበሩ" ትላለች ሮዛ። "ነገር ግን ምን ያህል እንደሆኑ በትክክል በደንብ ለይተን አናውቅም ነበር።"

በኦቲዝም የተጠቃ ልጅ ያላቸው ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከዘር የሚውረስ ይሆን?

በስቶክሆልም እና በኒውዮርክ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የስታቲስቲክስ እና የሥነ አእምሮ ባለሙያ የሆነው ስቬን ሳንዲን ኦቲዝም በዘር የሚተላለፍ ነው ይላል።

ይህም ማለት በዘረ መል ምክንያቶች ነው፣ ነገር ግን በጣም ውስብስብ በሆነ ምክንያት የሚከሰት የዕድገት ዕክል ነው።

ሳንዲን በአምስት ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ባደረገው ምርምር ኤኤስዲ 80 በመቶው በዘር የሚተላለፍ መሆኑን አረጋግጧል።

ያም ማለት ምርመራ ካደረጉት በግምት 80 በመቶ የሚሆኑት የኤኤስዲ ተጋላጭነቶች በጄኔቲክ ልዩነት የተከሰቱ ናቸው።

በሌላ አነጋገር ዘረመል ከአብዛኞቹ የኤኤስዲ ጉዳዮች ጀርባ አለ ማለት ነው።

ሳንዲን በስዊድን ባደረገው ጥናት በተለይ በወንዶች መካከል 87 በመቶ እና በሴቶች 75.7 በመቶ በዘር የሚተላለፍ መሆኑን አረጋግጧል።

ነገር ግን ከምርምር ሥራው ግልጽ የሚመስለው ኦቲዝም በቤተሰብ ውስጥ እንደሚኖር ነው።

ወንድማቸው ወይም እህታቸው ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች፣ ወንድም እህቶቻቸው ኦቲዝም ከሌለባቸው ልጆች ጋር ሲነጻጸሩ ራሳቸው ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድላቸው 10 እጥፍ ሆኖ ተገኝቷል።

በአንድ ወገናቸው ወንድም ወይም እህት ብቻ ኦቲዝም ካለባቸው ደግሞ ለዕክሉ የመጋለጥ ዕድላቸው ሦስት እጥፍ ይሆናል።

ተመሳሳይ መንትዮች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንዱ ልጅ ኤኤስዲ ካለበት ከ65 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ሌላኛው መንትያም ይኖርበታል።

ነገር ግን ኦቲዝም በዘር የሚተላለፍ መሆኑን ማወቅ አንድ ዘረ-መል (ጂን) ላለው ሁሉ ተጠያቂ ነው ማለት አይደለም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ከ100 በላይ ጂኖች ከኦቲዝም ምርመራ ጋር የተወሰነ ግንኙነት እንዳላቸው ተለይተዋል።

ምንም እንኳን እነዚህ ለኦቲዝም ብቻ የተወሰነ ባይሆኑም እና ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር የሚገናኙም አሉ።

አልጋ ላይ ተኝተው መጽሀፍ የሚያነቡ እናት እና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአካባቢ ሚና

ዘረ መል ብቻ ለሁሉ ነገር ተጠያቂ ነው ማለት አይደለም።

"ያለው አጠቃላይ እምነት… እጅግ በጣም ብዙ የተለያዩ ጂኖች እና በጣም ውስብስብ የጄኔቲክ መዋቅሮች እንዳሉ እና ምናልባትም [ኦቲዝምን] ለመቀስቀስ አካባቢያዊ ተፅእኖዎች ጋር የተገናኙ መሆናቸው ነው" ይላል ሳንዲን።

የጎደሉትን ነጥቦች ለመጠቆም፣ ተመራማሪዎች የተለያዩ የባህሪ እና የአካባቢ አጋላጭ ነገሮችን መርምረዋል።

አንዳንድ ማብራሪያዎች ውድቅ ተደርገዋል፣ ለምሳሌ ሳንዲን ወላጆች የሚጠቀሟቸው አንዳንድ ፀረ-ድብርት መድኃኒቶች በልጆች ላይ ከኦቲዝም ጋር የተቆራኙ ናቸው የሚለውን ሀሳብ አጠራጣሪ ነው ይላል።

ከፍተኛ የሆነ ኦቲዝም ሊያጋጥማቸው የሚችል ልጆች በዕድሜ ከፍ ካሉ ወላጆች በሚወለዱበት ወቅት ነው።

በተጨማሪም፣ ለፀረ-ተባይ እና ለአየር ብክለት የተጋለጠ አካባቢም የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አንዳንድ ጥናቶች በተጨማሪም በወሊድ መካከል ያለ ክፍተት እና እንደ የስኳር በሽታ፣ ማጨስ እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት ከእናቶች የጤና ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ህመሞች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ነገር ግን እነዚህ ከኦቲዝም ጋር አያይዞ በቀጥታ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ለማስረዳት ከባድ ነው።

ከእነዚህ አካባቢያዊ ጉዳዮች ውስጥ ቢያንስ አንዳንዶቹ፣ ምናልባትም ጥቃቅን አስተዋጽኦ ኖሯቸው በጋራ ሲደመሩ የበለጠ ተጽዕኖ ኖሯቸው ሊሆን ይችላል።

በአጠቃላይ ግን አብዛኛዎቹ የአካባቢ ሁኔታዎች መደምደሚያ ላይ ከመድረሱ በፊት የበለጠ ምርምር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይስማማሉ።

ሙሉ በሙሉ ውድቅ የተደረገው ግን ከክትባት ጋር ተያይዞ ያለ ለኦትዝም ተጋላጭነት ነው።

ይህ ለብዙዎች እርካታ አይሰጥም ይላል ግሮስ። "ብዙ ሰዎች ቀላል ማብራሪያ ይፈልጋሉ። በተለይ በኦቲዝም ምክንያት መገለል ሲገጥማቸው፤ ምናልባትም ስለ ልጃቸው የአካል ጉዳት ብዙ አሉታዊ ነገሮች ሲሰሙ ማብራሪያ ብቻ ሳይሆን ተወቃሽ የሚያደርጉት ይፈልጋሉ።"

የተፈጠረው ክፍተት ቀለል ያሉ ሀሳቦች በተደጋጋሚ ውድቅ የተደረጉ እና ማስረጃ የሌላቸው ነጥቦችን ጨምሮ እንዲሠራጭ ዕድል ፈጥሯል።

ሮዛ በበኩሏ እውነተኛው ቀውስ ኦቲዝም ሳይሆን እንክብካቤ እና ድጋፍ ነው ትላለች።

ሊዮ ዛሬ የ24 ዓመቱ ሲሆን የእግር ጉዞ ማድረግ እና ፒዛን ይወድዳል።

ሮዛ ልጇን ለመደገፍ መንገዶችን መፈለግ ስትቀጥል፣ ተመራማሪዎች የኦቲዝምን ሳይንስ መፈተሻቸውን ይቀጥላሉ።