የአማራ ልዩ ኃይል ከሽረ እንዳሥላሴ እና አካባቢው መውጣቱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force
በትግራይ ሽረ እንዳሥላሴ እና አካባቢው ተሰማርቶ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ከአካባቢው እንዲወጣ መደረጉን የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ጦርነቱን ለማስቆም በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት የአማራ ልዩ ኃይሎች ከአካባቢው እንዲወጣ ተደርጓል ብሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ሐሙስ ጥር 04/2015 ዓ.ም. በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ነው ልዩ ኃይሉ መውጣቱን የገለጸው።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በሽረ እና አካባቢው ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ተሠልፎ አገራዊ ተልዕኮን ሲፈፅም የነበረው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በስምምነቱ መሠረት ከቀጠናው እንዲወጣ አድርጓል” ብሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት የኤርትራ፣ የአማራን ጨምሮ የክልል ልዩ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ሲዋጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በዘላቂነት ለማቆም በደረሱት የሰላም ስምምነት፤ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቃቸውን በመፍታት ለፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እንደሚያስረክቡ እና ከፌደራሉ መንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ እንደወጡ መስማማታቸው ይታወቃል።
በዚሁ መሠረት የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ተዋጊዎችን የመበተን እና መልሶ የማቋቋም ሥራው በዚህ ሳምንት በይፋ መጀመሩ ተዘግቧል።
ከጥቂት ቀናት በፊትም የአገር መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ኃይሎች የፈቱትን ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች በተገኙበት መረከብ መጀመሩ ተገልጿል።
በዚህ ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩት የጎረቤት አገር ኤርትራ ሠራዊት አባላትም ከክልሉ የመውጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ ከሳምንት በፊት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የሽረ እና አክሱም ከተማ ነዋሪዎች የኤርትራ ወታደሮች እንቅስቃሴ መኖሩን መመልከታቸውን ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ ወታደሮቹ አሁንም በከተሞቹ ዙሪያ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራን ባስከተለው ጦርነት ሲፋለሙ የቆዩት ሁለቱ ኃይሎች ጦርነቱን ለማቆም የሰላም ስምምነት ከደረሱ ወዲህ ከፌደራሉ መንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ አካባቢዎች መውጣታቸው በይፋ ሲገለጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሐሙስ ጥር 04/2015 ዓ.ም. “ለአማራ ልዩ ኃይል ሽኝት” ሲደረግ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ እና የዕዝ አመራሮች ተገኝተው ነበር ተብሏል።
የክልሉ ጦር አካባቢውን ለቅቆ ሲወጣ አመራሮቹ “የከፈልነው ዋጋ ለጋራ ሠላማችን ስንል ነውና በመንግሥት ትዕዛዝ መሠረት በተደረሰው የሠላም ስምምነት ኃይላችንን ከሽረ እና አካባቢው እያስወጣን ነው” ስለማለታቸው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defence Force
ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት
ይህን ለሁለት ዓመታት የዘለቀ የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ሽምግልና ሲያካሂድ ቆይቶ የተሰካለት ባለው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ ነበር።
ሁለቱ ወገኖች ፕሪቶሪያ ላይ በደረሱት ስምምነት በዋናነት ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት የፈረሙ ሲሆን በዚህም ሰብዓዊ እርዳታ ያለገድብ እንዲቀርብ፣ የተቋረጡ መሠረታዊ አግልገሎቶች መልሰው እንዲጀመሩ እና የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ወስነው ነበር።
በስምምነቱ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ በሚፈቱበት በተመሳሳይ ጊዜም የኤርትራን ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንደሚወጡ ተገልጿል።
የህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች ከፕሪቶሪያ በማስከተል ለሁለት ጊዜ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ ተገናኝተው በስምምነቱ አተገባበር ላይ ተወያይተው ከስምምነት ደርሰዋል።
ባለፉት ሳምንታት የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ፣ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ሥራ እየተመለሱ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት በትግራይ የሚገኙ የፌደራል መንግሥቱን ተቋማት መቆጣጠር ጀምረዋል።












