ወርቃማው ደም፡ በዓለማችን 50 ሰዎች ብቻ ያላቸው የደም ዓይነት

የደም ናሙና
የምስሉ መግለጫ, የደም ናሙና

ከስድስት ሚሊዮን ሰዎች አንዱ ብቻ አርኤች ነል (Rh null) የተባለው የደም ዓይነት አለው። አሁን ተመራማሪዎች የበርካቶችን ሕይወት ሊያድን ይችላል በሚል ተስፋ ይህንን የደም ዓይነት በቤተ ሙከራ ውስጥ ለማዘጋጀት እየሞከሩ ነው።

ደም ለሚያስፈልገው ታማሚ የሌላ ሰው ደም ሰጥቶ ማከም የዘመናዊ ሕክምናን መልክ በእጅጉ ቀይሯል።

አይበለውና ጉዳት ከደረሰብን፣ ወይም ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ካስፈለገን ሌሎች የለገሱት ደም ሕይወታችንን ሊታደግ ይችላል።

ነገር ግን ሁሉም ሰው ከዚህ ተጠቃሚ መሆን አይችልም። የተለየ የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች ከራሳቸው ጋር የሚስማማ ደም ለማግኘት ይቸገራሉ።

በጣም አልፎ አልፎ ከሚታዩት መካከል አንዱ የሆነው አርኤች ነል ( Rh null) የደም ዓይነት እንዳላቸው የታወቁ የዓለማችን ሰዎች 50 ብቻ ናቸው።

እነዚህ ሰዎች ጉዳት ቢደርስባቸው እና ደም መውሰድ ቢያስፈልጋቸው የማግኘት ዕድላቸው ከሸረሪት ድር የቀጠነ ነው።

አርኤች ነል የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች የራሳቸውን ደም ለረጅም ጊዜ በማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲያስቀምጡ ይበረታታሉ።

ምንም እንኳን ያልተለመደ የደም ዓይነት ቢሆንም፣ ይህ የደም ዓይነት በሌሎች ምክንያቶችም በጣም በልዩ ሁኔታ የሚታይ ነው።

በሕክምና ባለሙያዎች እና በተመራማሪዎች ዘንድ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን መንገድ በማየት አንዳንድ ጊዜ "ወርቃማው ደም" ተብሎ ይጠራል።

በተጨማሪም ሳይንቲስቶች ከለጋሾች የተገኘ ደም ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚገድቡትን የበሽታ መከላከል ጉዳዮች ለመፍታት በሚመራመሩበት ወቅት የተለያየ የደም ዓይነት ላላቸው ሰዎች ሁሉ ሊሰጥ የሚችል ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

ሦስት ሰዎች ቆመው ስልካቸውን እየተመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተለያዩ የደም ዓይነቶችን የሚያሳይ የግድግዳ ስዕል

የደም ዓይነቶች የሚከፋፈሉት እንዴት ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመላ ሰውነታችን የሚዘዋወረው የደም ዓይነት የሚከፋፈለው በቀይ የደም ህዋሶቻችን ውስጥ ባሉ ወይንም በጎደሉ ነገሮች ላይ በመመሥረት ነው።

እነዚህ ጠቋሚዎች፣ አንቲጂኖች በመባል የሚታወቁ ሲሆን በህዋሶቻችን ላይ በሚጣበቁ ወይንም በበሽታ የመከላከል ሥርዓታችን ላይ ታቅፈው የሚገኙ ፕሮቲኖችን ወይንም ስኳሮችን ይይዛሉ።

በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የሴል ባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አሽ ቶዬ "በራሳችን ደም ውስጥ ካለ የተለየ አንቲጂን የያዘ ሌላ ደም ከተሰጠን፣ ለዚያ ደም አንቲቦዲዎችን በማምረት ያጠቃዋል" ብለዋል።

"ያ ደም እንደገና ለግለሰቡ የሚሰጥ ከሆነ ለሕይወቱ አስጊ ሊሆን ይችላል።"

ትልቁን የበሽታ መከላከል የሚቀሰቅሱት ሁለቱ የደም ዓይነቶች ኤቢኦ (ABO ) እና ሬሰስ (አርኤች) ናቸው። አንድ ኤ የደም ዓይነት ያለው ሰው በቀይ የደም ሕዋሱ ላይ ኤ አንቲጂኖች ሲኖሩት ቢ የደም ዓይነት ያለው ሰው ደግሞ ቢ አንቲጂኖች አሉት።

የኤቢ የደም ዓይነት ያለው ሁለቱም ኤ እና ቢ አንቲጂኖች ይኖሩታል። ከ ኦ የደም ዓይነት ጋር ምንም የለውም። እያንዳንዱ ቡድን አርኤች ፖዘቲቭ (Rh-positive) ወይም አርኤች ኔጋቲቭ (Rh negative) ሊሆን ይችላል።

ኦ ኔጋቲቭ የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለሁሉም የደም ዓይነት መለገስ የሚችሉ ናቸው። ምክንያቱም ደማቸው ኤ፣ ቢ ወይም አርኤች አንቲጂኖች የለውም። ሆኖም ይህ ጉዳዩን ከመጠን በላይ ማቅለል ነው።

በአሁኑ ጊዜ እስከ ጥቅምት 2024 ድረስ ብቻ 47 የታወቁ የደም ዓይነቶች እና 366 የተለያዩ አንቲጂኖች አሉ።

ይህ ማለት አንድ ኦ ኔጋቲቭ የሚሰጠው ሰው ለሌሎች አንቲጂኖች የበሽታ መከላከያ ምልክት ሊያሳይ ይችላል። ምንም እንኳን አንዳንድ አንቲጂኖች ከሌሎች የበለጠ በሽታ የመቋቋም ምላሽ ሊያሳዩ ይችላሉ።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ከ50 አርኤች በላይ አንቲጂኖች አሉ። ሰዎች ስለ አር ኤች ኔጌቲቭ ሲናገሩ፣ የሚጠቅሱት የአርኤች(ዲ) አንቲጂንን ነው። ነገር ግን ቀይ የደም ሴሎቻቸው አሁንም ሌሎች አርኤች ፕሮቲኖችን ይዟል።

እንዲሁም በዓለም ዙሪያ እጅግ በጣም ብዙ የአርኤች አንቲጂኖች አሉ። ይህም እውነተኛ ተመሳሳይ ለጋሽ ማግኘት አስቸጋሪ ያደርጋል። በተለይ በአንድ አገር ውስጥ ካሉ አናሳ ጎሳ ለሚመጡ ሰዎች ይህ ፈታኝ ነው።

የተለገሰ ደም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርኤች ነል የደም ዓይነት በጣም በብዛት የማይገኝ ቢሆንም ለሕክምና ግን በጣም ጠቃሚ ነው

አርኤች ነል (Rh null) ደም ያላቸው ሰዎች ግን ሁሉም 50 አርኤች አንቲጂኖች ይጎድላቸዋል። እነዚህ ሰዎች ማንኛውንም ሌላ የደም ዓይነት መቀበል ባይችሉም፣ አርኤች ነል ደም ግን ከብዙ አርኤች የደም ዓይነቶች ጋር ይጣጣማል።

ይህም የኦ ደም ዓይነት አርኤች ነል እጅግ በጣም ተፈላጊ ያደርገዋል፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰዎች፣ ሁሉም ዓይነት ኤቢኦ ያላቸው ግለሰቦችን ጨምሮ፣ ሊሰጣቸው መቻሉ ነው።

የታካሚው የደም ዓይነት በማይታወቅበት ድንገተኛ ሁኔታ ውስጥ፣ ኦ የደም ዓይነት ያለው አርኤች ነል ደም በትንሹ የአለርጂ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሳይንቲስቶች ይህንን "ወርቃማ ደም" ለመሥራት መንገዶችን እየፈለጉ ነው።

ፕሮፌሰር ቶዬ "አርኤች አንቲጅኖች ጠንካራ የመከላከል ምላሽ እንዲኖር ያደርጋሉ፤ በመሆኑም ከእነዚህ መካከል ምንም ከሌለህ የመከላከል አቅምህ ምላሽ የሚሰጠው ምንም ነገር የለም" ብለዋል።

"ኦ የደም ዓይነት እና አርኤች ነል ከሆንክ ያ በጣም ለሁሉም የሚስማማ ነው። ነገር ግን አሁንም ግምት ውስጥ የሚገቡ ሌሎች የደም ዓይነቶች አሉ።"

የአርኤች ነል ደም መነሻ

የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንዳረጋገጡት አርኤች ነል ደም የሚፈጠረው በልውጥ ዘረ መል ምክንያት ሲሆን፣ ይህም በቀይ የደም ሴሎች ውስጥ ወሳኝ ሚና በሚጫወት ፕሮቲን ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ወቅት ነው።

ይህም ከአርኤች ጋር የተገናኘ ግላይኮፕሮቲን ወይም አርኤችኤጂ (RHAG) በመባል ይታወቃል።

እነዚህ ልውጦች የዚህን ፕሮቲን ቅርጽ የሚያሳጥሩ ወይም የሚቀይሩ ናቸው፤ ይህም የሌሎችን አርኤች አንቲጂኖች አሠራር ይረብሸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 በተደረገ ጥናት፣ ፕሮፌሰር ቶዬ እና የብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ባልደረቦች አርኤች ነል ደም በቤተ ሙከራ ውስጥ መሥራት ችለዋል። ይህንን ለማድረግ አንድ ህዋስን በመውሰድ በቤተ ሙከራ ውስጥ በአግባቡ ወዳልደረጁ ህዋሶች እንዲያድጉ አድርገዋል። ይህም በበቂ ያልደረጁ ቀይ የደም ህዋሶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

ቡድኑ የዘረ መል ማስተካከያ መሳሪያን በመጠቀም በአምስቱ የደም ዓይነቶች ሥርዓት ውስጥ አንቲጂኖችን በማምረት ላለመጣጣሙ ተጠያቂ የሆኑትን አስወግዷል። ይህም ኤቢኦ እና አርኤች አንቲጂኖችን እንዲሁም ኬል፣ ዱፊ እና ጂፒቢ የሚባሉ ሌሎችንም ያካትታል።

የተገኙት የደም ህዋሶች ለሁሉም ዋና ዋና የደም ዓይነቶች ተስማሚ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከአራት ሚሊዮን ሰዎች መካከል አንዱ ላይ ብቻ ለሚገኙት እንደ አርኤች ነል እና እንደ ቦምቤይ ፌኖታይፕ ላሉ የተለዩ የደም ዓይነቶችም ይሆናል።

ይህ የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች ኦ፣ ኤ፣ ቢ ወይም ኤቢ ደም ሊሰጣቸው አይችልም።

የዘረ መል ማስተካከያ ስልቶችን መጠቀም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች አወዛጋቢ እና ቁጥጥር የሚደረግበት በመሆኑ እጅግ የሚጣጣም የደም ዓይነት በቤተ ሙከራ ሊገኝ የሚችልበት ጊዜ ሊርቅ ይችላል።

ከመፈቀዱ በፊት ብዙ ዙሮች በቤተ ሙከራ የሚደረጉ ምርምሮችን እና ፍተሻዎችን ማለፍ ያስፈልገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ፕሮፌሰር ቶዬ አርኤች ነልን (Rh null) ጨምሮ ያልተለመዱ የደም ዓይነት ካላቸው ሰዎች የደም ልገሳ የሚሰበስብ ስካርሌት ቴራፒዩቲክስ የተሰኘ ኩባንያ አቋቁመዋል።

ቡድኑ ያንን ደም በመጠቀም በቤተ ሙከራ ውስጥ ሊያድጉ የሚችሉ ህዋሳትን በመፍጠር ቀይ የደም ህዋሶችን ላልተወሰነ ጊዜ ለማምረት ተስፋ አድርገዋል። ይህ በቤተ ሙከራ ያደገው ደም ለድንገተኛ አደጋ በማቀዝቀዣ ውስጥ ተቀምጦ የተለየ የደም ዓይነቶች ያላቸው ሰዎች ይገለግሉበታል።

ፕሮፌሰር ቶዬ የዘረ መል ማስተካከያ ሳይጠቀሙ በቤተ ሙከራ ውስጥ የተለየ ደም ዓይነት ባንኮችን ለማቋቋም ተስፋ ያደርጋሉ።

"ያለ ማስተካከያ መሥራት ከቻልን በጣም ትልቅ ነገር ነው። ነገር ግን ማረም ለእኛ አማራጭ ነው" ብለዋል።

"እያደረግን ያለነው ለጋሾችን በጥንቃቄ በመምረጥ ሁሉም አንቲጂኖቻቸው በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች እንዲስማሙ ለማድረግ ነው። ከዚያ ምናልባት ለሁሉም ሰው ተስማሚ እንዲሆን የዘረ መል አርትዖት ማድረግ ይኖርብናል።"

ደም የምትለግስት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቤተ ሙከራ የሚያድግ ደም ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የደም ልገሳ ግን ውጤታማ ተግባር ነው

በአውሮፓውያኑ 2021 የበሽታ መከላከያ ሥርዓት ተመራማሪዎቹ ግሪጎሪ ዴኖም እና ሚልዋኪ አሜሪካ ውስጥ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ የደም ምርምር ተቋም ውስጥ ካሉ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የዘረ መል ማስተካከያን በመጠቀም አርኤች ነልን ጨምሮ የተሻሻሉ የደም ዓይነቶችን ለመፍጠር ሞክረዋል።

እነዚህ ስቴም ህዋሳት ከኢምብሮዮ ህዋሳት ጋር ተመሳሳይነት ባህሪያት አላቸው። እንዲሁም ትክክለኛ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰው አካል ውስጥ ያለ ማንኛውም ህዋስ የመሆን አቅም አላቸው።

ሌሎች ሳይንቲስቶች የደም ህዋሳት ለመሆን አስቀድሞ የተዘጋጁ ሌላ ዓይነት ስቴም ህዋሳትን እየተጠቀሙ ነው፤ ነገር ግን የትኛውን ዓይነትየሚለውን እስካሁን አልወሰኑም። ለምሳሌ፣ በካናዳ ኪውቤክ የሚገኘው የላቫል ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች በቅርቡ ኤ ፖዘቲቭ ደም ካላቸው ለጋሾች የደም ስቴም ህዋሳትን ወስደዋል።

በመቀጠል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኤ እና አርኤች አንቲጂኖችን ዘረመል በመሰረዝ፣ ኦ አርኤች ነል በአግባቡ ያልደረጁ ቀይ የደም ህዋሳትን ፈጠሩ።

በስፔን ባርሴሎና የሚገኙ ተመራማሪዎችም በቅርቡ ስቴም ህዋሳትን ከአርኤች ነል ደም ለጋሽ ወስደዋል፤ እና ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የደሙን ዓይነት ከኤ ወደ ኦ በመቀየር ለሁሉም የሚስማማ አድርገዋል።

እነዚህ አስደናቂ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ ቤተ ሙከራ ውስጥ የበለፀገ ደም ሰዎች ሊጠቀሙበት በሚችሉበት ደረጃ መፍጠር አሁንም በጣም ሩቅ ነው ማለት ይቻላል።

አንድ አስቸጋሪ ነገር ስቴም ህዋሳት ወደ በአግባቡ የደረጀ ቀይ የደም ህዋሳት እንዲያድጉ ማድረግ ነው።

በሰውነታችን ውስጥ ቀይ የደም ህዋሳት የሚመነጩት ከመቅኒ ውስጥ ከሚገኙ ስቴም ህዋሳት ሲሆን ይህም እንዴት እንደሚዳብሩ ለማወቅ ውስብስብ ፍንጮችን ለይተዋል። በዚህም የተነሳ በቤተ ሙከራ ውስጥ ለመድገም አስቸጋሪ ነው።

በግሪፍሎስ ዲያግኖስቲክ ሶሉሽንስ ውስጥ የሚሠሩት ዴኖምሜ "አርኤች ነል ወይም ሌላ ምንም ዓይነት ነል የደም ዓይነት ሲፈጠር የቀይ የደም ህዋሳት ዕድገት እና መደርጀት ሊታወክ የሚችልበት ተጨማሪ ችግር አለ" ይላሉ።

"የተወሰኑ የደም ዓይነት ዘረመሎችን መሥራት የህዋስ ሽፋን እንዲፈርስ ወይም በህዋስ ናሙና ውስጥ ቀይ የደም ህዋሳትን በብቃት ማምረት እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል" ሲሉም አክለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ፕሮፌሰር ቶዬ በዓለም የመጀመሪያው ክሊኒካዊ ሙከራን በመምራት ላይ ናቸው። ለጤናማ በጎ ፈቃደኞች በቤተ ሙከራ ውስጥ ከለጋሾች ከተገኘ የደም ስቴም ህዋሳት ተወስደው በሰው ሠራሽ መንገድ የሚያድጉትን ቀይ የደም ህዋሳት የመስጠትን ደኅንነት እየፈተሹ ነው።

በሙከራው ውስጥ ያለው ሰው ሠራሽ ደም በምንም መልኩ በዘረ መል አርትኦት አልተስተካከለም፤ ነገር ግን ሳይንቲስቶች በሰዎች ላይ ለመፈተሽ ዝግጁ ወደነበሩበት ደረጃ ለመድረስ አሁንም የ10 ዓመት ጥናት ፈጅቷል።

"በአሁኑ ጊዜ ደምን ከአንድ ሰው መውሰድ የበለጠ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ ነው፤ እናም ለወደፊቱ ደም ለጋሾች እንፈልጋለን" ብለዋል ፕሮፌሰር ቶዬ።

ነገር ግን ሌሎች ለጋሾች በጣም ጥቂት በሆኑባቸው፣ የተለየ የደም ዓይነቶች ላላቸው ሰዎች ብዙ ደም ማሳደግ ከቻልን ያ በጣም አስደሳች ይሆናል።"