የእርጅና ምልክቶችን የሚያዘገየው እና በቆዳችን ጤንነት ላይ ጉልህ ውጤት የሚኖረው ምርምር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተመራማሪዎች የእርጅና ምልክቶችን ለማዘግየት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የተባሉ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ይፋ አድርገዋል።
የተመራማሪዎቹ ቡድን፣ የሰው አካል ከስቴም ሕዋስ እንዴት ቆዳን እንደሚፈጥር እንዲሁም የተወሰነ መጠን ያለው ቆዳን በቤተ ሙከራ ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ደርሶበታል።
ምርምሩ እያንዳንዱ የሰውነት አካል እንዴት እንደተፈጠረ ለመረዳት እየተካሄደ ያለ ጥናት አካል ነው።
ግኝቶቹም እርጅናን ከመከላከል ባሻገር የሰው ሠራሽ ቆዳ ንቅለ ተከላ ለማድረግ እና ጠባሳን ለማስወገድ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ተብሏል።
ምርምሩ የተካሄደው በ'ሂውማን ሴል አትላስ ኮንሶርቲየም' ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በሥነ ሕይወት ዘርፍ ካሉ ትላልቅ የምርምር ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ነው።
ሂውማን ሴል አትላስ ዓለም አቀፍ ተቋም ሲሆን፣ በካምብሪጅ በሚገኘው ዌልካም ሳንገር ማዕከሉን አድርጓል።
ፕሮጀክቱን ከሚመሩት መካከል አንዷ የሆኑት ፕሮፌሰር ሙዝሊፋህ ሃኒፋ እንዳሉት የምርምሩ ግኝቶች ተመራማሪዎች በሽታዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያክሙ ይረዳቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ምርምሩ ለረዥም ጊዜ ጤናማ ሆነን እንዲንቆይ የሚረዱና ምናልባትም ወጣት መስለን እንድንቆይ የሚያስችሉ አዳዲስ ዘዴዎችን ማግኘቱን ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል።
“ቆዳችንን ማስተካከል እና እርጅናን መከላከል ከቻልን በጣም ጥቂት የቆዳ መሸብሸብ ብቻ ነው የሚኖረን” ብለዋል ፕሮፌሰር ሃኒፋ ።
“ከመጀመሪያው ዕድገታቸው ጀምሮ እስከ እርጅና ዕድሜ ድረስ ሕዋሶቻችን እንዴት እንደሚለወጡ ከተረዳን በኋላ የአካል ክፍሎችን እንዴት ማደስ እችላለሁ፣ ልባችንን እንዴት ወጣት ማድረግ እንችላለን? ቆዳንስ? ማለት እና መሞከር ትችላላችሁ” ይላሉ።
ይህ ራዕይ በሂደት ላይ ያለ ቢሆንም ተመራማሪዎች አበረታች ውጤቶችን እያዩ ነው።
በቅርቡ በሰው ልጆች ሕይወት የመጀመሪያው ዕድገት በሆነው ፅንስ ውስጥ የቆዳ ሕዋሶች እንዴት እንደሚያድጉ በመረዳት ላይ ናቸው።
እንቁላል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲዳብር የሁሉም ሰው ሕዋሶች ተመሳሳይ ናቸው። ከሦስት ሳምንታት በኋላ ግን በስቴም ሕዋሳት ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ጂኖች የተለያዩ የሰውነት አካል ክፍሎችን ለመሥራት መመሪያዎችን ያስተላልፋሉ።
በዚህም መሠረት ትልቁ የአካል ክፍላችን የሆነውን ቆዳችንን ለመሥራት የትኞቹ ጂኖች በየትኛው ጊዜ እና የት ቦታ ላይ እንደተቀየሩ ተመራማሪዎች መለየት ችለዋል።
እነዚህ ጂኖች በአጉሊ መነጽር እና በኬሚካል እገዛ ሲታዩ በጣም ትናንሽ የጌጥ መብራቶች ነው የሚመስሉት።
ወደ ብርቱካናማ ቀለም የሚቀየሩ ጂኖች የቆዳውን ገጽ የሚፈጥሩ ሲሆን፣ ሌሎቹ ቢጫ ቀለም ያላቸው ደግሞ የቆዳውን ቀለም ይወስናሉ።
ሌሎች በጣም በርካታ ጂኖች ደግሞ የሰውነት ላብ እንዲወጣ የሚያስችሉ እና ከውጪው ዓለም የሚጠብቁንን ፀጉሮች የሚያበቅለውን የቆዳ ክፍል ይፈጥራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Inserm
ተመራማሪዎቹ የሰው ልጅ ቆዳን ለመፍጠር የሚያስችሉ መመሪያዎችን ያገኙ ሲሆን፣ ግኝታቸውንም ኔቸር በተባለ መጽሔት ላይ አሳትመውታል። እነዚህን መመሪያዎች ማንበብ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማወቅ ይረዳል።
ለምሳሌ ተመራማሪዎች የፅንስ ቆዳ ያለምንም ጠባሳ እንደሚድን ደርሰውበታል።
መመሪያውም ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እና በቀዶ ሕክምና ጊዜ በአዋቂዎች ቆዳ ላይ መተካት ይቻል እንደሆነ የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎችን ይዟል።
ወሳኝ በሆነው የምርምሩ ግኝት ውስጥ ተመራማሪዎቹ የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት በቆዳ ውስጥ የደም ስሮች ለመፈጠራቸው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የደረሱበት ሲሆን፣ ከዚህም በቤተ ሙከራ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ መመሪያዎችን መኮረጅ ችለዋል።
ቆዳን ከስቴም ሴል በሰው ሰራሽ መንገድ ለማሳደግ ጂኖቹን በትክክለኛው ጊዜ እና ቦታ ለማጥፋት እና ለማስነሳትም ኬሚካሎችን ተጠቅመዋል። በዚህም መሠረት ፀጉር ማብቀል የቻለ በጣም ትንሽ ለስላሳ ቆዳ በቤተ ሙከራ ውስጥ ማሳደግ ችለዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ሃኒፋ ከሆነ የምርምሩ ዓላማ ይህንን ዘዴ ስህተት አልባ ማድረግ ነው።
“የሰው ልጅ ቆዳን እንዴት መሥራት እንደሚቻል ካወቅን በቃጠሎ ምክንያት ለተጎዱ ህሙማን ልንጠቀምበት እንችላለን። የሕብረ ሕዋሳት (ቲሹ) ንቅለ ተከላ ዘዴ ሊሆንም ይችላል” ብለዋል።
“የፀጉር ቀዳዳዎችን መሥራት ከቻልን ደግሞ ለመላጣ ሰዎች ፀጉር ማሳደግ የሚያስችል ዘዴ መፍጠር እንችላለን ማለት ነው።” ይላሉ።
ምርምሩ በዘር የሚተላለፉ የቆዳ በሽታዎች እንዴት እንደሚከሰቱ ለማወቅ እና ሕክምናውን ለመፈለግም ሊጠቅም ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Megumi
ዘ ሂውማን ሴል አትላስ ፕሮጀክት ምርምሩን ለመሥራት ላለፉት ስምንት ዓመታት ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የተወሰዱ 100 ሚሊዮን ሕዋሳትን ተንትኗል።
ፕሮጀክቱ የአንጎል እና የሳንባን አወቃቀርን የተመለከተ ንድፍ የፈጠረ ሲሆን፣ ተመራማሪዎች በኩላሊት፣ በጉበት እና በልብ ላይ እየሠሩ ናቸው።
ቀጣዩ ሒደትም የግለሰቦችን የአካል ክፍሎች በአንድ ላይ መገጣጠም መሆኑን ዘ ሂውማን ሴል አትላስ ቡድንን ከመሠረቱት እና ከሚመሩት መካከል አንዷ የሆኑት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ሳራህ ቴችማን ተናግረዋል።
“በጣም የሚያስደስት ነው፤ ምክንያቱም በፊዚዮሎጂ፣ አናቶሚ እና የሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ አዲስ ሃሳብ እየሰጠን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ምርምሩ ስለራሳችን፣ ስለሕብረ ሕዋሳችን (ቲሹ) እና አካላችን እንዲሁም እነዚህ የአካል ክፍሎች እንዴት እንደሚሠሩ መማሪያ መጽሐፍትን እንደገና ለመጻፍም ይመራሉ” ብለዋል።












