ኢሰመኮ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ “ለተዓማኒ እና እውነተኛ” የሽግግር ፍትህ እሰራለሁ አለ

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እና ሌሎች ወንጀሎችን የሚመለከተው የሽግግር ወቅት የፍትህ አስተዳደር “እውነተኛ፣ ተአማኒ እና ግልጽነት ያለው” እንዲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንደሚያግዝ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሰላም ስምምነቱ ላይ የተጠቀሰው አይነት የሽግግር ፍትህ እንዲተገበር ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት በምክረ ሀሳብ ደረጃ ማስቀመጡን አስታወሰው፣ ይህ እንዲሆን መወሰኑ “ትክክለኛ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ኢሰመኮ በሁለት ዓመቱ የጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚመለከት ተጨማሪ ምርመራ አያደርግም ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ይህ የሚከናወነው የሽግግር ወቅት ፍትህን በሚመራው አካል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሆኖም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ወዲህ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ተቋማቸው ምርመራ ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ አጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ እና በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም የሚፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወይም ስጋቶች የሚኖሩ ከሆነ ክትትል ለማድረግ ዕቅድ አለን" በማለት ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጨምረውም “ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ግን. . . አሁን ሊተገበር የሚገባው በሽግግር ወቅት ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ነው” ብለዋል።

ይህ የፍትህ ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን ግን ኮሚሽናቸው አስተወጽኦ እንደሚያደረግ አስረድተዋል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን ምን አይነት የሽግግር ወቅት ፍትህ አስተዳደር መተግበር አለበት በሚል ጥናት እያከናወነ ስለመሆኑ የገለጹ ሲሆን፣ ጥናቱ በክልሎች በመዘዋወር ምክክር ተደርጎበታል ብለዋል።

ጥናቱ ላይ በመመርኮዝም ለኢትዮጵያ ተስማሚ ነው የሚለውን የሽግግር ወቅት ፍትህ ሥርዓት ምክረ ሀሳብ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።

ይህ ምክረ ሃሳብ እንዲተገበርም የሙያ እና የቴከኒክ ደጋፍ ኢሰመኮ እንደሚያደርግ፣ ሲተገበርም በትክክል ስለመከናወኑ የሰብአዊ መብት ክትትልና ምርመራ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማቆም ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የሽግግር ፍትህ አስተዳደር እና ፋይዳው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አገራት ከግጭት እና ከፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ሲመለሱ በግጭቱ ወቅት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች እንዴት ይታዩ? የሚለው ጉዳይ ሁልጊዜም ጥያቄ ሆኖ የሚነሳ ነው ይላሉ - ዳንኤል (ዶ/ር)።

እነዚህ ጥሰቶች እና ወንጀሎች በርካታ እንዲሁም ውስብስብ ስለሚሆኑ በመደበኛው የፍትህ ሥርዓቱ አማካይነት ለመመልከት አስቸጋሪ ይሆናሉ።

ታዲያ ይህንን ችግር ለመፍታት አገራት ከግጭት ወደ ሰላም የሚደረግ የሽግግር ወቅት ፍትህ አስተዳደር ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

የተለያዩ ቀውሶች በአገራት ውስጥ በሚያጋጥሙበት ጊዜ ለመፍትሄ ከሚቀርቡ አማራጮች መካከል የሽግግር ፍትህ ሥርዓት አንዱ ነው። የአፍሪካ ኅብረትም ይህንን ይህንን ሥርዓት በተመለከተ የእራሱ የሆነ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለው።

ይህ የፍትህ ሥርዓት መፍትሄ ለማበጀት የሚቀርበው ለወቅታዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ቆየት ላሉ ታሪካዊ ቀውሶችም ጭምር ነው። በዚህም ለደረሱ መጠነ ሰፊ ጉዳቶች ወይም ለቆዩ ታሪካዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ሥር ለሰደዱ መከፋፈሎች እና ለኢፍትሃዊነት ድርጊቶች በመደበኛ ወይም በኢመደበኛ መንገድ መፍትሄ የሚፈለግበት መንገድ ነው።

ይህ የሽግግር ፍትህ ሥርዓት አራት ዋነኛ ዓላማዎችን የሚይዝ ሲሆን፣ ቀዳሚው እውነትን ማፈላለግ እና ማወቅ ነው።

ኮሚሽነሩ እንደሚሉት በግጭት ወቅት “የተሟላውን እውነት” ስለማይታወቅ የት ቦታ ምን ተፈጠረ የሚለውን ማጣራት እና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት የሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ቁንጮ ነው።

የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ሁለተኛው ዓላማ ሲሆን፣ ከፍተኛ ከሚባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል አንጻር ተጠያቂነት ማረጋገጥ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው።

በአራተኛ ደረጃ አገሪቱ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ በድጋሚ እንዳትገባ ምን አይነት ለውጥ እና ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚለውን መመርመር ነው።

ይህም ብዙ ጊዜ የሕገ መንግሥት፣ የሕግ ወይም ፖሊሲ ለውጥ በማድረግ የችግሩን መሠረት በዘላቂት ለመፍታት የሚደረግ ነው ብለዋል - ዳንኤል (ዶ/ር)።

በማን ተግባራዊ ይሆናል?

በኢትዮጵያም ይህ ዓይነት የፍትህ ሥርዓት እንዲዘረጋ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መካተቱን ያደነቁት ኮሚሸነሩ “አሁን ደግሞ ተግባራዊ እንዲሆን የምንፍልገው፣ ልክ በሰጠነው ምክረ ሃሳብ መሠረት እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እውነተኛ፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ የሽግግር ወቅት ፍትህ እንዲቋቋም እና እንዲተገበር ነው” ብለዋል።

በብዙ አገራት ይህንን ተግባር የሚያከናውን አካል ራሱን ችሎ በሚዋቀር ተቋም የሚመራ ሲሆን፣ በተወሰኑ አገራት ደግሞ በሥራ ላይ ካሉ ተቋማት በሚወጣጡ አካላት አማካይነት ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ይህንን የፍትህ ሥርዓት ለመተግበር ምክንያት ቢሆንም፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሊተገበር የሚገባው መሆኑን የኢሰመኮ ኮሚሽነር ጠቅሰዋል።

ይህ አይነት የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ሳይተገበር በመቆየቱ “ምን አልባምት ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የምንመለከተው ለዚህ ነው ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

በዚህም ሳቢያ በተቻለ መጠን ይህ ተግባር በአገር አቀፍ ደረጃ ሊከናወን ይገባል ብሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንደሚያምን ተናግረዋል።

ዳንኤል (ዶ/ር) ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚመሩት ኮሚሽን ጦርነቱ እንዲቋጭ እና ለተደረሰው የሰላም ስምምነት “የበኩሉን አስዋጾ ያደረገ ጠቃሚ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል” በማለት፣ ከዚህም በላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተዛምቶ የነበረው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕልፈት ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኪሚሽንን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በርካታ የመብት ተቆርቋሪዎች የጦርነቱ ተሳታፊዎች የነበሩ ሁሉም ወገኖች የተለያዩ አይነት ከባድ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲሉ ሪፖርቶችን ማውጣታቸው ይታወሳል።