በትግራዩ ጦርነት 600 ሺህ ያህል ሰው ሞቷል - ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ ዋነኛ ሚና የተጫወቱት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ በሁለት ዓመቱ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ተናገሩ።
የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ በመሆን አሸማጋይ የነበሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ለፋይናንሻል ታይምስ በጦርነቱ 600,000 ያህል ሰው ሳይሞት እንዳልቀረ ተናግረዋል።
ኦባሳንጆ ለጋዜጣው በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በሁለት ዓመቱ የእርስ በርስ ጦርነት የሞቱት ሰዎች አሃዝ “600,000 ሺህ አካባቢ” ይሆናል ብለዋል።
ነገር ግን በጦርነቱ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። አንድ የቤልጂየም ዩኒቨርስቲ ቀደም ሲል ባደረገው ጥናት መሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ገምቶ ነበር።
ኦባሳንጆ የጠቀሱትን የሟቾች ቁጥርን በተመለከተ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር የሆኑትን ዳንኤል በቀለን (ዶ/ር) ጠይቆ የሟቾች አሃዝን በተመለከተ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ “ሙሉውን ቁጥር ለማወቅ አዳጋች መሆኑን” ጠቅሰው በሁሉም ወገኖች የቀረቡ ግምቶች በጥንቃቄ ሊመረመሩ ይገባል ብለዋል።
ይህ ጦርነት ከሁለት ዓመት በፊት የትግራይ ኃይሎች በክልሉ ውስጥ የሰፈረውን የፌደራሉን ሠራዊት ካጠቁ በኋላ የተጀመረ ሲሆን፣ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን በትግራይ እንዲሁም በአጎራባቾቹ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ላይ አድርሷል።
በኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተመራው የአፍሪካ ኅብረት ጥረት አማካይነት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት ባለፈው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ተፈራርመው ጦርነቱ መቆሙ ይታወቃል።
ኦባሳንጆ ለፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገሩት በሁለቱ ወገኖች መካከል ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ስምምነት በፈረሙበት ዕለት አንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን “በየዕለቱ የሚከሰትን የ1,000 ሰዎች ሞትን አስቁመናል” በማለት መናገሩን ጠቅሰዋል።
ባለፈው ዓመት ቤልጂየም ውስጥ የሚገኘው ጌንት ዩኒቨርስቲ ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት ዙሪያ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሜ አደረኩት ባለው ጥናት 400,000 ያህል ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ ነበር።
ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በቀጥታ በውጊያ እና በተፈጸሙ ጥቃቶች ከሞቱ ሰዎች ባሻገር በምግብ እና በመድኃኒት እጦት ለህልፈት የተዳረጉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ሲነገር ቆይቷል።












