ጀርመን እና ፈረንሳይ በሰሜኑ ጦርነት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር አሳሰቡ

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ከጀርባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ

የፎቶው ባለመብት, Florian Gaertner/photothek.de

የምስሉ መግለጫ, የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ከጀርባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ

የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር አሳሰቡ።

ሁለቱ ሚኒስትሮች ሐሙስ ጥር 04/2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰውን ስምምነት ለመደገፍ እንደሆነ ተነግሯል።

ከዚህም ባተጨማሪ ሚኒስትሮቹ በትግራይ ጦርነት ወቅት ለተፈፀሙ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ጥሪ ማቅረባቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሞቱበት እና ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች ተፈፅመዋል ብለዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና በበኩላቸው አውሮፓ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀጠል የተደረሰውን ስምምነት መተግበር እና ተጠያቂነትን ማስፈን ቅድመ ሁኔታ መሆኑን መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል ።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ ስለዘላቂ ሰላም አስፈላጊነት፣ በአካባቢው ስላለ የምግብ ዋስትና ጉዳይ እና በአውሮፓ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል ስለሚኖር ትብብር እንደሚወያዩ ተገልጿል።

ሚኒስትሮቹ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በመጀመሪያው ቀን ጉብኝታቸው ሐሙስ ጥር 04/2015 ዓ.ም. የተገናኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሁለቱ አውሮፓውያን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጋር “ጥልቅ እና ፍሬያማ” ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ስምምነት ከተደረሰ ከሁለት ወር በኋላ ሲሆን ስምምነቱም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ጦርነቱ የቆመ ሲሆን መሠረታዊ አገልግሎቶች ማስጀመር እና ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ተጀምሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባርቦክ “ሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደመሆኔ አስገድዶ መድፈር የጦርነት አካል መሆኑ የተለመደ አይደለም። በጦርነት ወቅት ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ዓለም አቀፉ የስብዓዊ መብት ሕግ በግልጽ ያስቀምጣል። አስገድዶ መድፈር የጦር ወንጀል ነው” ማለታቸውን ኤፒ ዘግቧል።

ሚኒስትሯ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ከተገናኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ያለፍትህ ዘላቂ ሰላም የለም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከሁለት ዓመት በፊት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወንጀሎች እየተፈፀሙ ነው በማለት የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አግዶ ነበር።

ኅብረቱ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የበጀት ድጋፍ እና እርዳታን ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ ወደ 110 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የበጀት ድጋፍ እንዲዘገይ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የኅብረቱን ውሳኔ “በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የተወሰደ እርምጃ ነው” ሲል ተቃውሞውን መግለጹ ይታወሳል። 

የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች የአጎራባቾቹን የአማራ አፋር ክልሎችን በጎዳው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈፀሙ የአስገድዶ መድፈር እና የግድያ ማስረጃዎች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ወግነው በጦርነቱ የተሳተፉ ጎረቤት አገር ኤርትራ ታደሮችም መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈፀም ይከሰሳሉ።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አብዛኞቹ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች የተፈፀሙት በጦርነቱ በተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ወንጀሎች ለመመርመር እና ወንጀል ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሽግግር የፍትሕ ሥርዓት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን አሳውቋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎችም ተፈፀሙ የተባሉ ወንጀሎችን ለመመርመር እየሰራ መሆኑም ይታወቃል።

ለሁለት ዓመታት ተካሂዶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ያደረሰውን ጦርነት በዘላቂነት ለማቆም ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት መድረሳቸው በምዕራባውያኑ አገራት ሙሉ ድጋፍን አግኝቷል።

ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ግጭት እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ምዕራባውያኑ አበክረው ሲወተውቱ ነበር።

ምዕራባውያኑ ጦርነት እንዲቆም በተደጋጋሚ ከሚያወጡት መግለጫ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎችም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ቆይተዋል።