የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali/fb

የምስሉ መግለጫ, የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና

የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትግራይ ውስጥ የተካሄደውን ጦርነትን ለማስቆም የተደረሰውን ስምምነት ለመደገፍ ያለመ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገቡ።

የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ እንደተናገሩት፣ ከፈረንሳይ አቻቸው ካትሪን ኮሎና ጋር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ስለዘላቂ ሰላም አስፈላጊነት፣ በአካባቢው ስላለ የምግብ ዋስትና ጉዳይ እና በአውሮፓ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል ስለሚኖር ትብብር ይወያያሉ።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ዛሬ ሐሙስ ጥር 04/2015 ዓ.ም. የተገናኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሁለቱ አውሮፓውያን ባለሥልጣናት ጋር “ጥልቅ እና ፍሬያማ” ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ግጭቶችን በዘላቂነት ላስቆመው፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲጀመር እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ላስቻላው እንዲሁም የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ መፍታት እንዲጀምሩ ላደረገው ስምምነት ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሏል።

በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ ባለሥልጣናቱ ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል ሊሆን እንደሚችል የተነገረ ሲሆን፣ በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ከአውሮፓ በኩል ለኢትዮጵያ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍም በሚኒስትሮቹ ጉብኝት ወቅት ይፋ ይደረጋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ስምምነት ከተደረሰ ከሁለት ወር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙበት በአሁኑ ወቅት ስምምነቱ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ባለፈው ሳምንት ከጀርመኗ አቻቸው አናሌና ቤርቦክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ለአንድ የፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጦርነቱን ለማቆም የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማበረታታት እና የአፍሪካ ኅብረትን ጥረት ለመደገፍ እንደሚጓዙ ኤልሲአይ ለተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉት ለሁለት ቀናት ጥር 4 እና 5/2015 ዓ.ም. እንደሚሆን ኤአፍፒ ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሁለቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ስላላት ግንኙነት ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ይነጋገራሉ ብሎ ይጠበቃል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነትን በዘላቂነት ለማቆም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የሰላም ስምምት መድረሳቸው ይታወሳል።

ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰውን ጦርነት በዘላቂነት ለማቆም ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ከስምምነት መድረሳቸው በምዕራባውያኑ አገራት ሙሉ ድጋፍ የተቸረው ሂደት ነው።

ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ግጭት እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ምዕራባውያኑ አበክረው ሲወተውቱ ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ተባብሶ በነበረበት ጊዜ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ደርሳ የነበረውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነት እንዲቋረጥ አድርጋለች።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ 2011 ዓ.ም. ደርሰውት የነበረው ወታደራዊ ስምምነት ሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መታገዱን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቦ ነበር።

በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስምምነት፣ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ሰላም ከወረደ በኋላ ዳግም ተግባራዊ ስለመደረጉ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ምዕራባውያኑ ጦርነት እንዲቆም በተደጋጋሚ ከሚያወጡት መግለጫ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎችም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ኅዳር ማብቂያ 2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ መቃረባቸውን ተከትሎ ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸው ይታወሳል።

የአውሮፓ ኅብረት አገራት እና ኢትዮጵያ

የአውሮፓ ኅብረት ቁልፍ አባላት የሆኑት ፈረንሳይ እና ጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸውን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ማሰባቸው በኅብረቱ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ላይ ውጤት ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።

ባለፈው ሳምንት ኅብረቱ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚ መሆን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት መልሶ ለመጀመር የሚያስችለውን ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጾ ነበር።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ያታዩ ለውጦችን ያደነቀው የአውሮፓ ኅብረት ለዚህም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ፣ “የስምምነቱ በዘላቂነት ተግባራዊ መሆን የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን መልሶ ለመጀመር እንደሚያስችለው” አመልክቷል።

የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የበጀት ድጋፍ እና እርዳታን ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ ወደ 110 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የበጀት ድጋፍ እንዲዘገይ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የኅብረቱን ውሳኔ “በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የተወሰደ እርምጃ ነው” ሲል ተቃውሞውን መግለጹ ይታወሳል።

ኅብረቱ እንዳለው የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ለመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት መኖር ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የልማት እና የምጣኔ ሀብት ድጋፍ ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ያደርጋል ብሏል።

ጨምሮም የኢትዮጵያ አጠቃላይ መረጋጋት፣ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሰላማዊ ልማት ለአካባቢው እና ለአውሮፓ ኅብረት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሷል።

ለሁለት ዓመት ከተካሄደውን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በተለያየ መልኩ ጫና ሲያሳድር የቆየ ሲሆን፣ ለአገሪቱ ሲሰጥ በነበረው የበጀት እና የልማት ድጋፍ ላይም ቅነሳ እና ማዘግየት አድርጓል።

ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነትን ተከትሎ ጦርነት የቆመ ሲሆን፣ በሰብአዊ እርዳታ እና በመሠረታዊ አገልግሎቶች አቀርቦት ላይ መሻሻል መታየቱ ባለፉት ሳምንታት ተገልጿል።