የስምምነቱ ተግባራዊነት ከኢትዮጵያ ጋር ላለን ግንኙነት መሻሻል ወሳኝ ነው፡ የአውሮፓ ኅብረት

አውሮፓ ኅብረት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚ መሆን የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት መልሶ ለመጀመር የሚያስችለውን ሁኔታ እንደሚፈጥር ገለጸ።

ከአንድ ወር በፊት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በአፈጻሙ ዙሪያ ናይሮቢ ላይ ለተፈረሙት ስምምነቶች ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለህወሓት የአውሮፓ ኅብረት አድናቆቱን ገልጿል።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ያታዩ ለውጦችን ያደነቀው የአውሮፓ ኅብረት ለዚህም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ፣ “የስምምነቱ በዘላቂነት ተግባራዊ መሆን የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን መልሶ ለመጀመር እንደሚያስችለው” ገልጿል።

የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ከፍተተኛ መጠን ያለው የበጀት ድጋፍ እና እርዳታን ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ ወደ 110 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የበጀት ድጋፍ እንዲዘገይ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የኅብረቱን ውሳኔ “በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የተወሰደ እርምጃ ነው” ሲል ተቃውሞውን መግለጹ ይታወሳል።

የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው መግለጫ እንዳለው የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና ለመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት መኖር ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የልማት እና የምጣኔ ሀብት ድጋፍ ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ያደርጋል ብሏል።

ኅብረቱ ዘላቂ ግጭት የማስወገድ ስምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ ጠንካራ አመራር እና ዘላቂ የቁጥጥር ዘዴ መኖር ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን በማክበር ጦርነቱ ካስከተለው ጉዳት ለማገገም፣ ለመልሶ ግንባታ እና ለእርቅ መንገድ እንሚከፍት አመልክቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የእርዳታ አቅርቦት ፍላጎት መኖሩን በመጥቀስ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሏል።

ጨምሮም የኢትዮጵያ አጠቃላይ መረጋጋት፣ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሰላማዊ ልማት ለአካባቢው እና ለአውሮፓ ኅብረት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሷል።

ኤርትራንም በተመለከተ የድንበር ጦርነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት መካከል የተደረሰውን የአልጀርስ ስምምነት እንዲሁም ከአራት ዓመት በፊት የተደረሰውን የሰላም ስምምነትን ጠቃሚነት የገለጸው ኅብረቱ፣ የኤርትራ ሠራዊት በአስቸኳይና ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ጠይቋል።

ለሁለት ዓመት ከተካሄደውን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በተለያየ መልኩ ጫና ሲያሳድር የቆየ ሲሆን፣ ለአገሪቱ ሲሰጥ በነበረው የበጀት እና የልማት ድጋፍ ላይም ቅነሳ እና ማዘግየት አድርጓል።

ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት ባለፈው ጥቅም መጨረሻ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነትን ተከትሎ ጦርነት የቆመ ሲሆን፣ በሰብአዊ እርዳታ እና በመሠረታዊ አገልግሎቶች አቀርቦት ላይ መሻሻል መታየቱ ባለፉት ሳምንታት ተገልጿል።

ግጭትን በዘላቂነት የማቆሙ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ በትግራይ ክልል መደበኛ ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት መመለሳቸውን ለማረጋገጥ የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች በቀጣይ ቀናት ወደ መቀለ እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።