በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በጅብ የሚፈጸም ጥቃት የነዋሪዎች ስጋት እየሆነ ነው

ጅብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዋ በጅብ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ስጋት መጨመሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከቀናት በፊትም በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረ ግለሰብ በአዲስ አበባ ዙሪያ በምትገኘው ለገጣፎ ለገ ዳዲ ከተማ በጅብ ተበልቶ መሞቱን ነዋሪዎች እና ፖሊስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትን እና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ጅብ ስምንት ሰዎችን ገድሏል ብሏል።

ባለሙያዎች በከተሞች ዙሪያ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የዱር እንስሳው ባህሪ መቀየር በሰዎች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ።

‘ጥበቃው ምሽት ላይ ተበላ’

ከአዲስ አበባ በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከጥቂት ቀናት በፊት ያጋጠመው ክስተት ነዋሪዎችን ያሸበረ ሆኗል።

ካንትሪ ክለብ ዲቨሎፐርስ (ሲሲዲ) በተባለ የመኖሪያ መንደር ጊቢ አካባቢ የአንድ መኖሪያ ቤት ጥበቃ የሆነ ግለሰብ ቅዳሜ ታኅሣሥ 01/2015 ዓ.ም. በጅብ ተበልቶ መሞቱን ነዋሪዎች እና የከተማው ፖሊስ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በሲሲዲ የመኖሪያ መንደር ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት “እዚያ ግቢ ውስጥ [የመኖሪያ መንደር] ጅብ ከሰው እኩል ነው የሚንቀሳቀሰው። ምሽት 12 ሰዓት ከሆነ በኋላ በሁሉም ቦታ ይታያል” ትላለች።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አለማየሁ፣ በጅብ ተበልቶ የሞተው ግለሰብ የከተማዋ ነዋሪ መሆኑን አረጋገጠው የጥበቃ ሥራውን አጠናቆ ከመንደሩ እየወጣ ሳለ መበላቱን ተናግረዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሲሲዲ መኖሪያ መንደር አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ስሜ አይጠቀስ ያለ የተቋሙ ሠራተኛ ግን በጅቦች ጥቃት ለሕልፈት የተዳረገውን ግለሰብ “ውሾች ሲጮሁ ነዋሪዎች ወጥተው ባትሪ በማብራት ቢያስጥሉትም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም” ብሏል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ጅብ ከ12 ሰዓት ጀምሮ አንዳንድ ጊዜም ከ11 ሰዓት ጀምሮ በመኖሪያ መንደሩ አካባቢ መታየት የሚጀምርበት ጊዜ እንዳለ ጠቅሰዋል።

የልጆች እናት መሆኗን የምትናገር የመንደሩ ነዋሪ ሴት፣ በአካባቢው በጅብ የመበላት ስጋት እንደጨመረ ታስረዳለች።

“ከጅቦቹ ብዛት አንጻር በጣም ያስፈራል። በአካባቢው ያሉ ጥበቃዎች ‘ከዚህ ቦታ አትለፉ’ ብለው የሚከለክሉባቸው ቦታዎች አሉ” ትላለች።

ጅቡ በመኖሪያ መንደር ውስጥ ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እየኖረ እንደሆነ የተቋሙ ሠራተኛ ይናገራሉ።

ጅብ ስጋት በመፍጠሩ የመኖሪያ መንደሩ የከተማ አስተዳደሩን እርዳታ ከጠየቀ በኋላ ከፌደራል እና ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ ባለሙያዎች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የፖሊስ አባላት ባለፉት ቀናት አደን ሲያካሂዱ ቆይተዋል ሲል ሠራተኛው ለቢቢሲ ተናግሯል።

‘በርካታ ጅብ ነው ያለው’

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕብረተሰብ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንኪ ቡዳሞ ወደ ስፍራው ተልኮ የነበረ ሁኔታውን የሚያጣራ የባለሙያዎች ቡድን በአካባቢው በርካታ ጅብ እንዳለ ሪፖርት አድርጓል ብለዋል።

“በአካባቢው ያለው የጅብ ብዛት በነዋሪው የዕለታዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እያስከተለ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል” ብለዋል።

በዚህ መሠረት የጅብ ቁጥርን ለመቀነስ እና ተደናግጦ አካባቢውን ጥሎ የሚሸሽ ከሆነ በሚል ጥረት ተጀምሯል ያሉ ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ሌላ አማራጭ እንደሚፈለግ ገልጸዋል።

ነዋሪው በተኩስ ድምጽ እንዳይረበሽ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ ለቀናት የዘለቀ አደን ተደርጎ 7 ጅቦች መገደላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከሦስተኛው ቀን በኋላ የአደን ሥራው መሳካት አለመቻሉን የሲሲዲ ሠራተኛው “ሦስተኛው ምሽት ላይ ጆቦቹ ተደብቀው ሊገኝ አልቻሉም” ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

የአደን ሥራው ከቆመ በኋላ አሁን በአካባቢ ጅብ መታየት መቀጠሉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

“መጀመሪያ የነበረበት ቦታ ላይ እንደ ከዚህ በፊቱ ነው ያለው። አሁን ለምሳሌ መኖሪያ ቤቴ ፊትለፊት አለ” ያሉት ደግሞ የልጆች እናቷ ነዋሪ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ መኖሪያ ቤቶች እና ሕንጻዎች ውስጥ እየኖረ ያለው የጅብ መንጋ፤ ለሕዝብ ስጋት እንዳይሆን እና “የሰው እና የጅብ መኖሪያ የተለያያ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ” ዳግም የምንመለከተው ይሆናል ሲሉ አቶ ባንኪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሙያው ጅቦች በከተማዋ እና በከተማዋ ዙሪያ ለምን ወደ ሰዎች መኖሪያ እየመጡ እንደሆነ ሲያስረዱ፤ “የጅብ መኖሪያ በሰው እየተያዘ ጅብ ከሰው ጋር እየተቀላቀለ ነው። ደን የለም፤ እየተመነጠረ ነው። የተረፈ ምግብ በየሜዳው ስለሚጣል ጅብ ሰው ወዳለበት ይመጣል” ብለዋል።

አቶ ባንኪ ከአኗኗር መቀያየር ጋር ተያይዞ የእንስሳት ባህሪ ሊቀየር እንደሚችልም ይናገራሉ።

“የሚውሉበት እና የሚያድሩበት ቦታ ተቀየር፤ በቀላሉ ያገኙት የነበረው ምግብ ካነሰባቸው ወይም ካጡ ሰው ወደሚኖርበት ቦታ መሰማራታቸው ግድ ይሆናል። አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለው ይህ ነው” ብለዋል።