ህልውናቸው አደጋ ላይ ያሉት የባቢሌ ዝሆኖች ባለፉት ወራት 13 ሰዎችን ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኘው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ያሉ አደጋ ላይ የሚገኙት ዝሆኖች ካለፈው ዓመት ወዲህ 13 ሰዎችን መግደላቸው ተነገረ።
የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንስሳቱ በሰው ልጆች ላይ ካደረሷቸው ሞትና ጉዳቶች በተጨማሪ ዝሆኖችም በሰዎች እየተገደሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ኃላፊው አደም መሐመድ ሰዎች ወደ ዝሆን መጠለያው በሕገ-ወጥ መልኩ በመግባት መስፈራቸው በሰው እና በዝሆኖች መካከል ግጭት እየፈጠረ በሰዎች እና በዝሆኖች ላይ ሞት እያጋጠመ ነው ብለዋል።
የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፣ የተመሰረተው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1962 ዓ.ም. ነበር።
በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል በሚገኘው በዚህ መጠለያ በአሁኑ ወቅት እስከ 350 የሚገመቱ 'ሎክሶዳንታ አፍሪካና' የሚባል ዝርያ ያላቸው ዝሆኖች ይገኛሉ።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በመጠለያው በብዛት መስፈር ጀመሩ። ዝሆኖች ተገፍተው ተገፍተው ሁለት ሸለቆ ውስጥ እየኖሩ ነው።
“አሁንም ሰዎች ወደ ሸለቆዎቹ እየገቡ ደን እየመነጠሩ ማረስ እና ቤት መስራት ጀመሩ በዚህ ምክንያት የሰው እና የዝሆን ግጭት ጨምረ” በማለት አቶ አደም መሐመድ ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ሰዎች ወደ ዝሆኖቹ የመኖሪያ አካባቢ ይዞታቸውን እያሰፉ በመሄዳቸው በተፈጠረው ግጭት ከ2014 ወዲህ በእንስሳቱ አማካይነት ለህልፈት ከተዳረጉት ሰዎች በተጨማሪ 15 ዝሆኖች መገደላቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
ለዝሆኖቹ ሞት ዋነኛ ምክንያቱ ለእርሻ መሬት ማስፋፋት ሲባል በሰዎች መገደል እና እንስሳቱ በሚገጥማቸው የምግብ እጥረት ምክንያት በሚፈጠር ረሃብ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለጥርሳቸው ሲባልም የሚገደሉ ዝሆኖች እንዳሉ ተናግረዋል።
በዝሆኖቹ መጠሊያ ውስጥ ሰፍረው ያሉ ሰዎች ደግሞ ከእንስሳቱ ጋር በሚፈጠር ግጭት በሚደርስባቸው ጥቃት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ አቶ አደም ገልጸዋል።
ዝሆኖቹ ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ በኩምቢያቸው በማንሳት ወደ ላይ አርቀው ሰዎችን አፈናጥረው ስለሚወረውሩ፣ ሰዎቹ ከመሬት ጋር ክፉኛ ስለሚጋጩ የአብዛኞቹ ሕይወት ለህልፈት ይዳረጋል።
ዝሆኖቹ በሰዎች ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ባሻገር ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ በሆኑ ምክንያቶች የዝሆኖቹ የራሳቸው ህልውናም አሳሳቢ አደጋ ላይ መውደቁን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከ3ሺህ የማያንሱ ሰዎች ወደ ዝሆኖቹ መጠለያ መግባታቸው በመጥቀስ፤ ይህም ሕገ ወጥ አደን እና የመኖ እጥረት የፈጠረው ረሃብ ለዝሆኖቹ ደኅንነት ከፍተኛ አደጋ ሆኗል ይላሉ።
ዝሆን በቀን እስከ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ 200 ሊትር ውሃ እና ከ250 አስከ 300 ኪሎ ግራም እንደሚመገብ እንስሳ በመሆኑ ለደኅንነታቸው ሲባል መጠለያው ለእንስሳቱ መኖሪያነት ብቻ መተው እንዳለበት አቶ አደም አጽንኦት በመስጠተር አሳስበዋል።
“ሰዎች ወደ መጠለያው እየገቡ ዝሆኖች ላይ ይጮሃሉ” የሚሉት አደም መሐመድ፤ ዝሆን ጩኸት ስለማይወድ አካባቢውን ጥሎ እንደሚሄድም ይናገራሉ።
“ዝሆን ከተጨነቀ፣ ከተረበሸ እና ምግብ ካጣ እንደልቡ ሰለማይራባ፤ ሳይረበሽ በሰላም እንዲኖር መጠለያው ከሰው ነጻ መሆን አለበት።”
በዚህ ሁኔታ በመጠለያው ውስጥ ያሉት የዝሆኖች ቁጥር እየቀነሰ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በየዓመቱ ከ10 እስከ 12 ዝሆኖች እየሞቱ በመሆናቸው ብዛታቸው እየቀነሰ ይገኛል።
“አሁን ያለው ሁኔታ ለዝሆኖቹ ጥበቃ እና ደኅንት አመቺ ሳይሆን በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ዝሆኖቹ ሊጠፉ ይችላሉ” የሚል ስጋት እንዳላቸው ኃላፊው አመልክተዋል።
ዝሆኖች በምሥራቅ ሐረርጌ ባቢሌ ውስጥ በስፋት ይኑር እንጂ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል፣ በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና በትግራይ ክልሎች ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ይገኛሉ።
በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ከግዙፎቹ እንስሳት በተጨማሪ በርካታ አጥቢ እንስሳት እና አእዋፋት ይገኙበታል።












