በደቡብ ኢትዮጵያ በርካታ አህዮች ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ እየሞቱ ነው

አህዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን ውስጥ የሚገኙ አህዮች ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ እየሞቱ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአካባቢው ነዋሪዎች በዞኑ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ሕብረተሰቡ ለዕለት ከዕለት የጭነት አገለግሎት የሚያውላቸው አህዮች ባላወቁት ሁኔታ በብዛት እየሞቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጎፋ ዞኑ በሚገኙት ዛላ፣ ደምባ ጎፋ እና ሳውላ ወረዳዎች እስካሁን ድረስ 148 አህዮች ባልታወቀው በሽታ መሞታቸውን የጎፋ ዞን የግብርና መመሪያ እንስሳት እና አሣ ሃብት ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ተመስገን ለቢበሲ አረጋግጠዋል።

ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የአህዮች ሞት በሦስቱ ወረዳዎች መመዝገብ መጀመሩን የሚገልጹት አቶ ሙሉቀን፤ በዛላ ወረዳ 64 አህዮች፣ በደምባ ጎፋ እና ሳውላ ወረዳዎች ደግሞ ከ70 ያላነሱ አህዮች ሞታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

በበሽታው የተያዙ አህዮች የበሽታውን ምልክት ባሳዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሞቱ የሚገልጹት አቶ ሙሉቀን፤ ምንነቱ እስካሁን ባልታወቀው በሽታ የሚያዙት አህዮች የተለያዩ ምልክቶች ይታዩባቸዋል።

አህዮቹን ለሞት የሚዳርጋቸው በሽታ ከሚያሳየው ምልክቶች መካከል ባለቡት ቦታ ሆነው መሸከርከር፣ መንቀጥቀጥ፣ ሲተነፍሱ አንገታቸውን ማስረዘም፣ በአፋቸው አረፋ መድፈቅ እንደሚታይባቸው ኃላፊው ገልጸዋል።

የሽታው ምልክት የሚታይባቸው አህዮች በፍጥነት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ጨምረው ተናግረዋል።

“ምልክቱን የሚያሳዩት አፋጠኝ የሆነ ሞት ነው የሚያጋጥማቸው። ምልክቱ እንደታየባቸው በሰዓታት ውስጥ ነው የሚሞቱት።”

ይህ አህዮቹን በፍጥነት የሚገድለው ያልታወቀ በሸታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ እንስሳትን በመግደል በሕብረተሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ስጋትና ጫና እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።

የበሽታውን ምንነት ለማወቅ “ለወላይታ ሶዶ ላብራቶሪ ሪፖርት አድርገን ናሙና ወስደው ውጤቱን ለማረጋገጥ ወደ ሰበታ ላብራቶሪ መላካቸውን ነግረውናል” የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ በአሁኑ ወቅት በቀበሌ ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች አሰሳዎችን እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋማ ከብት ባለቤቶች የበሽታ ምልክት የሚታይባቸው እንስሳቶች ከጤነኛ እንስሳት በአፋጣኝ እንዲለዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የላብራቶሪ ውጤት እንደደረሰ ለእንስሳቱ ክትባት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ይህንኑ ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ ሙሉቀን ጨምረው ተናግረዋል።

በዞኑ ከ35ሺህ በላይ አህያዎች እንዳለ የሚገልጹት አቶ ሙሉቀን፤ በማኅብረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ አህዮች ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ጠቃሚ የቤት እንስሳ ናቸው ይላሉ።

ኢትዮጵያ በአህዮች ብዛት በዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት አንዷ ስትሆን፣ አህዮች በገጠርና በከተሞች ውስጥ ከባድ የጭነት አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።

በእነዚህ እንስሳት ላይ የሚከሰት የጤና ችግር እና ሞት በተለይ በገጠሩ ሕዝብ ላይ ከባድ ጫናን ማስከተሉ የማይቀር እንደሆነ ይታመናል።