ዋትስአፕ አዲስ የግላዊ መረጃ መጠበቂያ ገጽታዎችን ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ባለቤት የሆነው ሜታ በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው ዋትስአፕ አዲስ የተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ መጠበቂያ ዘዴን ይፋ አደረገ።
በዚህም ተጠቃሚዎች በቡድን ከሚደረጉ ምልልስሶች ምንም ሳያስታውቁ መውጣት፣ በበይነ መረብ ላይ የሚታዩ መረጃዎቻቸውን መቆጣጠርና አንድ ጊዜ በሚታዩ መልዕክቶች ላይ ያሉ ምስሎችን መገደብ ይችላሉ።
የግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ሜታ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፋጻሚ ማርክ ዛከርበርግ እንዳለው ይህ አዲስ ገጽታ የዋትስአፕ መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ “ፊት ለፊት የመነጋገርን ያህል ግላዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያስችላል።”
እነዚህ የዋትስአፕ አዲስ ገጽታዎች የሚካሄዱ የማስተዋወቂያ ዘመቻዎችን ተከትሎ ከዩናይትድ ኪንግደም ጀምሮ ከቀጣዩ መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋሉ።
በዓለም ዙሪያ ታዋቂ የሆነው ዋትስአፕ የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ በአሁኑ ጊዜ ለቡድን አገልግሎት በሚጠቀሙት ዘንድ አንድ አባል ከቡድኑ ሲወጣ ወይም እንዲወጣ ሲደረግ ሁሉም አባላት እንዲያውቁ ያደርጋል።
ይህ እንዳይሆን የማድረጊያ መንገድ ቢኖርም፣ ነገር ግን አንድ አባል ሌሎች ሳያውቁ ከቡድኑ መውጣት ቢፈልግ ሁሉም ለማወቅ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ቡድኑን ማንም ሳያውቅ መልቀቅ የሚፈልጉ ሰዎችን ምቾት የሚነዳ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል።
አሁን ግን፣ ከነበሩበት ቡድን መልቀቅ የሚፈልጉ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች የቡድኑ መሪ ብቻ በሚያውቅበት ሁኔታ ማንም ሳያውቅ መልቀቅ እንዲችሉ ያደርጋል።
ይህ የዋትስአፕ አዲስ ገጽታ “ተጠቃሚዎች መልዕክቶቻቸው እና ግላዊ መረጃዎቻቸው የበለጠ እንዲቆጣጠሩ ለማስቻል የታሰበ ነው” ስትል የሜታ ኃላፊ አሜ ቮራ ተናግራለች።
ጨምራም “ግላዊ እና ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ የመልዕክት ምልልሶችን ለማድረግ ዋትስአፕ በጣም አስተማማኙ መድረክ ነው ብለን እናምናለን።”
“በጽሁፍ፣ በድምጽ እና በመስል የሚደረገፉ የምልዕክት ልውውጥ አገልግሎት የሚሰጡ ዓለም አቀፍ መተግበሪያዎች እንዲህ አይነቱም የደኅንነት ጥበቃ በዚህ ደረጃ አይሰጡም” ብለልች።
አዲሱ የዋትስአፕ ገጽታ መተግበሪያውን እየተጠቀምን መሆናችንን ለመረጥናቸው ሰዎች እንዲያሳይ ወይም ለማንም እንዳያሳይ ማድረግም ያስችላል ተብለወል።
“ተጠቃሚዎች በሚገለገሉበት መተግበሪያ ላይ የበለጠ ቁጥጥር እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፣ ስለዚህም ይህንን ለተጠቃሚዎች መስጠት ጥሩ ነገር ነው” ሲሉ በአለን ተሪንግ ተቋም ውስጥ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት የንስ ዎንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ተጠቃሚዎች አዳዲሶቹን ገጽታዎች እንዲጠቀሙ ካልተጠየቁ ወይም በደንብ እንዲያውቋቸው ካልተደረጉ አገልግሎቶቹ የሚኖራቸው ውጤት ውስን ይሆናል።
“ገጽታዎቹ በእራሳቸው ተግባራዊ የሚሆኑ፣ ስለጠቀሜታቸው ካላወቁና ያሉ አገልግሎቶቹን አማራጮች እንዲያውቁ ካልተደረጉ ውጤት አይኖረውም” ብለዋል።












