ለተለያዩ ነገሮች የሚጠቀሙት የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) ምን ያህል ጠንካራ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሠሞኑን ከተሰሙ ዜናዎች መካከል አንዱ የተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማት የኢሜይልና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የይለፍ ቃላቸው ተሰብሮ ገጻቸው 'ሃክ' መደረጉ ነው።
ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። እርስዎ ኮምፒውተርዎን እና መረጃዎችዎን ከመዝባሪዎች በቀላሉ መታደግ እንዲችሉ ቀጣዩን አጭር መረጃ አሰናድተናል።
* * * *
ከቤትዎ ወደ ገበያ አልያም ጎረቤት ለመሄድ ሲወጡ በርዎን መለስ አድርገው ብቻ አይሄዱም። በሚገባ መቆለፉን ሳያረጋግጡ በሄዱበት ቤትዎ ሌባ ገብቶ ያለዎትን ሙልጭ አድርግዎ ቢዘርፍዎት ምን ይላሉ?
ምን ጊዜም ቤትዎ አልያም የቤትዎ አጥር ጠንካራ መሆኑን፣ ዘራፊዎች ሰብረው መግባት እንደማይችሉ ለራስዎ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ሲሆን ሲሆን ውሻ ያሳድጋሉ፣ አጥርዎ ላይ ሽቦ ያደርጋሉ።
የኮምፒውተር ይለፍ ቃልም መጠናከር ያለበት ልክ እንዲሁ ነው።
ጠንካራ ካልሆነ በቀላሉ የመረጃ መንታፊዎች ወደ ኢሜልዎ፣ ኮምፒውተርዎ ሰተት ብለው በመግባት ያለዎትን መረጃ አደባባይ ያሰጡታል፣ አልያም ይቆልፉት እና ማስለቀቂያ ገንዘብ ይደራደራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock
መረጃ መንታፊዎች እንዴት ወደ ኮምፒውተርዎ ሊገቡ ይችላሉ?
ባለሙያዎች የመረጃ መንታፊዎች ሦስት የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው የይለፍ ቃልዎን ሰብረው ወደ ኮምፒውተርዎ አንደሚገቡ ይናገራሉ።
በስፋት የሚታወቀው ፊሺንግ ስካም (Phishing scams) የሚባለው ነው። ይህም ማለት አንድ የሚታወቅ ድርጅት ድረ ገጽን በመላክ እና ሎተሪ እንዳሸነፉ በመግለጽ ኮድ እንዲያስገቡ መጠየቅ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በግምት መሞከር ነው።
በርካቶች የኢሜል የይለፍ ቁጥራቸው 123456 መሆኑ ይነገራል። ይህ የሆነው ያለምክንያት አይደለም። እንዳይረሱት ፈልገው እንደሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ደግሞም እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ በዓለም ላይ ከ23.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮምፒውተር የይለፍ ቃላቸው 123456 ሆኖ ተገኝቷል።
በአንድ ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም ተደረገ ጥናት የበርካታ የኮምፒውተር የይለፍ ቃል ተመሳሳይ መሆኑን አሳይቷል።
ታዲያ እንዲህ በቀላሉ ሊገመቱ የሚችሉ የይለፍ ቃሎች ያለ ችግር በኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች አካውንታችን እንዲሰበር እና እንዲበረበር በር ይከፍታል።
የኮምፒውተር ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ቁጥሮችን በቅደም ተከተል በመጠቀም ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ስም መጠቀምም እንደ ይለፍ ቃል መጠቀም እጅጉን የተለመደ ነው።
እስቲ ልብ ይበሉ የልጅዎን ወይንም የባለቤትዎን፣ የእናትዎን አልያም የአባትዎን ስም፣ Love አልያም ደግሞ IloveYou በይለፍ ቃልነት ይጠቀሙ ይሆናል።
ይህም ለግምት በጣም ቀላል እና የመዝባሪዎቹን ሥራ የሚያቀል ይለፍ ቃል ሆኖ ተገኝቷል።
ሌላኛው በይለፍ ቃልነት በብዛት ሰዎች ተጠቅመውት የገነው ራሱ password የሚለውን ቃል ነው።
1111111 ይህንን እንደ ይለፍ ቃል የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም።
ታዋቂ እግር ኳስ ቡድኖች፣ ተጫዋቾቻቸው፣ የራሳቸውን ስም፣ የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን የልደት ቀን የሚጠቀሙ ሰዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ ቁጥር አላቸው።
የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች እነዚህ በቀላሉ የሚገመቱ ይለፍ ቃሎች የማይሳካላቸው ከሆነ አቅማቸውን አደራጅተው ይመጣሉ።
በአንድ ሰከንድ 8 ቢሊዮን የይለፍ ቃሎችን ማምረት የሚችል አልጎሪዝም ወይም ፕሮግራሞች በመጠቀም ኮምፒውተርዎን አልፈው ለመግባት ይሞክራሉ።
በዚህም ስድስት ፊደል ያላቸውን የይለፍ ቃሎች በሰከንድ ውስጥ፣ 12 ያላቸውን ደግሞ በሦስት ደቂቃ ውስጥ ሰብረው መግባት ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock
ታዲያ እንዴት ጠንካራ የይለፍ ቃል ሊፈጥሩ ይችላሉ?
በኮምፒውተርዎ አልያም በኤሜል አድራሻዎ በኩል የሚገኙ መረጃዎችን በሚገባ መጠበቅ ይኖርብዎታል።
የኮምፒውተር ሰርሳሪዎች የግል አካውንትዎን ሰብረው ከገቡ ሌሎች ማግኘት የሌለባቸውን መረጃ ሊያገኙ እና ጉዳት ሊያስከትሉብዎ ይችላሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን በእርስዎ አካውንት በመጠቀም ለሌሎች ሰዎች ያልተገባ መልዕክት በመላክ ግንኙነትዎን ያበላሻሉ።
ስለዚህ የማይረሱት ነገር ግን ጠንካራ የሆነ ይለፍ ቃል መጠቀም መልካም መፍትሄ ነው።
- ተገማች ነገርን አይጠቀሙ- የሚደግፉት የእግር ኳስ ቡድን ለይለፍ ቃልነት የሚመከር አይደለም። የሚደግፉት ብቻ ሳይሆን የሚነቅፉትም ቢሆን አይመከርም። ከስም ወጣ ያለ እና ትንሽ ለግምት የሚያስቸግር፣ ወሰብሰብ ያለ እንዲሆን ይመከራል።
- ቃል ሳይሆን ሐረግን ይምረጡ - የይለፍ ቃሎች ረዥም በሆኑ ቁጥር ለግምት ያስቸግራሉ። ስለዚህ ረዘም ያሉ ሐረጎችን ለይለፍ ቃልነት መጠቀም በእጅጉ ይመከራል። ለምሳሌ 'Itismydam' የሚለውን ሐረግ የመሰለውን መውሰድ እንችላለን።
- ትልልቁን እና ትንንሾቹን ፊደላት በማቀላቀል ይጠቀሙ- የይለፍ ቃል ሲጠቀሙ ሁሉንም ፊደላት በትልቁ አልያም በትንሹ ብቻ መጠቀም የመዝባሪዎቹን ሥራ ያቀለዋል። ስለዚህ ማቀላቀል ብልህነት ነው። ይህም የይለፍ ቃልዎ እንዳይገመት የማድረግ አቅም አለው። ለምሳሌም 'iTIsMyD@M'' ቢሆን ለመገመት እድሉን ያሳንሰዋል።
- ቁጥሮችን እና ምልክቶችን ቀላቅለው ይጠቀሙ- የይለፍ ቃልዎን የበለጠ ማጠናከር የሚፈልጉ ከሆነ ቁጥሮችን እና ምልከቶችን አቀላቅለው ይጠቀሙ። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ባየነው የይለፍ ቃል ምትክ ይህኛውን ብንተካ እንደማለት 'iTI5MyD@M' በማለት ለመስበር አሰቸጋሪ ማድረግ ይቻላል።
- ስለ ይለፍ ቃልዎ ለማንም አንዳይናገሩ- ይህ ምናልባት እርስዎም አስቀድመው የሚወስዱት እርምጃ ይሆናል። ነገር ግን የፈጠሩትን ጠንካራ የይለፍ ቃል በቀላሉ ሊያጡበት የሚችሉበት እድል በርካታ ነው። ለምሳሌ በጋራ ከሌሎች ጋር በሚጠቀሙት ኮምፒውተር ላይ መጻፍ፣ ኮምፒውተርዎን ክፍት አድርገው መሄድ፣ ለጓደኛዎ የይለፍ ቃልዎን ማጋራት እና የይለፍ ቃልዎ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ በመግለጽ መናገር ለኮምፒውር መዝባሪዎችና ሰርሳሪዎች ሊያጋልጥዎት ይችላል።
በስተመጨረሻም እዚህ በአስረጅነት የተጠቀምንባቸውን የይለፍ ቃሎች እንዳይጠቀሙባቸው አደራ እንላለን።
















