በርካቶች ከስማርት ፎን ይልቅ ‘ኤርጌንዶ’ ስልክ ለምን ይመርጣሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ17 ዓመቷ ሮበን ዌስት ከጓደኞቿ ትለያለች። የምትይዘው ተንቀሳቃሽ ስልክ ዘመን ያለፈበት ነው።
ስልኳ ስማርት ፎን ስላልሆነ እንደ ጓደኞቿ ቲክ ቶክ እና ኢንስታግራም አታይም።
ስልኳ አይፎን አይደለም። ስለዚህም የስልክ ጥሪ ከመቀበል፣ የጽሑፍ መልዕክት ከመላክ ያለፈ እምብዛም አገልግሎት አይሰጥም።
ስልኳ መተግበሪያ አይጭንም። ኢንተርኔት አያስጠቅምም። ምናልባት ራድዮ ትሰማበት ይሆናል።
ይህ ስልክ እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ነው።
ሮበን ቀድሞ ስማርት ስልክ ነበራት። ከዚያ ግን ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ ጥንታዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ለመመለስ ወሰነች።
የስልክ መለዋወጫ ሱቅ ውስጥ ሳለች ዋጋው ርካሽ የሆነ ስልክ ተመለከተች። ወደ ሱቁ ያመራችው ለስማርት ስልኳ መለዋወጫ ለመግዛት ነበር።
ነገር ግን የቀድሞውን ስልክ ዋጋ ርካሽነት ስታይ ተደነቀች።
"ያንን ጥንታዊ ስልክ እስከገዛሁበት ቅጽበት ድረስ ስማርት ስልክ ምን ያህል ሕይወቴን ተቆጣጥሮት እንደነበር አልገባኝም ነበር" ትላለች።
ስማርት ስልኳ ላይ የሌላት የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ የለም።
"በጣም ብዙ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እጠቀም ነበር። ስልኬ ላይ የማጠፋውን ጊዜ ያህል ሥራዬ ላይ አላጠፋም" ትላለች።
ከዚህ በኋላ ወደ ስማርት ስልክ የመመለስ ዕቅድ የላትም።
"አሁን ያለኝ ጥንታዊ ስልክ ለሥራ ጊዜ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ስማርት ስልክ ስለሌለኝ የሚጎድልብኝ ነገር የለም" ስትል ውሳኔዋን ታስረዳለች።
ብዙዎች የሮበንን ውሳኔ ይጋራሉ። ስልኮች ከቀን ወደ ቀን እየተቀናጡ ቢመጡም ወደ ቀደምቶቹ ስልኮች ለመመለስ የሚመርጡ እየተበራከቱ መጥተዋል።
ሲምራሽ የተባለው ድርጅት በሠራው ጥናት መሠረት፤ እአአ ከ2018 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት የጥንታዊ ስልኮች ተፈላጊነት ወደ 89 በመቶ ከፍ ብሏል።
ምን ያህል ጥንታዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እንደሚሸጡ ግልጽ ቁጥር ባይኖርም፤ አንድ ሪፖርት እንደሚጠቁመው አምና የእነዚህ ስልኮች ሽያጭ አንድ ቢሊዮን ሊደርስ ነበር።
በሌላ በኩል አምና የተሸጡ ስማርት ስልኮች ቁጥር 1.4 ቢሊዮን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴሎቲ የተባለ ድርጅት አምና በሠራው ጥናት መሠረት፤ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከአስር ሰዎች አንዱ ጥንታዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ይጠቀማል።
የስልክ አጥኚ አርነስት ዶኩ "ጥንታዊ ስልክ መያዝ ፋሽን ሆኗል። የቀደመው ዘመን የሚናፍቃቸው ሰዎችም አሉ። ቲክ ቶክ ላይ እነዚህ ቀደምት ስልኮች መታየታቸው ተወዳጅ እንዲሆኑም አድርጓል" ይላሉ።
ብዙዎቻችን የመጀመሪያ ስልካች ጥንታዊው ተንቀሳቃሽ ስልክ ነው። በአገራችን በተለምዶ ኤርጌንዶ የሚባለው ዓይነት።
2017 ላይ ኖኪያ 3310 ስልኩን በድጋሚ አምርቷል። ይህ ስልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ የበቃው በ2000 ነበር።
ኖኪያ ይህንን የስልክ ዓይነት በድጋሚ ወደ ገበያ ለመመለስ የወሰነው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ ስልኮችን ለማስተዋወቅ ነው።
የስልክ አጥኚው አንድ የማይክዱት ሐቅ ስማርት ስልኮች የሚሰጡት አገልግሎት ተወዳዳሪ እንደሌለው ነው።
"ሆኖም ግን ጥንታዊ ስልኮች ረዥም ጊዜ ይቆያሉ። ባትሪያቸውም ቶሎ አያልቅም" ሲሉ ያስረዳሉ።
የሥነ ልቦና ባለሙያው ፕሪዝሜክ ኦልዛክ ስማርት ስልኩን በኖኪያ 3310 የለወጠው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር።
መጀመሪያ ላይ ስልኩን ለመለወጥ የወሰነው ባትሪው ረዥም ሰዓት እንዲቆይ ነበር።
ኋላ ላይ ግን ጥንታዊ ስልክ መያዝ ሌሎችም ጥቅሞች እንዳሉት ተረዳ።
ዋነኛው ጥቅም ማኅበራዊ ሚዲያን መቀነስ ነው።
"ድሮ ድሮ ፌስቡክ ሳይ ወይም ዜና ለማንበብ ስልኬን ስጎረጉር ነበር የምውለው። ይሄ አስፈላጊ አልነበረም። አሁን ላይ ለእራሴና ለቤተሰቤም በቂ ጊዜ መስጠት ጀምሬያለሁ" ይላል።
ጨምሮም "ላይክ እና ሼር በማድረግ የተጠመድኩበት ዘመን አክትሟል። ለሰዎች ስለ ሕይወቴ ከመናገር ተቆጥቤ ኑሮዬ የግሌ ሆኗል" ሲል ጥቅሙን ያስረዳል።
በእርግጥ ከስማርት ስልክ መላቀቅ ለሥነ ልቦና ባለሙያው ቀላል አልነበረም።
የትም ቦታ ሲሄድ የአውቶብስ ፕሮግራም፣ ሬስቶራንት እና ሌላም መረጃ የሚያገኘው ከስማርት ስልኩ ነበር።
ስማርት ስልክ መያዝ ሲያቆም ግን የት እንደሚሄድ፣ በየት በኩል እንደሚሄድና ሌላም የሚያስፈልገውን መረጃ ከቤቱ አዘጋጅቶ ከመውጣት ውጭ አማራጭ አልነበረውም።
ላይት ፎን፤ ኒው ዮርክ ውስጥ የሚገኝ የቀደምት ስልኮች አምራች ነው።
ስልኮቹ ማኅበራዊ ሚዲያ የላቸውም። ኢንተርኔትም አያገኙም።
ሆኖም ግን ከቀደምት ስልኮች መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎባቸው ተገልጋዮች ሙዚቃ እና ፖድካስት እንዲሰሙ ዕድል ይሰጣሉ።
"እንደ ዜና፣ ኢሜል፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ያሉ አስጨናቂ ገጾች በስልካችን ላይ አይጫኑም" ይላል አምራች ድርጅቱ።
በ2021 የስልክ ሽያጭ መጠኑ በ2020 ከነበረው 150% ከፍ ብሏል።
ስልኮቹን ከ99 ዶላር ጀምሮ መግዛት ይቻላል።
የስልክ አምራች ድርጅቱ አጋር መስራች ካይዊ ታንግ እንደሚለው፤ ስልኮቹ መጀመሪያ ላይ የተመረቱት ሰዎች እንደ ሁለተኛ ስልክ እንዲጠቀሙባቸው ነበር።
ስማርት ስልክ ያለው ሰው ከስልኩ እረፍት መውሰድ ሲፈልግ በእነዚህ ስልኮች እንዲጠቀም ታስቦ ነበር የተሠሩት።
ነገር ግን ግማሽ ያህሉ የድርጅቱ ደንበኞች ጥንታዊ ስልኮችን ብቸኛ ስልካቸው ለማድረግ ወስነዋል።
"ስማርት ስልክ የሰው ልጆችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ይህም እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ አይሄድም" ይላል።
ይህንን ያስተዋሉ ሰዎች በሕወታቸው ለውጥ ስለሚፈልጉ ወደ ጥንታዊ ስልኮች እየተመለሱ ይገኛሉ።
የስልክ አምራች ድርጅቱ ደንበኞች ከ25 እስከ 35 ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ፕ/ር ሳንድራ ዋቸር እንደሚሉት፤ አንዳንዶች ቀላል ስልክ ስለሚፈልጉ ጥንታዊ ስልክ መያዝ ይመርጣሉ።
"አሁን ላይ ስማርት ስልክ መዝናኛ ነው። የዜና ምንጭ ነው። ካርታ ነው። የውሎ መዝገብ ነው። መዝገበ ቃላት ነው። የገንዘብ ቦርሳ ነው። ስማርት ስልክ ሁሌም እንዳንላቀቀው አስሮናል" ሲሉ ባለሙያዋ ያብራራሉ።
የስማርት ስልክ በእያንዳንዱ የሕይወት ክፍል ጣልቃ መግባት የሚረብሻቸው ሰዎች ወደ ጥንታዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እየተመለሱም ነው።
"የድሮ ስልክ የሚይዝ ሰው ስልኩን ለተገባ ጥቅም ብቻ ነው የሚያውለው። ከስልክ ውጭ ሌሎች ነገሮች ላይ ለማተኮርም ጊዜ ያገኛል። ስማርት ስልክ የሚሰጠው ያልተገደበበ ምርጫ የሰዎች ደስታ የሚቀማ እና የሚረብሽ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ ባለሙያዋ።
ብዙዎች ሮበንን 'መቼ ነው ወደ ስማርት ስልክ የምትመለሽው?' እያሉ ይጠይቋታል።
እሷ ግን ወደ ስማርት ስልክ የመመለስ አንዳችም ፍላጎት ያላት አትመስልም።
















