በአፍሪካ የመጀመሪያው ስማርት ስልክ ማምረቻ ፋብሪካ በሩዋንዳ ተከፈተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩዋንዳ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ስማርት ስልክ ማምረቻ ከፈተች። ፋብሪካው በዋና ከተማዋ ኪጋሊ የሚገኝ ሲሆን በምረቃው ላይ ፕሬዚደንት ፓል ካጋሜ ተገኝተዋል።
በማራ ግሩፕ በተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ ማራ ኤክስና ማራ ዜድ ስማርት ስልኮችን የሚያመረተው ይህ ፋብሪካ ስልኮቹ የጎግልን አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም እንደሚጠቀሙ ተናግሯል።
ስልኮቹ 5500 ብርና 3700 ብር አካባቢ ዋጋ ተተምኖላቸዋል።
ሰኞ ዕለት ፋብሪካውን ጋዜጠኞች ተዟዙረው እንዲጎበኙ ከተደረገ በኋላ "ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያው ስማርት ስልክ ማምረቻ ነው" ብለዋል የማራ ግሩፕ የበላይ ኃላፊ አሺሽ ታካር ለሮይተርስ።
ታካር አክለውም ፋብሪካው ዒላማው ያደረገው ጥራት ላይ መሠረት አድርገው ለመክፈል የተዘጋጁ ግለሰቦችን ነው።
በአፍሪካ ውስጥ ከሚሸጡ በርካታ ስልኮች መካከል አብዛኞቹ የሚመጡት ከቻይና ነው። እነዚህ ስልኮች ሁለት ሲም የሚወስዱ እንዲሁም ማራ ግሩፕ ከተመነው ዋጋ ባነሰ ለቀበያ የሚቀርቡ ናቸው።
በኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የተለያዩ መለዋወጫዎችን ከቻይና በማስመጣት የሚገጣጠሙ ስማርት ስልኮች እንዳሉ ሚስተር ታከር ይናገራሉ።
"እኛ በማምረት ደረጃ የመጀመሪያዎቹ ነን። ማዘር ቦርዱን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ንዑሳን ክፍሎቹን የምናመርተው እዚሁ ነው። በእያንዳንዱ ስልክ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቃቅን ነገሮች አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
በቀን 1200 ስልኮችን ያመርታል የተባለው ይህ ፋብሪካን ለማቋቋም 24 ሚሊየን ዶላር እንደወጣበት ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ካጋሜ ፋብሪካው የሩዋንዳውያንን ስማርት ስልክ ተጠቃሚነት እንደሚጨምር ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
በአሁኑ ሰዓት በሩዋንዳ ከሚገኙ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች 15 በመቶው ብቻ ስማርት ስልክ ይጠቀማሉ።

















