የኩላሊት በሽታን መርምሮ ውጤት የሚነግረው መተግበሪያ [አፕ]

የተንቃሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ [አፕ] ነው። ሰዎች የኩላሊት በሽታ ይኑርባቸው፤ አይኑርባቸው በቀላሉ መለየት ያስችላል።
የሕክምና ባለሙያዎች ይህንን መተግበሪያ 'ሕይወት አድን' የሚል ስም ሰጥተውታል፤ የሕክምና አገልግሎት በደቂቃ ውስጥ እንዲሰጥ ማድረግ ችሏልና።
የኩላሊት በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል፤ አንዱ ደግሞ ከደም ጋር የተያያዘ ነው። ቢያንስ ከአምስት ሰዎች አንድ ሰው በኩላሊት በሽታ እንደሚጠቃ ይነገራል።
በሽታው ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን ያጠቃል። በጊዜ የሕክምና እርዳታ ካልተገኘ ለከፋ አደጋም ሊያጋልጥ ይችላል።
በእንግሊዝ ብቻ በየዓመቱ 100 ሺህ ገደማ ሰዎች በኩላሊት በሽታ ምክንያት ሕይዋታቸውን ያጣሉ።
አዲሱ የሞባይል መተግበሪያ በፊት ሰዓታት ይወስድ የነበረውን የኩላሊት በሽታ ምርመራ በ14 ደቂቃ ውስጥ ብቻ እንዲከናወን አስችሏል።
'ስትሪምስ' የተሰኘው መተግበሪያ ዋነኛ ተግባር በሰዎች ኩላሊት ወስጥ ያለውን አላስፈላጊ ቆሻሻ መጠን ለይቶ ለሕክምና ባለሙያዎች ያሳውቃል። የሕክምና ባለሙያዎች ውጤቱ የሚደርሳቸው በመተግበሪያው አማካይነት ነው።

መተግበሪያውን የተጠቀሙ ሆስፒታሎች የሕክምና ወጭ ከበፊቱ እጅጉን እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራሉ።
ነርስ ሜሪ ኤመርሰን መተግበሪያው በሥራዋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ለቢቢሲ ትናገራለች።
«ከየትኛው አካበቢ የሚመጡ መልዕክቶችን ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ ማወቅ መቻል እጅግ በጣም ድንቅ ነገር ነው።»
በሌላ የጤና እክል ምክንያት ኩላሊት ሥራውን በአግባቡ መከወን ሲያቅተው አጣዳፊ የኩላሊት በሽታን ያስከትላል። ከቀላል የኩላሊት ጉዳት ጀምሮ ኩላሊት ከሥራ ውጭ እስኪሆን ድረስ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
የኩላሊት በሽታ በጊዜ ሕክምና ካላገኘ ከከፍ አደጋ ጀምሮ እስከሞት ድረስ ሊያጋልጥ ይችላል።













